የአቶ ደመቀ መኮንን ከብልጽግና ፓርቲ መሸኘት
ዓርብ፣ ጥር 17 2016
የገዢው ፓርቲ ብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ የፓርቲውን ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ደመቀ መኮንንን በክብር መሸኘቱን አስታወቋል።አቶ ደመቀ መኮንንን በመተካት የብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ አባል ሆነው የቆዩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ፕሬዝዳን ሆነው ተመርጠዋል ትብሏል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከመንግሥት ኃላፊነታቸው ስለመነሳት አለመነሳታቸው በግልጽ የተባላ ነገር የለም።
ይሁንና አቶ ደመቀ መኮንን ከመንግሥታዊ ኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን የሚገልፁ መረጃዎች ከትናንት ጀምሮ ጉዳዩን ከሚያውቁ ሰዎች ተሰምቷል።በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥልጣን ደረጃ የሀገሪቱ ሁለተኛ ሰው በመሆን ለ11 ዓመታት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን በገዢው ብልጽግና ፓርቲም ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩበት ስልጣን ዛሬ በፓርቲው መሸኘታቸው ተገልጿል።
አቶ ደመቀ ምኮንን በመንግሥት መዋቅር ካላቸው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው ስለመነሳት አለመነሳታቸውም ይሁን ስለመልቀቃቸው በግልጽ የታወቀ ነገር የለም። የአቶ ደመቀ መኮንን ፖለቲካዊ ስብእናየአቶ ደመቀ መኮንን የቀድሞው ብአዴን ከዚያም የአዴፓ ሊቀመንበር ሆነውም አገልግለዋል። በአማራ ክልል ልዩ ልዩ ከፍተኛ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይም ያገለገሉ ሲሆን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነትም መርተዋል።
አቶ ደመቀ መኮንን የሀገሪቱ የመጨረሻው የሥልጣን አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሁም በትምህርት ሚኒስትርነትም ተሾመው ሠርተዋል።በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ውስጥ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው የኢሶዴፓ ፓርቲ ፀሐፊ ዶክተር ራሔል ባፌን የገዢ ፓርቲ መሰል ውሳኔን እና የሚከተሉ ሁነቶችን ጠይቀናቸዋል።
የፓርቲው ውሳኔ "በፓርቲ ውስጥ የሚፈይደው ነገር ሊኖር ይችላል። ለኢትዮጵያ ግን የሚፈይደው ነገር አይኖርም" ብለዋል። የምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን መግለጫ
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ከረቡእ ጥር 13 እስከ ዛሬ ጥር 17 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረጉት መደበኛ ስብሰባ መጠናቀቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ "በሰላማዊ የፖለቲካ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን ለሚያቀርቡ አካላት ሰላማዊ መንገዶች እስከሚቻለው ድረስ እንዲመቻቹ" ጥሪ ያቀረበው ብልጽግና ፓርቲ "ዓላማቸው በነፍጥ ፍላጎታቸውን ማስፈጸም በሆኑ" ባላቸው አካላት ላይ "ተገቢው ሕግን የማስከበር ሥራ በተጠናከረ መንገድ እንዲካሄድ" ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።
ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ