የአባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀምን አስመልክቶ የባለሙያዎች ውይይት
ቅዳሜ፣ ግንቦት 30 2017
የአባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀምን አስመልክቶ የባለሙያዎች ውይይት
የአባይ ውኃ ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚቀመጡ የመፍትሔ ዐሳቦች፣ የወንዙን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው፣የውኃ ጉዳይ ባለሙያዎች አመለከቱ።
በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች መማክርት፣ ባካሄደው አውደ ጥናት የተሳተፉ የዘርፉ አጥኚዎችና ባለሙያዎች፣ የአባይ ወንዝ ውኃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ክፍፍል፣ እንዲሁም ወንዙን ለመጠቀም ባሉ አማራጮች ዙሪያ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ውኃ ጉዳዮች መማክርት ፕሬዚዳንት አቶ መርስዔ እጅጉ እና የመማክርቱ የቦርድ አባል መቅደላዊት መሳይ ለዶቼ ቬለ እንደገለጹት፣ በአባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ተጨማሪ ቀጣይ ጥናት ያስፈልጋል የሚል መግባባት ላይም ተደርሷል።
በውኃ ጉዳዮች ላይ የሚያማክሩ፣ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን ያሰባሰበው የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች መማክርት፣ የተለያዩ ጥናቶችን እንደሚያካሂድ የመማክርቱ ፕሬዝዳንት የሆኑት የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግስት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር አቶ መርስዔ እጅጉ ገልጸውልናል።
"የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች መማክርት፣የምርምር ተቋም ነው።እና የተለያዩ ባለሙያዎችን ኢኮኖሚስቶችን፣አንትሮፖሎጂስቶችን፣አርክቴክቶችን ባለሙያዎችን አሰባስቦ፣የውኃዎች አጠቃቀም አያያዝ ላይ የሚመክር ነው።የፖሊሲ ዐሳብ የሚያቀርብ መረጃን የሚያሰባስብ እንደመሆኑ መጠን የአሁኑን ዛሬ ያጋጠመንን ችግር በቻ ሳይሆን ለወደፊት ከአምስት ዓመት አዐሥር ዓመት በኃላ ምን ለያጋጥመን ይችላል በሚል አንዳንድ ጉዳዮችን እያነሳ ጥናት የሚያደርግ ነው።"
የአውደ ጥናቱ አጀንዳዎች
የአሁኑ ውይይታቸው አበይት አጀንዳዎች ስለነበሩ ጉዳዮችም፣አቶ መርስዔ የሚከተለውን ተናግረዋል።"የውኃ አጠቃቀም ድልድል ምን ማለት ነው? ለአባይ ተፋሰስ ጠቀሜታ አለው ወይ?የድልድል መመዘኛዎቹ ምንድናቸው?የሌሎች ሃገርችስ ልምድ እንዴት ነው?በሚል ያለንን አጠቃላይ ግንዛቤ በእኛም ደረጃ ከፍ ለማድረግና ለወደፊት ምርምር መሠረት ለመጣል ነው።"
የመማክርቱ አባልና የአውደ ጥናቱ አስተናባሪ መቅደላዊት መሳይ በበኩላቸው፣የአባይ ውሃን ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀምባሉ አማራጮች፣ እንዲሁም የወንዙን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ መፍትሄዎች አስፈላጊነትን አስመልክቶ ስለተነሱ የውይይት ዐሳቦች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተውናል።
"ባለሙያዎቹ ያነሱት አንድ ትልቅ ነጥብ፣የአባይ ተፋሰስ በጣም ልዩ የሆኑ ነገሮች ስላሉት፣ የራሳችንን ነባራዊ ሁኔታ፣ውኃውን ለመጠቀም የሚመጣው መፍትሔ፣የዓባይን ሁኔታ ያገናዘበ መሆን አለበት የሚለውን ነገር በደንብ አስምረውበት ነው ያለፉት።"
በውኃ አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች
በአባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮችን አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የመማክርቱ አባል ሲመለሱ፣ እንደሚከተለው አስረድተዋል።"የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችወይም በተለይ የአባይ ተፋሰስ አጠቃቀም ላይ ከሚነሱ የመጀመሪያው ችግር ይኸው ነው። እንደሚታወቀው እንደ ጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር፣የ1959 ስምምነት በግብጽ እና በሱዳን መኻከል አካፍሎ ቁጭ በብሏል።ይኼ ማለት፣ሌሎች የተፋሰሱ ዘጠኝ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ 86 በመቶ በላይ ውኃውን በብናመነጭም፣በ1959 ስምምነት ምክንያት ምንም ዓይነት የልማት ኢንቨስትመንት የአባይ ተፋሰስ ላይ ስንጀምር ችግር ይገጥመናል።ይህንን በኅዳሴ ግድቡም ዐይተነዋል፤ ከኅዳሴ ግድቡ በፊትም የአባይን ተፋሰስ ለማልማት በነበሩት ተሞክሮዎቻችን ዐይተናል።"በአጠቃላይም፣የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች፣በአባይ ውኃ አጠቃቀም ላይ ተጨማሪ ቀጣይ ጥናት ያስፈልጋል የሚል መግባባት ላይ መድረሳቸውንም፣ ከመማክርቱ ፕሬዝደንትና የቦርድ አባል ለመረዳት ችለናል።
ታሪኩ ሀይሉ
ሽዋዬ ለገሠ
ፀሀይ ጫኔ