1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወንጀል ድርጊቶች በሀዋሳ ከተማ መበራከት የደህንነት ካሜራ እንዲተከል አስገደደ

ሰኞ፣ ነሐሴ 22 2015

የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የንግድና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደህንነት ካሜራ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ መመሪያ ይፋ አደረገ። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው መመሪያ በከተማው የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ያስችላል ተብሎ ተምኖበታል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የደህንነት ካሜራ
የወንጀል ድርጊቶች በሀዋሳ ከተማ መበራከት የደህንነት ካሜራ እንዲተከል አስገደደ። ፎቶ ከማኅደር፤ የደህንነት ካሜራምስል Mark Baker/AP Photo/picture alliance

አሳሳቢ የወንጀል ድርጊቶች በሀዋሳ ከተማ

This browser does not support the audio element.

የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የንግድና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደህንነት ካሜራ እንዲገጥሙ የሚያስገድድ መመሪያ ይፋ አደረገ። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው መመሪያ በከተማው የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ያስችላል ተብሎ ተምኖበታል። ዶቼ ቬለ DW መመሪያውን አስመልክቶ አስተያታቸውን የጠየቃቸው ስማቸው አንዳይጠቀስ የጠየቁ ነጋዴዎች በበኩላቸው የደህንነት ካሜራዎችን መጠቀሙ ተገቢ ነው ይላሉ። ነገር ግን ከጊዜው አጭርነትና ከወጪ ዝግጅት አንጻር ከግምት መግባት ነበረበት ባይ ናቸው።

ወንጀልን የመከላከል ጥረት በሀዋሳ

በሀዋሳከተማ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ያስችላል የተባለ የውይይት መድረክ ከከተማዋ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር እየተካሄደ ይገኛል። መድረኩን የመሩት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊዎች በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በንግድና፣ በመኖሪያ ቤቶች እና በግለሰቦች ላይ የሚፈጸሙ የሥርቆት ወንጀሎች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል። በተለይም የተሽከርካሪና የሞተር ብስክሌቶች ሥርቆት በተደጋጋሚ ሲፈጸም እንደሚስተዋል የጠቀሱት የሥራ ሃላፊዎቹ ቢሮው ወንጀሎቹን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። እስካሁን ብዛት ያለቸው የጦር መሣሪያዎች፣ ግምታቸው ከ14 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑና በኮትሮባንድ ሊገቡ የነበሩ አልባሳት ኅብረተሰቡ ባደረገው ትብብር በከተማው ፖሊስ አባላት መያዛቸውን ሃላፊዎቹ አብራርተዋል። በተጨማሪም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የተያዘ 69 ኪሎ ግራም አደዛዥ እፅ አንዲቃጠል የተደረገ ሲሆን ተሠርቀው የነበሩ 57 የሞተር ቢስክሌቶች ተይዘው ለባለንብረቶች መመለሳቸውን አስረድተዋል።

አስገዳጁ የደህንነት ካሜራዎች ተከላ

የወንጀል ድርጊቶች በሀዋሳ ከተማ በመበራከታቸው የከተማ አስተዳደሩ ነጋዴዎች እና ኩባንያዎች የደህንነት ካሜራ እንዲተክሉ መመሪያ እንዲያወጣ አድርጓል። ፎቶ ከማኅደር፤ የደህንነት ካሜራ ምስል Evgeniy Porokhin/ Zoonar/picture alliance

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ በከተማው የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልል የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊዎች አስታውቀዋል። ከእነኝሁ ተግባራት መካከልም በከተማዋ የሚገኙ የንግድና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወንጀልን ለመከላከል የሚያስችሉ የደህንነት ካሜራዎችን እንዲገጥሙ የሚያስገድደው መመሪያ አንዱ መሆኑን የሲዳማ ክልል  የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞጢዎስ ተናግረዋል።

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው መመሪያ በከተማው የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከል ያግዛል ተብሎ ተምኖበታል። በመመሪያው መሠረት የደህንነት ካሜራዎቹ  በሆቴሎች፣ በምሽት ቤቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎችና በባንኮች ላይ ተግባራዊ የሚደረጉ ይሆናል። ያም ሆኖ የካሜራዎቹ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ መመሪያው በአነስተኛ የንግድ ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደማይሆን ነው አቶ አለማየሁ የገለጹት። የንግድ ተቋማቱ አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የአንድ ወር የጊዜ ገደብ እንደተሰጣቸው የጠቀሱት አቶ አለማየሁ « ይህን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ ክትትል ይደረጋል» ብለዋል።

የንግድ ተቋማት ባለቤቶች መመሪያውን እንዴት አዩት?

ዶቼ ቬለ DW በመመሪያው ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸውና ስማችን አይጠቀስ ያሉ ነጋዴዎች በበኩላቸው የደህንነት ካሜራዎችን መጠቀሙ ተገቢ ነው ይላሉ። ፎቶ ከማኅደር፤ የሀዋሳ ከተማ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ዶቼ ቬለ DW በመመሪያው ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸውና ስማችን አይጠቀስ ያሉ ነጋዴዎች በበኩላቸው የደህንነት ካሜራዎችን መጠቀሙ ተገቢ ነው ይላሉ። ከከተማው ሥፋት አንጻር በየአካባቢው ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ «የድህንነት ካሜራዎች በሰዎች ሊታዩ የማይችሉ  የወንጀል ድርጊቶችን ለማወቅ ይረዳል። ነገር ግን ይህን ለማድረግ በቂ ጊዜና የወጪ ዝግጅት ስለሚጠይቅ የተሠጠው የአንድ ወር ጊዜ በጣም አጭር ነው» ብለዋል።

የደህንነት ካሜራዎች ከግለሰብ ነጻነት አንጻር

ዶቼ ቬለ DW መመሪያውን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ብረሃኑ ጋኔቦ «ሀሳቡ መልካም ቢሆንም በአተገባበር ሂደቱ ላይ ከግለሰቦች መብት አንጻር በጥንቃቄ ሊፈጸም ይገባል» ብለዋል። የድህንነት ካሜራዎች ሲተከሉ የራሳቸው አላማና አጠቃቀም  አንዳላቸው የገለጹት አቶ ብረሃኑ በካሜራዎቹ አማካኝነት የሚሰበሰቡ መረጃዎች ወንጀልን ለመከታተል በሕግ ሥልጣን ለተሰጣቸው አካላት እጅ ብቻ ሊገቡ አንደሚገባ ጠቅሰዋል። «በየተቋማቱ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ከግለሰቦች ፍቃድና እውቅና ውጭ አላሥፈላጊ ለሆነ ጉዳይ መዋል የለባቸውም። ይፋ ሊሆኑ በማይገባቸው የግለሰብ መረጃዎችን ከዜጎች መብት አንጻር በጥንቃቄ መያዝ ይኖርባቸዋል» ብለዋል።  

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW