1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ታዬ ደንደዓ የፍርድ ቤት ዉሎ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ኅዳር 9 2017

በፍትህ ሚኒስቴር ተከሰው እስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ በቀጠሮያቸው መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀረቡ። ችሎቱ አቶ ታዬ “ከህግ አግባብ ውጪ ታጥቀዋል” በሚል ስለቀረበባቸው ክስ፤ ዛሬ የቀረቡት ሁለቱ መከላከያ ምስክሮች ቃለመሃላ ፈጽመው ምስክረነታቸውን ሰጥተዋል።፡

አቶ ታዬ ደንደዓ
አቶ ታዬ ደንደዓምስል Million Haileselasi/DW

የአቶ ታዬ ደንደዓ የፍርድ ቤት ዉሎ

በፍትህ ሚኒስቴር ተከሰው እስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬ በቀጠሮያቸው መሰረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀረቡ። ችሎቱ የሁለት መከላከያ ምስክሮችን ቃልም አድምጧል፡፡

አቶ ታዬ ከተከሰሱባቸው ሶስት ክሶች ሁለቱ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጎላቸው፤ “የጦር መሳሪያን ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ይዘው ተገኝተዋል” በሚል የቀረበባቸውን ሶስተኛ የክስ ጭብጥእንዲከላከሉ በተሰጠው ብይን መሰረት ጉዳዩን የሚያውቁ ብለው ከጠሩዋቸው 5 ተከላካይ ምስክሮች መካከል ዛሬ ሁለቱ ቀርበው የምስክር ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በዚሁ መሰረት ዛሬ በፍርድ ቤት ተገኝተው ቃላቸውን ከሰጡ መካከል አቶ ታዬ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ስያገለግሉ አለቃቸው የነበሩ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እና በፌዴራል ፖሊስ የአጠቃላይ ወንጀል መከላከል መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፈንታ ናቸው፡፡ ችሎቱም የሁለቱ ተከላካይ ምስክሮች ቃል ከሰማ በኋላ የቀሪ ምስክሮች ቃል ለመስማት ለህዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡ የአቶ ታዬ ደንደዓ ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ አለማየሁ ይህንኑን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

ተከሳሽ አቶ ታዬ ምስክሮቹ የምስክርነት ቃላቸውን ከመስጠታቸው አስቀድመው ችሎቱን ጠይቀው በሰጡት ሃሳብ “የታሰርኩበት ምክንያት የከረዩ አባገዳዎች ግድያ በሶስት የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት መፈጸሙን በመግለጽ በመቃወሜ ነው” ብለዋል፡፡

በስልጣን ላይ እያሉም ሶስቴ የግድያ ሙከራ እንደተፈጸመባቸው የገለጹት የቀድሞ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ፤ በተለይም ጠባቂዎቻቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ‘የደህንነት ስጋት’ እንዳለባቸው ለምክትል ኮሚሽነር መላኩ ፋንታ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሳሪያ ለመታጠቅ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ደብዳቤ እንዲጽፉ እንደተነገራቸው አስረድተዋል፡፡

ከዚያም የሰላም ሚኒስትር የሆኑት አለቃቸው አቶ ብናልፍ አንዱዓለምን አማክረዉ፤  ደብዳቤ መጻፍ ሳያስፈልግ እንዲሁ በቃል ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ተስማምተው አንድ ክላሽ ከሁለት ካዝና ጥይት ጋር በ2015 ዓ.ም. መታጠቃቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ታዬ “ከህግ አግባብ ውጪ ታጥቀዋል” በሚል ስለቀረበባቸው ክስ ይህን ካሉ በኋላ፤ ነዉ ዛሬ የቀረቡት ሁለቱ መከላከያ ምስክሮች ቃለመሃላ ፈጽመው ምስክረነታቸውን የሰጡት፡፡

ችሎቱም የሁለቱ ተከላካይ ምስክሮች ቃል ከሰማ በኋላ የቀሪ ምስክሮች ቃል ለመስማት ለህዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዟል፡፡  

አቶ ታዬ ደንደዓ ጉዳዩን ያውቁልኛል ብለው አምስት ምስክሮችን ሲጠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህምድን እና የአዲስ አበባ ከንቲባ የወ/ሮ አዳነች አቤቤን ስም መጠቀሳቸዉን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የቀድሞ ባለስልጣን፣ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን እና የኦሮሚያ ክልል መንግስት ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) አባል አቶ ታዬ፤ ከዚህ በፊት በሰጡት የእምነት ክደት የጦር መሳሪያውን መያዛቸውን ሳይክዱ ክሱ የቀረበበትን አኳሃን ግን መሞገታቸው አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW