የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ተፈጸመ
ሐሙስ፣ መስከረም 19 2015
መስከረም 17 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተከርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ማቲያስ፤ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ ሚኒስትሮች፣ አርቲስቶች፣ የድምፃዊው ወዳጆች እና አድናቂዎች ተገኝተዋል።
«መሰለ ጌታሁን እባላለሁ። የዘፈን ግጥም ደራሲ ነኝ። ማዲ ነፍሱን ይማረውና በጣም በጣም ተግባቢ፤ በጣም ደግ ችግር እንኳን አርቲስቶች መሀል አንድ ነገር ሲፈጠር ሰው አስተባብሮ በመርዳት የሚታወቅ ልጅ ነው። በጣም ለጋስ የሆነ ልጅ ነው። በጣም ትሁት የሆነ ፈጣሪውን የሚፈራ ልጅ ነው ማዲንጎ»
ዛሬ ከቀኑ 6 ሰአት በወዳጅነት አደባባይ የአርቲስት ማዲንጎ የሞያ አጋሮቹ፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ቤተሰቦቹ እና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት የስንብት ዝግጅት መከናወኑን የአዲስ አበባ ወኪላችን ሐና ደምሴ ዘግባለች። በቀድሞው ጎንደር ክፍለ ሀገር አዘዞ ተወልዶ ደብረታቦር ያደገው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ከአባቱ ከአቶ አፈወርቅ መንግሥቱ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ሀገርነሽ ዋሴ ሚያዝያ 10 ቀን፣ 1970 ዓ.ም መወለዱን መረጃዎች ያሳያሉ። በቅርብ የሚያውቁት ቅን እና መልካም ሰውነቱን የሚገልጹለት አርቲስት ማዲንጎ የአንዲት ሴት ልጅ አባት ነበር።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሐና ደምሴ
ታምራት ዲንሳ