1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአባይ ግድብ፣ የጠ/ሚ ማብራሪያ እና የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት

ዓርብ፣ የካቲት 18 2014

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚውን የኅብረተሰብ ክፍል የሚያወያዩ ኹነቶች ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ይመስላል። በዚህ ሳምንት በተለይ የኅዳሴ ግድብ በአንድ ተርባይን የኤሌክትሪክ ማመንጨት ተግባር መጀመር፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በምክር ቤት የሰጡት ማብራሪያ እንዲሁም የሩሲያ እና ዩክሬን ጉዳይ ላይ ከተሰነዘሩ አስተያዮች የተወሰኑትን መራርጠናል።

ETHIOPIA-EGYPT-SUDAN-DAM-ELECTRICITY
ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.

 

ከአዎንታዊ ዜናዎች ተርታ የአባይ ግድብ አንዱ ተርባይን ኤሌክትሪክ የማመንጨት ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ አስተያየት ከሰጡ መካከል «አባይ ማደሪያ አገኘ አሁን ግንድ ይዞ አይዞርም ግድብ ሆኖ ያለማል።» ያሉት ባራሳ ዋሬ ናቸው በትዊተር። የፌስቤክ ተጠቃሚ እንደሆኑት እንደ ሁንዴ ሲቡ፤ «እንኳን ደስ አለን ወገኖች!» የሚለው የበርካቶች መልእክት ሲሆን ፍሪትዝ ሱራ በትዊተር፤ «የሕዳሴው ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያመነጭ ስናይ፤ ሰናይ እንኳን ደስ አለን። ነገ የኢ/ር ስመኘው ቀን ይሁን ያልሞተ ሥራህ ነገ ብርሀን ይሆናል።» በማለት በግድቡ ላይ የማይዘነጋ አሻራቸውን ያሳረፉትን ታላቅ ሰው አስታውሰዋል። ሳሚ ቢን ጀማልም እንዲሁ በትዊተር፤ «ተሸጧል የተባለው ግድብ ለኢትዮጵያ ብርሃን አበራ። አባይ ለኢትዮጵያውያን እጁን ሰጠ፤ እንኳን ደስ አላችሁ በድጋሚ፤ በድጋሚ አሁንም በድጋሚ ኢትዮጵያ በጉባ ተራሮች ላይ አሸብርቃ ደምቃለች! የድል ድምጽ ከታላቁ ሸለቆ እየተሰማ ነው።» ብለዋል። ሶሎሞን አሰፋ ደግሞ በሆነው የረኩ አይመስሉም፤ «ገና አላለቀም፤ ያውም ሁለት ተርባይን ተብለን አንዱ ነው ሥራ የጀመረው። 10 ተርባይን አካባቢ አለው ሲያልቅ።» ይላሉ ደስታውን በልኩ በሚል መንፈስ። የፌስቡክ ተጠቃሚ የሆኑት ሄሮ ኩስቶ ደግሞ ጭራሽ የተባለውን ዜና ያመኑም አይመስሉም። «ውሸት» ነው ያሉት። ኤፍ ሶሳይቲ ደግሞ በትዊተር፤ «አባይ ግድብ በተመረቀ በመጀመሪያው ቀን ገርጂ ላይ መብራት ጠፍቷል። እሪ በሉ!» በማለት ኢትዮጵያ ውስጥ መደበኛ ወደመሆን የተሸጋገረውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስተጓጎል አስታውሰዋል። ተመስገን ጓዴ ደግሞ ሌላ ነገር ነው የታያቸው፤ «ደሞ ተጀመረ? የኢትዮጵያ ህዝብ ትዕግስት አጥቷል የደስታ ሰልፍ እያሉ ደግሞ ናላችንን ሊያዞሩት ነው።» ብለዋል።


ምስል፦ Solomon Muche/DW

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማክሰኞ ዕለት ከምክር ቤት አባላት በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ እና ምላሽ በርካቶች በማኅበራዊ መገናኛው ሲወያዩበት ተስተውሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህወሃት ጋር ድርድር ተጀምሯል ይባላል በሚል ለቀረበላቸው የሰጡትን ምላሽ ተንተርሶ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል፤ አለማየሁ አሸናፊ በፌስቡክ ምላሻቸው፣ «አልሸሹም ዞር አሉ አይነት ንግግር» ይላሉ፤ ምህረተ አብ ገብረሥላሴም ሃሳባቸውን የሚጋሩ ይመስላል፤ «በተዘዋዋሪ አለ በቀጥታ ድርድር አለተጀመረም ማለቱ ነው ።» በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ በራሳቸው መንገድ ያብራራሉ፤ ቁምላቸው ሙላቴም ግራ የተጋቡ ይመስላል፤ «ታዲያ ምን አየተካሄደ ነው? የዘፈን ዳርዳርታው እስክስታ ነው አሉ፤ ወንጀለኞችን ለመያዝ ስንት መስዋዕትነት ተከፍሎ እንደዋዛ ሲለቀቁ ምንን ያመላክታል? እንግዲህ በሕይወት ከቆየን ሁሉንም እናያለን፤ ብቻ ከፈጣሪ እንጅ ከሰው ብዙም አንጠብቅም።» ማስተዋል በለጠ ደግሞ፤ «ድሮስ ጉዳይ ካለቀ በኋላ ነው እንጂ ዛሬ ምን ሊል ይችላል!!! የነዛ መግለጫ እኮ ቢጀምሩም የምራቸውን አለመሆኑንና ህዝብ ጉዳዩ ገምግሞ ከመንግሥትን እንዲቃወም ነው።» ነው የሚሉት።

ምስል፦ Solomon Muche/DW

 አልይ አማን ደግሞ፤ «ፈደራል መንግሥት እንዴት ከክልል ጋር ይደረድራል?? ከተደረደሩ በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዲሽታ ጊናን ይቅርታ መጠየቅ አለበት፤ ምክንያቱም ያኔ ይቅርታ ሲጠይቅ የጮኸው እና ከመድረክ ውረድ ያለው ህዝብ ዛሬ ምን ሆኖ ይሆን? ሰዉየዉ ያኔ አዉቋል ማለት ነው፤ ለኛ ግን ዉርደት ነዉ።» ይላሉ። የአብርሃ ወአጽበሃ አስተያየት ደግሞ ይለያል፤ « የኢትዮጵያ ወቅታዊና አደገኛው ችግር ቂመኛነትና ጥላቻ ነው። ይህንን አስተሳሰብ ከውስጣችን እስካላወጣን ድረስ እግዚአብሔርም አይታረቀንም፣ ስቃይና መከራችንም በዝቶ ገዝግዞ ይጥለናል፡፡» ነው የሚሉት። ወደሰላም ለመሻገር ድርድር አይቀርም የሚሉት ደግሞ ጋንቲ ፈይሳ ናቸው በፌስቡክ፤«እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል ለሰላም ሲባል በቅርቡ ወደ ድርድር ይገባል፤ በጦርነት ተጀምሮ በጦርነት የተቋጨ እስካሁን የትም አልታየም።» በማክሰኞው የምክር ቤት ማብራሪያቸው ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ እያለች ኤኮኖሚዋ አድጓል ሲሉ የተናገሩትን በተመለከተ ደግሞ ሃሚድ አወል፤ «ኢኮኖሚው አድጎ ሊሆን ይችላል እኛ አናውቅም ነገር ግን የፍጆታ ዕቃዎች በየቀኑ ዋጋ እየቀጠሉ ነው አብዛኛው ሕዝቡም ኑሮ በጣም እጅግ በጣም ከብዶታል።» ነው ያሉት በፉስቡክ፤  ኢሳ ኢየሱስ እሸቱ የተባሉ ሌላው የፌስቡክ ተጠቃሚም እንዲሁ፤ «ለባለሥልጣናት ዕድገት አሳይቷል ለህዝብ ግን ዕድገት ቀርቶ ባለበት መኖሩ ያጠራጥራል።ኢኮኖሚው ማደግ አለማደጉን ለማረጋገጥ ከኪሰዎ ገንዘብ አዉጥተዉ በልተው ይሞክሩ ።» ይላሉ። ደመቀ የማታወርቅ በማሳያ ነው ሃሳባቸውን ያጋሩት፤ «የኢትዮጵያ ነገሥታታ ለምንድነዉ ሁል ግዜ ኢኮኖሚያቸዉን ለማደባበስ የሚሮጡት? ዘይት 1ሊትር = 142ብር ፣ ጨዉ 1ኪሎ =20 ብር ፣ ሳሙና የ8ብሩ =20ብር ፣ የ15ብሩ = 30ብር ሆኖ ሳለ ፤ ገቢ የለ፤ አብሶ ለመንግሥት ሠራተኛ ፤ መንግሥት ከላይ ቁጭ ብሎ ኢኮኖሚው አድጎጓል ይላል አያሳዝንም? እንዳዉም ያስለቅሳል::» ብለዋል። የፌስቡክ ተጠቃሚው አስፋው ዓለሙ ይጠይቃሉ፤ «ጥቂቱ ሰው ሳይሆን ብዙሃኑ ፆሙን እያደረ እንዴት ያለ እድገት ነው?» ማሙሽ ባጀ ደግሞ፤ «የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የኔ ፀጉር መቼ ነው ማደግ እሚያቆሙት? ዓለም ላይ ስንት ኢትዮጵያ ነው ያለው? የኛ ኢትዮጵያ እንኳን ኢኮኖሚዋ ህዝቧንም በጦርነትና በተንኮል እየቀነሱት ነው ወይ ማደግ።» ብለዋል።

ምስል፦ Konstantin Mihalchevskiy/Sputnik/picture alliance/dpa

በምሥራቅ አውሮጳ የዓለምን ትኩረት የሳበው የዩክሬን ሩሲያ ፍጥጫ ሞስኮ የጦር ኃይሏን ወደ ዩክሬን በማስገባት ወታደራዊ ርምጃ መጀመሯ ሌላው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል። አብዛኞቹ የኢትዮጵያውያን አስተያየት የምዕራቡ ዓለም ተጽዕኖን በመቃወም ላይ ያተኮረ ነው። በለጠ በላይ በፌስቡክ ፤« አርበተበታቸው» በማለት ለፕሬዝደንት ብላድሚር ፑቲን ድጋፋቸውን ሲገልጹ ዋኪራ ዲና በበኩላቸው፤ « ራሽያ ምንም አላጠፋች ዩክሬን መገንጠሏ ሳያንስ በእናት ሀገሯ ላይ ለምትሰራው ሴራ ፑቲን መድሀኒት ነው።» ባይ ናቸው። አበባው መኮንን ደግሞ እንዲህ ነው የሚሉት፤ «አሜሪካ እኩያዋን አግኝታለች ሀያልነኝ ብሎ መጎረር አይደልም መበርታት ነው።» አያ ልጅ አቡ በበኩላቸው የሩሲያን ወታደራዊ አቅም ያጎላሉ፤ « የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል አይነት ገጠማት ዩክሬንን፤ አሜሪካን ተማምና አሜሪካ ራዳር ተክላ ስትወጣጠር በ20 ደቂቃ ወደ አመድነት ተቀይሯል አሜሪካ ሰራሹ ራዳር።» በማለት። ሰናይ ምህረተአብ ደግሞ፤ «ኢራቕና፡ ሊብያ፡ በአውሮፓ አሜሪካ ሲወረሩ UN የት ነበር አሁን ማንገራገር ምን ዋጋ አለው አውሮፓ ችግር ውስጥ መግባቱ አይቀርም አፍርቃ እና እስያን ለችግር አጋልጦ ሰላም የለም።» ነው የሚሉት። አሚን አወል ሁሴንም እንዲሁ፤ «የአውሮፓ ሕብረት አሜሪካን ትታደገኛለች በማለት ሩስያ ላይ የአሜሪካን ፍላጎት ለመሙላት የሚያደርገው ፍፁም ሞኝነት ነው። ሩስያ እኮ የኒውክልየር ቦምብ ባለቤት ናት ከተነሳች አሜሪካን ጨምሮ ጠቅላላ አውሮፓን ሕይወት አልባ ማድረግ የሚያስችላት በቂ አቅም አላት።» ይላሉ። አሚር መሀመድ በበኩላቸው በፌስቡክ፤ «የአለም ህዝብ በምዕራባውያን ሴራ ፣ ተንኮል ፣ ዝርፊያ ፣ ግድያ እና ማጭበርበር ስልችችችችትትትት ብሏል። ሚስኪኗ ዩክሬን ግን አውድሟ መሆኗ ያሳዝናል። አላህ ንፁሀን ወገኖቻችንን ይጠብቃቸው።» ብለዋል። አህመድ መሀመድ ደግሞ፤ «ከዩክሬክ ጎን እቆማለሁ!» ሲሉ፤ አሌክስ ተስፈኛውም እንዲሁ« ፍትህ ለዩክሬን» ብለዋል። ናቢኦት ግርማ ደግሞ፤ « ምናልባት የምድራችንን ታሪክ ፈጣሪ ለመቀየር ቢሆን ማን ያዉቀዋል ?» ነው የሚሉት። ዳዊት ወርቁ ችግሩ ለዓለም እንዳይተርፍ ሰግተዋል፤ «እጅግ በጣም ከባድ ጊዜ ሊሆንብን ነው ዓለም አስከፊውን ጦርነት ከጀመረች መተላለቅና መጠፋፋት ብቻ ይሆናል ከዚህ በኋላ ሰው የሚኖር አይመስለኝም ምክንያቱም ጦርነቱ የሁሉም ነውና።» ሲሉ ኬሪ የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ መልእክታቸው ጸሎት አይነት ነው፤ «እንደ ሀገር ሳያልፍልንማ ሦስተኛው ጦርነት ባልተጀመረ።» እኛም በዚሁ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት አበቃለን።

ምስል፦ Alexey Nikolsky/AFP

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW