የአንቶኒ ብሊንከን የአፍሪቃ ጉዞ አንድምታው
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 7 2014
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አንቶኒ ብሊንከን ሰሞኑን ሦስት የአፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝተዋል። የጉብኝታቸው ዋነኛ ዓላማ በሩዋንዳ እና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሎም በአካባቢው ሃገራት የሰፈረው ውጥረት እንደሆነ ቢናገሩም ተንታኞች ለሩስያ አጸፌታ ነው ባይ ናቸው።
የዩናይትድስ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በሦስት የአፍሪቃ ሃገራት ያደረጉትን ጉዞ ባሳለፍነው ማክሰኞ ሩዋንዳ ላይ ሲያጠናቅቁ ለአካባቢው ሃገራት ማስጠንቀቂያ ብጤም አስተላልፈዋል። በተለይ በኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሬፐብሊክ ምሥራቅ ክፍል የቀጠለው ሰብአዊ ቀውስን ኮንጎም ኾነች ጎረቤቷ ሩዋንዳ አስቸኳይ መፍትኄ እንዲያበጁ አሳስበዋል። አንቶኒ ብሊንከን ይህንኑ ማክሰኞ እለት ከኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሬፐብሊክ ርእሰ ብሔር ክሪስቶፍ ሉቱንዱላ እና የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፌሊክስ ሺሴኬዲ ጋር በግንባር በተነጋገሩበት ወቅት አንስተው አስጠንቅቀዋል። ከዐሥር ዓመት በፊት ምሥራቃዊ ኮንጎ የጎማ አውራጃን በመቆጣጠር ሥጋት ፈጥሮ የነበረው M23የተሰኘው የታጣቂ ቡድንን መርዳታችሁን አቁሙም ብለዋል። የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሪፐብሊክ ቋፍ የደረሰ የፀጥታ ኹኔታን በማጣቀስም ለአካባቢው ሃገራት ጥሪ አስተላልፈዋል።
«ከታማኝ ምንጭ በደረሰን መረጃ መሰረት ሩዋንዳ ለM23 ድጋፍ መስጠቷ እጅግ አሳስቦናል። በቀጣናው የሚገኙ አካላት በአጠቃላይ ለM23 የሚያደርጉትን ድጋፍ በአጠቃላይ እንዲያቋርጡ ጥሪ እናስተላልፋለን።»
አንዳንድ ተንታኞች የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር የምሥራቅ ኮንጎ ጉዳይ ያሳሰባቸው ቢመስልም የምር ያስጨነቃቸው ግን የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሠርጌ ላብሮቭ በቅርቡ የአፍሪቃ ሃገራትን መጎብኘታቸው ነው ብለዋል። የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ኢትዮጵያን፤ ግብጽን፤ ኡጋንዳን እና የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ከጎበኙ በኋላ አፍታም ሳይቆይ ነበር የአሜሪካው አቻቸው ወደ አፍሪቃ ያቀኑት። ባሳለፍነው እሁድ ደቡብ አፍሪቃን የጎበኙት አንቶኑ ብሊንከን የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ደርሰው በሩዋንዳ ነበር ጉብኝታቸውን ያጠናቀቁት።
ብሊንከን ሥልጣን ከያዙ ሁለተኛቸው የሆነው ይህ የአፍሪቃ ጉብኝታቸው የሩስያ ተጽእኖን ለመመከት መሆኑን በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል። ዎንዶ ኦማንዩንዲ ቤልጂየም ብራስልስ በሚገኘው የሰላም እና ደኅንነት ምርምር እና መረጃ ተቋም ባልደረባ ናቸው። እሳቸውም በዚሁ ሐሳብ ይስማማሉ።
«ሩዋንዳ በቀጣናው ዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲካዋን ለማደላደል በዚያውም ያልተነገረ የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነትን ለማስፈጸም እምነት የምትጥልባት ቁልፍ ሀገርነቷ ቀጥሏል። ብሊንከን አፍሪቃ ውስጥ በተለይ ሰላም በማስከበሩ ረገድ እጅግ ጠቃሚ ኾኖ ባገኙት የሩዋንዳ ዲፕሎማሲ ክኅሎት ላይም እምነት ማሳደራቸውን ይቀጥላሉ።»
አንቶኒ ብሊንከን ከዘጠኝ ወራት በፊት በነበረው የመጀመረያ የአፍሪቃ ጉብኝታቸው 3 የአፍሪቃ ሃገራትን ማለትም ኬንያ፣ ሴኔጋል እና ናይጄሪያን ጎብኝተው ነበር። አንቶኒ ብሊንከን በወቅቱ ለጉብኝት ስለመረጧቸው ሃገራት ሲናገሩም፦ «ዝቅተኛውን የዴሞክራሲ መስፈርት የሚያሟሉ» የሚል የዳቦ ስም ሰጥተውት ነበር። የዚያን ሰሞን ግን ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን ገለል በማድረግ ከፍተኛ የዴፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር የምትጥርበት ነበር።
አንቶኒ ብሊንከን በአፍሪቃ ሁለተኛ ጉዟቸው በሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የተጎበኘችው የአካባቢው ሀገር ኡጋንዳን ዘለዋል። ኡጋንዳ የዩናይትድ ስቴትስም ኾነ የምዕራባውያን ወዳጅ ተደርጋ ትታይ ነበር፤ የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ብቅ እስካሉበት ድረስ። ምሥራቃዊ ኮንጎን ሰበብ በማድረግም ዩናይትድ ስቴትስ በአካባቢው ተጽኖዋን ለማስጠበቅ እየሠራች እንደሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትሯን ሩዋንዳ እና የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሬፐብሊክ የላከችው በሁለቱ ሃገራት መካከል ሠላም እንዲሰፍን እና የደኅንነት ዋስትና እንዲረጋገጥ ነው ትላለች። ሃገራቱ ግን አማጺያኑን በመርዳት እርስ በእርስ ይካሰሳሉ። የሩዋንዳ መንግስት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1994 ዓ.ም በ800,000 ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሑቱዎች መጨፍጨፍ እጃቸው አለበት ያለቻቸው የሁቱ አማጺያን የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሬፐብሊክ ውስጥ መሽገዋል ሲል ወቀሳ ያሰማል። በቅርቡ ምሥራቅ ኮንጎ ውስጥ የተከሰተው ውጥረት ሌላ ስጋት አጭሯል።
በእርግጥ የሩዋንዳ መንግሥት የM23 አማጺያንን ለመርዳት ወታደሮቹን የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሬፐብሊክ ለመላኩ ተጨባጭ መረጃዎች እንዳሉ የሚናገሩ አሉ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊነት የተጠና እና ይፋ ያልሆነ ዘገባ ይህንኑ እንደሚያረጋግጥ ይነገራል። የሩዋንዳ መንግሥት ይህን የሚያደርገው ለሕዝቡ ደኅንነት መሆኑን የሩዋንዳ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ቪንሴንት ቢሩታ ከአንቶኒ ብሊንከን ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
«የሩዋንዳ መንግሥት የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሪፐብሊክ ውስጥም ኾነ በቀጣናው ማድረግ የቻላቸው ማናቸውም ነገሮች ሕዝባችንን የመጠበቅ ናቸው። የግዛት አንድነታችን እና ሉዓላዊነታችን የሚያስጠብቁ ናቸው። ጉዳዩ ለM23 ድጋፍ መስጠት አይደለም። የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ እና በአካባቢው ዘላቂ መፍትኄ ከተፈለገ፤ የችግሩ ሥረ መሠረትን መጋፈጥ ያሻል።»
ሚንሥትሩ አክለውም የኮንጎ መንግሥት የሩዋንዳ ዲሞክራሲያዊ ነጻ አውጪ ኃይል በፈረንሳይኛ ምህጻር (FDLR) ለተሰኘው የሁቱ አማጺያን ድጋፍ እያደረገ ነው ሲሉ ክስ አቅርበዋል። የኮንጎ ጦር ከሁቱ አማጺያን ጋር ተባብሮ እየሠራም ነው ብለዋል።
የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ከሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ጋር በተነጋገሩበት ወቅትም ስለ አካባቢው ውጥረት አንስተዋል። ሚንሥትሩ ጉዟቸውን አጠናቀው አፍሪቃን ቢሰናበቱም የአካባቢው ሃገራት ውጥረት እና ፍጥጫ ግን ቀጥሏል። አንቶኒ ብሊንከን በሩዋንዳ እና የኮንጎ ዴሞክራሴያዊ ሬፐብሊክ መንግሥታት መካከል የቀጥታ ንግግር እንዲደረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። በዚህ ሁሉ መሀል ግን የሩስያ ወደ አፍሪቃ ማማተር እና ብቅ ማለት ዩናይትድ ስቴትስን ለአጸፌታው እንድትፈጥን አድርጓታል የሚሉ በርካቶች ናቸው። ዋናው ጉዳይ ለፕሮቶኮል አደባባይ ባይወጣም፤ የአንቶኒ ብሊንከንም ኾነ የሩስያው ውጭ ጉዳይ የቅርቡ የአፍሪቃ ጉብኝት ኃያላኑ ሃገራት የአፍሪቃ ወኪሎቻቸውን አሰልፈው ፍጥጫቸውን እንዳጠናከሩ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ማርቲና ሽቪኮቭስኪ
እሸቴ በቀለ