1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባለፈው ሳምንት በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የተካሔደው ተቃውሞ እያወዛገበ ነው።

ሰኞ፣ ጥቅምት 27 2010

"ብዙ ሰዎች እንደታሰሩ፤ የታሰሩትም ሰዎች እንዳልተፈቱ፤ ታስረው ያሉትም ሰዎች ሕፃናት እና እናቶች ሳይቀር መደብደብ እና ማስፈራራት እየደረሰባቸው እንደሆነ ነው የሰማንው" -የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሰላም ኪዳኔ

Eine afrikanische Insel der Architektur
ምስል DW/Y.Tegenewerk

ሞተዋል የተባሉ ሰዎች ቁጥር በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም

This browser does not support the audio element.

ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የተካሔደውን ተቃውሞ ያሳያል ተብሎ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጨ ቪዲዮ ላይ ከባድ የተኩስ ድምፅ ይሰማል።  መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ባደረጉ ተቃዋሚዎች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ በስፋት የተሰራጨው ምሥል በተንቀሳቃሽ ስልክ የተቀረጸ ሲሆን ጥራቱም ደብዛዛ ነው። በቪዲዮ ምሥሉ የተኩስ ድምፅ ከተሰማ በኋላ ከሽሯማ ፎቅ አጠገብ የተሰበሰቡ ሰዎች በደመነፍስ ጩኸት እያሰሙ ሲበታተኑ ያሳያል።

ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩት እና መቀመጫቸውን በብሪታኒያ ያደረጉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሰላም ኪዳኔ እንደሚሉት ተቃውሞው የተነሳው ከመሐል አስመራ እምብዛም በማይርቅ ቦታ ነበር። አል ዲያ የተባለው የእስልምና ትምህርት ቤት ከሚገኝበት አኽሪያ የተነሳው የተቃውሞ ሰልፍ "ወደ መሐል ከተማ፤ ከመሐል ከተማ ወደ ትምህርት ሚኒሥቴር፤ ከትምህርት ሚኒሥቴር ወደ ፕሬዝዳንቱ ፅ/ቤት ለመሄድ ነበር። ግን በተለያየ ምክንያት ያንን ለማድረግ አልተቻለም። ከዛ ወደ ማዕከላዊ መስጊድ በመሔድ አላማቸውን ገልጸው ጸሎቱን ተካፍለው ወደ ሰፈራቸው ወደ አኽሪያ ነው የተመለሱት" ሲሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ያስረዳሉ። እንደ ሰላም ኪዳኔ አባባል ወደ አኽሪያ ሲመለሱ ከመንግስት ጸጥታ ኃይሎች "ትልቅ" ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። በማኅበራዊ ድረ-ገፅ የተሰራጨው ቪዲዮ ላይ የተሰማው የተኩስ ድምፅ የተከሰተው አኽሪያ በተባለው ቦታ እንደሆነ ሰላም ኪዳኔ ጨምረው ገልጠዋል። 
የጀርመን-ኤርትራ ማኅበረሰብ ምክትል ሊቀ-መንበር ኡልሪሽ ኮፔል የአስመራው ተቃውሞ ሲጀመር እምባይሶራ ሆቴል ነበሩ። ኡልሪሽ ኮፔል የነበሩበት ቦታ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች የተሰራጨው ቪዲዮ ከተቀረጸበት እና ተኩስ ተከፍቶበታል ከተባለው አውራ ጎዳና እምብዛም አይርቅም። 

ምስል DW/Y.Tegenewerk

"ከተቃዋሚዎች መካከል የተወሰኑት መታሰራቸውን ማረጋግጥ እችላለሁ።  ነገር ግን በሰዎች ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። የተሰራጨውን ቪዲዮ ፈትሸናል። በሆቴል የነበሩ ሰዎች ይኸን ቪዲዮ እንዲያረጋግጡ ለማድረግ ሁለት ቀናት ወስዶብናል። በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ ያለው ድምፅ ትክክለኛው አይደለም። ብዙ የተኩስ ድምፅ እና የትልልቅ የጦር መሳሪያ ድምፆች ገብተውበታል። የአውቶማቲክ የጦር መሳሪያ ድምፅ ገብቶበታል። በትክክል የተኩስ ድምፅ ነበር። በርካታ ተኩስ ነበር። ነገር ግን በአውቶማቲክ የጦር መሳሪያ እና በትልቅ የጦር መሳሪያ አልነበረም።"

የአስመራው ተቃውሞ የተቀሰቀሰው የአል ዲያ የእስልምና ትምህርት ቤት ኃላፊ የሆኑት ሐጂ ሙሳ መሐመድ ኑር በመታሰራቸው ነበር። ኡልሪሽ ኮፔል እንደሚሉት ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ድንጋይ በመወርወራቸው ፖሊስ ወደ ሰማይ ጥይት መተኮሱን ከአይን እማኝ አረጋግጠዋል። 

"ወደ ጀርመን ለመምጣት አውሮፕላን ስሳፈር በተቃውሞው ቦታ ምን እንደተፈጠረ የተመለከተች ወጣት አግኝቼ ነበር። እሷ እንደደነገረችኝ አላሁ አክበር ሲሉ የነበሩ ወጣት እና ጎልማሳ ተቃዋሚዎች በፖሊስ ላይ ድንጋይ ወርውረዋል። በዚህ ምክንያት ፖሊስ ለማስጠንቀቅ ወደ ሰማይ ተኩሷል። ከዚያ ሁሉም ነገር ሰላም ሆነ፤ ሥርዓትም ያዘ።"

ምስል DW

የኤርትራ መንግሥት የኢንፎርሜሽን ሚኒሥቴር በድረ-ገፁ ባሰፈረው ሐተታ በአስመራ ጎዳና የተፈጠረው ክስተት እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አጋነውታል ብሏል። መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገው የቀይ ባህር አፋር ዴሞክራሲያዊ ድርጅት በተቃውሞው 28 ሰዎች መገደላቸውን ቢገልጥም እስካሁን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ሰላም ኪዳኔ እንደሚሉት ግን የአስመራው ኩነት በኤርትራም ይሁን ከኤርትራ ውጪ ያሉ ዜጎችን አስቆጥቷል።

"ብዙ ሰዎች እንደታሰሩ፤ የታሰሩትም ሰዎች እንዳልተፈቱ፤ ታስረው ያሉትም ሰዎች ሕፃናት እና እናቶች ሳይቀር የመደብደብ እና የማስፈራራት እየደረሰባቸው እንደሆነ ነው የሰማንው። ከሕዝቡ ወገን ደግሞ ተቃውሞውን አኽሪያ ላይ ለተሰለፉት ሰዎች ይሁን ለታሰሩት ሰዎች ድጋፉን እንደሚቀጥል ያ ድግፍ ደግሞ እንደማይቋረጥ ነው ደጋግመው የሚገልጡልን።" የሚሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ በውጪ አገሮች የሚገኙ ተቃዋሚዎች በተለያዩ ከተሞች ሰልፎች እያደረጉ ነው ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

 


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW