1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአሶሳ ሆስፒታል የመድኃኒትና አቅርቦት ችግር

ረቡዕ፣ ጥር 15 2016

የአሶሳ ሆስፒታል በግብአት እጥረት መቸገሩን ዐስታወቀ፡፡ ክልሉን የሚያገናኙ ሁለት መንገዶች ላይ በሚከሰቱት የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የመድኃኒትና የተለያዩ ዕቃዎች በመኪና ለማስገባት እንዳልተቻለ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሶፊያ አወድ ተናግረዋል ።

የአሶሳ ከተማ
የአሶሳ ከተማ ። ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Negassa Desalegn/DW

የፀጥታ ችግሮች የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ሳንካ ፈጥረዋል

This browser does not support the audio element.

የአሶሳ ሆስፒታል በግብአት እጥረት መቸገሩን ዐስታወቀ፡፡ ክልሉን የሚያገናኙ ሁለት መንገዶች ላይ በሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት የመድኃኒትና የተለያዩ ዕቃዎች በመኪና ለማስገባት እንዳልተቻለ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሶፊያ አወድ ተናግረዋል ። በአሁኑ ወቅት መድኃኒት  የሚጓጓዘው በአየር እንደሆነ ገልጸው ተጠቃሚው ብዙ ከመሆኑም የተነሳ የመድኃኒት እጥረት እንዳለ ጠቁሟል ። ከሆስፒታሉ አቅም በላይ የሆኑ የህክምና ትዕዛዞችን ወደ ሌላ ሐኪም ቤት ለመላክ እና በአንቡላንስ ለማድረስ በመንገድ ችግር ሳቢያ እንደማይቻልም ገልጸዋል ። 

በፀጥታ ችግር ምክንያት መድኃኒት በመኪና ማጓጓዝ አልተቻለም

በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚስተዋለው የፀጥታ አለመረጋጋት በጤና ተቋማት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሞያዎችና ተቋማት ሲገልጹ ቆይቷል፡፡ በእዚሁ አካባቢው በሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መድኃኒትና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ማጓጓዝና ሰዎችን ለተሻለ ህክምና ወደ ሌላ አካባቢ መላክ ፈታኝን መሆኑን የአሶሳ ሆስፒታል ገልጿል፡፡

የአሶሳ ጠቅላላ ሆስፒታል በአሶሳ ዞን እና አጎራባች የሆኑት የምዕራብ ወለጋ ዞን ወረዳ ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሶፊያ አወድ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከፌደራል ተቋማት ጋር በመነጋገር መድኃኒት በአየር ትራንስፖርት እና አልፎ አልፎ በእጅባ እየመጣ እንደሚገኝ ጠቁመው ከዋጋ አንጻርም ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉን አብራርተዋል፡፡ የታካሚው ቁጥር መጨመርና ፍልሰተኞች መብዛት ጋር ተዳምሮ ለሆስፒታሉ የሚላኩ መድኃኒቶች እየተዳረሰ አይደለም ብሏል፡፡

በክልሉ ስድስት ሆስፒታሎች የአቅርቦት ችግር ስለመኖሩ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ጽ/ቤት በበኩሉ አሶሳ ሆስፒታልን ጨምሮ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ሆስፒታሎች ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ጠቁሟል፡፡ የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ዓለም ደበሎ በአራት የመጀመሪያ እና 2 ጠቅላላ ሆስፒታሎች የአቅርቦት ችግር መኖሩን አመልክተዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፈ ሲባል በአየር ትራንስፖርት ማጓጓዝ ቢቻልም በቂ አለመሆኑንና ሌሎች የህክምና ቁሳቀሶችን  ማስመጣት እንዳልተቻለ ጠቁሟል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለም ደበሎምስል፦ Negassa Desalegn/DW

በክልሉ የፀጥታ ጉዳይ  ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ከፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት  ያደረኩት ጥረት አልተሳም፡፡ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ሰኔ 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መረጃ በምዕራብ ወለጋ ብቻ 42 የሚደርሱ የጤና ተቋማት በደረሰባቸው ጉዳት እና ስርቆት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንደማይሰጡ አመልክተዋል፡፡ በዚሁ አካባቢ በርካታ ሰዎች ለወባ በሽታ እና ልዩ ልዩ በሽታዎች እየተዳረጉ እንደሚገኙም ሲዘገብ ቆይቷል፡፡

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW