1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአርጎባ ጀበርት ይፋት ሱልጣኔት ሹመት

ሰኞ፣ ሐምሌ 3 2015

የአርጎባ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን) ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ለዛሬ የታቀደውን የሱልጣኔት ሹመት ተቃውሞ ነበር፡፡ የበዓሉ አስተባባሪ አቶ እስማኤል ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት በአፋር ክልልም በአርጎባ ልዩ ወረዳ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነው ሁሉንም በእኩል ያገለግላሉ የተባሉ ሰው የተሾሙት፡፡

Argobba – Shonke Dorf Äthiopien
ምስል፦ DW

የአርጎባ ጀበርት ይፋት ሱልጣኔት ሹመትና ተቃውሞው

This browser does not support the audio element.

ለዘመናት ተቋርጦ የነበረውን የአርጎባ ጀበርት ይፋት ሱልጣኔት ሹመት በአርጎባ ልማት ማህበር አስተባባሪነት ዛሬ በአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ ተከናወነ፡፡ ዛሬ ሰኞ ሃምሌ 03 ቀን 2015 ዓ.ም. የሱልጣኔቱ በዓለ ሲመት የተከናወነው በደማቅ ስነስርዓት ነው ተብሏል፡፡
ለ400-500 ዓመታት ገደማ ተቋርጦ የነበረውን ስርዓት ለማስቀጠል የቀድሞ የአፋር ክልል አርጎባ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ ሱልጣን መሃመድ አሽራዬ ዛሬ ሹመቱን መቀበላቸውም ተሰምቷል፡፡ የሹመት ሂደቱ ባለፈው ሳምንት ከስነስርዓቱም አስቀድሞ ከአርጎባ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን) ተቃውሞ አስነስቶ ነበር፡፡ 
“በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡ መላው የአርጎባ ህዝብ ከአራቱም አቅጣጫዎች ተሰባስበው ስርዓቱን በደማቅ ሁኔታ ከውነዋል፡፡ከውጪም ጭምር በርካቶች የተሳተፉበት ስርኣት ነበር፡፡” 
ዛሬ በአፋር ክልል ዞን 03 አርጎባ ልዩ ወረዳ በጋቸኒ ከተማ የአርጎባ ይፋት ሱልጣኔት የሹመት ስነስርዓት መከናወኑን ተከትሎ የብሔረሰቡ የቀጣይ ዓመታት ባህላዊ መሪ ሆነው የተሾሙት ሱልጣን መሃመድ አሽራዬ ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት ነው፡፡ የአርጎባ ብሔረሰብ ከሚኖሩባቸው ኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር እና ሀረሪ ክልሎች እንዲሁም ከውጪ አገር የብሔረሰቡ ተወላጆች በብዛት ታድመውበታል የተባለለት ይህ ባህላዊ የሹመት ስርዓት ደማቅም እንደነበር ተነግሯል፡፡ ከ500 ዓመታት ገደማ በኋላ ተቋርጦ የቆየውን ስርዓት ለማስቀጠል ዛሬ የተሰየሙት ሱልጣን መሐመድ በቀጣይ ስለሚጠብቃቸው ሃላፊነትም ይህን ብለዋል፡፡ “አርጎባ በባህላዊ ስርዓት አባቱ ስር ተሰባስቦ እርሰ በርስም ይሁን ከሌላው ጋር ያለውን ችግሩን ይፈታበታል፡፡ ባህልና ማንነቱንም አጠናክሮ ያስቀጥልበታል፡፡” 
አዲሱ የአርጎባ ሱልጣኔት ሱልጣን መሃመድ አሽራዬ በአፋር ክልል የአርጎባ ልዩ ወረዳን ከማስተዳደር ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ያገለገሉ ተብሎላቸዋል፡፡
በአርጎባ ልማት ማህበር አስተባባሪነት ዛሬ አንዲቀጥል የተደረገው የአርጎባ ጀበርት ኢፋት ሱልጣኔት ሱልጣን ሹመት፤ በዘር ሃረግ የተሳሰረው የሃሺማይት ይፋት ወላስማ ስርወ-መንግስት ከተቋረጠበት ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ በኋላ የመጀመሪያው ነው፡፡ የልማት ማህበሩ አመራር ቦርድ አባልና የዚህ በዓል አስተባባሪ አቶ እስማኤል ቱሃ፤ ስርዓቱን የማስቀጠል አስፈላጊነት ሲያስረዱ፤ “በተለያዩ ክልሎች በተለይም በአፋርና በአማራ ክልሎች በሁለት ልዩ ወረዳዎች ተከልሎና በኦሮሚያ እና ሃረሪ ክልሎችም ተበታትኖ ለሚኖር የአርጎባ ህዝብ ማንነት አሰባሳቢ አባት ለመሰየም ነው” ብለዋል፡፡ “እየጠፋ ነው ለሚባለው የአርጎባ ቋንቋ እና ማንነት አንድ አባት ያስፈልገዋል በሚል ነው ስርዓቱን ማስቀጠል ያስፈለገው፡፡” አቶ እስማኤል ሲቀጥሉ “በተለያየ መልክ የሚፈጠሩትን ግጭቶች አርጎባ ባለው ባህላዊ እሴት እንዲፈታው በመታቀዱ ነው ይህ የሱልጣኔት ሹመት ያስፈለገው” ብለዋል፡፡
የአርጎባ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አብዴን) ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለዛሬ የታቀደውን የሱልጣኔት ሹመት ተቃውሞ ነበር፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ሀሰን መሃመድ ሀሰን በተለያዩ አከባቢዎች ተበታትነው ያሉ የብሔረሰቡ ተወላጆች አሊያም ተወካዮቻቸው ባልተወያዩበት መካሄዱ ተገቢነት የለውም ነበር ያሉት፡፡ በተለያዩ አከባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ሰኔ 27 በአዳማ መክረው ሂደቱን መቃወማቸውንም አንስተው ነበር፡፡
በዚህም “ባሁን ወቅት የሱልጣኔቱን ሹመት ማስቀጠል የሚኖረው ሚና ግልጽ ባለመሆኑ፣ በሹመቱ መካሄድ ላይ መግባባት ብፈጠር እንኳ በታሪክ ያለውን የዑመር ወላስማን ዝርያ በማግኘት ስርዓቱን ማስቀጠል አዳጋች መሆኑ፣ ከዑመር ወላስማ ዝርያ ውጪም ስርዓቱን ማስቀጠል ካስፈለገ አስፈላጊነቱም ላይ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የብሔረሰቡ ተወካዮች ባልተስማሙበት በጥቂት ሰዎች ምርጫ ሹመቱን ማከናወን ተቀባይነት የለውም” ብሎ ነበር ፓርቲው በመግለጫው፡፡ 
የበዓሉ አስተባባሪ አቶ እስማኤል ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ “በሀረሪ የኦሮሚያ እና ሀረሪ ክልል የብሔሩ ተወላጆች ተወካዮችን አወያይተናል፡፡ በአፋር ክልልም በአርጎባ ልዩ ወረዳ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ነው ሁሉንም በእኩል ያገለግላሉ የተባሉ ሰው የተሾሙት፡፡ ከሁሉም አከባቢም ዛሬ በስርዓቱ ተሳትፎን አድርገዋል፡፡”
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW