1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአረብ ሊግና የእስላማዊ አገሮች ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ

ገበያው ንጉሤ
ረቡዕ፣ መስከረም 7 2018

ትናንት በቀጠር የተካሄደው የአረብና ሌሎች እስላም አገሮች መሪዎች ጉባኤ፤ እስራኤል ባለፈው ማክስኞ በዶሀ የሀማስ የሰላም ተደራዳሪዎች ላይ የፈጸመችው ጥቃት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ፤ የሰላም ድርድሩን የሚያፈርስ ሕገወጥ ድርጊት ሲል ኮንኗል።

ዶሀ ቀጠር ላይ የተካሄደው የአረብ ሃገራት መሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ
ሰኞ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓም ዶሀ ቀጠር ላይ የተካሄደው የአረብ ሃገራት መሪዎች አስቸኳይ ጉባኤ ምስል፦ Mahmud Hams/AFP

የአረብ ሊግና የእስላማዊ አገሮች ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ

This browser does not support the audio element.

 

ከሀምሳ በላይ የሚሆኑት  የጉባኤው ተሳታፊ የአገር መሪዎች፤ እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ያለው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃትና የአገሮችን ሉዓላዊነት በመጣስ የምትወስዳቸው እርምጃዎች በዝምታ ሊታለፍ አይገባውም በማለትም ለዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ በተለይም ለአሜሪካ ጥሪ አቅርበዋል።

የእስራኤል ምላሽና ለአሜሪካ የቀረበ ጥሪ

አሜሪካ ዋና የእስራኤል ወዳጅና አጋር መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን የራሷምወዳጅና የሰላም አደራዳሪ በሆነችው ቀጠር ላይ የተወሰደውን ሕገወጥ እርምጃ በሚገባው ልክ አለማውገዛቸው እስራኤል ተመሳሳይ ወንጀል እንድትፈጽም የሚያበረታታ ነው በማለት ቅሬታቸውን ማሰማታቸውም ተገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስተር ናታኒያሁ ግን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባሉበት፤ ባለፈው እሑድ በሰጡት መገልጫ፤ እስራኤል ሀማስ አለ በሚባልበት ቦታ ሁሉ ወታደራዊ እርምጃ ከመውሰድ እንደማትቆጠብ ያሳወቁ ሲሆን፤ መሪዎቹ አሜሪካ በተለይም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጠ/ሚኒስትር ናታኒያሁ እየወሰዷቸው ካሉት ወታደራዊ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ ጫና እንዲያደርጉ አሳስበዋል።  

የጉባኤው መግለጫ ይዘትና በእስራኤል ላይ የተሰማው ቁጣ

መሪዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ እስራኤልን፤ የአገሮችን ሉዓላዊነት በመጣስ፣ ጋዛ ላይ ሰብአዊና የጦር ወንጀሎችን በመፈፈጸምና የሚደረጉ የሰላማዊ ጥረቶችን በማደናቀፍ ተጠያቂ አድርገው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእስራኤል ላይ ዝምታውን እንዲሰብር ጠይቀዋል።

መሪዎቹ በጉባኤው ላይ ያሰሟቸው ንግግሮችም እስራኤልን በክፍተኛ ደረጃ ከማውገዝአልፎ ቁጣ የተስተጋባባቸው እንደነበሩ ተገልጿል። የግብጹ መሪና ሌሎቹም እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ ይሁን በሌሎች የአካባቢው አገሮች ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ አካባቢውን የግጭትና ጦርነት ቀጣና እያደረገች መሆኑን የሚገልጹ ንግግሮች ማሰማታቸው ተዘግቧል።

የአረብ ሊግና የባሕረሰላጤው አገሮች የጋራ ወታደራዊ ኃይል ግንባታ ዕሳቤ  

 የአረብና የባሕረሰላጤ አገሮች የጋራ ወታደራዊ ኃይል አስፈልጊነትም በጉባኤው የተነሳ መሆኑ ታውቋል። ሆኖም ግን በአገሮቹ መካከል ያለው ልዩነትና በእስራኤል ላይ ያላቸው የተለያየ አቋም ወደ እዚህ ዓይነት ወታደራዊ ቡድን ምስረታ ለመግባት አይስችላቸውም ነው ተንታኖች የሚሉት። ባጠቃላይም ጉባኤው በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ቁጣ የተስተጋባበትና ውግዘት የተሰማበት ቢሆንም ተጨባጭ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ውሳኔ የተላለፈበት እንዳልሆነ ነው ከጉባኤው የወጡ መረጃዎች የሚገልጹት።

የቀጠር ዋና ከተማ ዶሀ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችምስል፦ Ibraheem Abu Mustafa/REUTERS

ከጉባኤው የወጡ ፍሬ ነገሮች

በመካከልኛ ምሥራቅ ጉዳይ ጸሐፊና ተመራማሪ የሆኑት ሚስተር ጀምስ ዴርሴይ ከጉባኤው ሦስት ነገሮች ወጥተዋል ይላሉ፡ «አንደኛ በጋራ መግለጫውም ሆነ መሪዎቹ ባሰሟቸው ንግግሮች በእስራኤል ላይበከፍተኛ ደረጃ ቁጣና ተቃውሞ ተስተጋብቷል። ሁለተኛ፤ አንንዳንዶቹ የጉባኤው ተሳታፊ አገሮች በሚቀጥለው ሳምንት በኒውዮርክ በሚካሂደው ጉባኤ እስራኤል የድርጅቱን ቻርተር በመጣስ ከአባልነት እንድትታገድ የሚጠይቁትን ሊቀላቀሉና ደቡብ አፍርካ በእስራኤል ላይ ያቀረብችውን የዘር ማጥፋት ክስ ሊደግፉ ይችላሉ። ሦስተኛ፤ የአረብና የባሕረ ሰላጤው አገሮች የጋራ የመከላከያ ኃይል ለመገንባት ያላቸውን ዕቅድ እነቃቅቶታል» በማለት ጉባኤው ከተጨባጭ እርምጃዎች ባሻገር የፖለቲካ አንድነት የታየበትና የተስጋባበት መሆኑን ገልጸዋል።

በእስራኤል ላይ የተስማው ቁጣና ውግዘት ወዴት ሊያመራ ይችላል?

የጉባኤው መግለጫና በመሪዎች የተሰሙ ጠንካራ ንግግሮችና ፍረጃዎች አገሮቹን ወደ ግጭትና ጦርነት ይከታቸው ይሆን? ተብለው የተጠይቁት በለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚስክስ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ፕሮፌሰር ፋዋዝ ገርጌስ፤ «አይመስለኝም ምክኒያቱም ግብጽም ሆነች፣ ዮርዳኖስ ወይም ሳኡዲ አረቢያ ወይም ቀጠር ከእስራኤል ጋር ወደ ግጭት መግባት አይፈልጉም። ባንጻሩ ባለፉት ወራት እንዳየነው የአረብ መሪዎች የእስራኤልን ሕዝብ ነው እያሳሰቡና እያስጠነቀቁ ያሉት፤ መሪዎቹ አሜሪካንን ነው ጠቅላይ ሚንስተር ናታኒያሁን ከጦረኛነት እንዲታቀቡ ጫና እንዲፈጥሩ እየጠየቁ ያሉት» በማለት አገሮቹ በእስራኤል ፍልስጤም ግጭት በቀጥታ ለመግባት የማይፈልጉ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ገበያው ንጉሤ

 ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW