1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንካራው ስምምነት የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነትን ይሽራልን?

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 4 2017

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት የቆዩበትን ውጥረት በቱርክ አደራዳሪነት በአንካራ ማርገባቸው ለሁለቱ አገራት እና ለአፍሪቃ ቀንድ እፎታን የሰጠ ይመስላል። ለስምንት ሰዓታት የዘለቀዉ ታሪካዊ የተባለው የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ የሶማሊያን አገራዊ ሉዓላዊነት ባከበረ መንገድ ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር እንደምታገኝ ያመላክታል፤ ተብሏል።

የአንካራው የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነት
የአንካራው የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነት ምስል Murat Kula//TUR Presidency/Handout/Anadolu/picture alliance

የአንካራው ስምምነት የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነትን ይሽራልን?

This browser does not support the audio element.

የአንካራው ስምምነት የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነትን ይሽራልን?
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ለአንድ ዓመት የቆዩበትን ውጥረት በቱርክ አደራዳሪነት በአንካራ ማርገባቸው ለሁለቱ አገራት እና ለአፍሪቃ ቀንድ እፎታን ሰጥቷል፡፡
በቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይር ኤርዶሃን አሸማጋይነት ስምንት ሰዓታትን የፈጀው ታሪካዊ የተባለው የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ የሶማሊያን አገራዊ ሉዓላዊነት ባከበረ መንገድ ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር እንደምታገኝ ያወሳል፡፡ ይህ የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ እየተገባደደ ባለው የጎርጎሳውያን ኣመት መጀመሪያ ከ11 ወራት በፊት እራሷን እንደ አገር ከምትቆጥረውና ሶማሊያ ግን የግዛቷ አካል አድርጋ ከምትመለከተው ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያሰረችው የመግባቢያ ስምምነት ስለመሻር አለመሻሩ ግን በግልጽ የተቀመጠ ነገር አልተሰማም፡፡

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ባለፈው ዓመት ታህሳስ መጨረሻ ኢትዮጵያ ከራስገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ አጠቃቀም ስምምነት ማሰሯን ተከትሎ የለየለት ዲፕሎማሲያዊ መካረር ውስጥ ገብተው ዓመቱን ሙሉ ዘልቀዋል፡፡ ቱርክ ሁለቱን አገራት ከዚህ በፊት በሁለት ዙር በመጥራት ችግሩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማርገብ ያደረገችው ጥረትም አልሰምር ብሎ፤ አሁን በሶስተኛ ዙር ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒሰርትር ዐቢይ አህመድን ከሶማሊያው አቻቸው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼኸክ ሞሀመድ ጋር ፊትለፊት በማገናኘት ከስምምነት ተደርሷል፡፡


የአንካራው ስምምነት ይዘት
አንካራ ድክላሬሽን የተሰኘው ይህ የአንካራው ስምምነት ሁለቱ አገራት የመጡበትን ልዩነት ወደጎን በመተው በመከባበርና በወዳጅነት ስሜት ለጋራ ብልጽግና እንድተባበሩ ያዛል፡፡ ሁለቱ አገራት በዓለማቀፍ ህግ፣ በተባበሩት መንግስታት ቻርተርና የአፍሪካ ህብረት መርህ መሰረት አንዳቸው ለሌላኛው ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እውቅና ተሰጣጥተዋል፡፡ እንደስምምነቱ ሶማሊያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአፍሪካ ህብረት ተልእኮ ስር ለሚከፍለው የደም ዋጋም እውቅና ሰጥታ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ በተለያየ መንገድ ልገለጽ የሚችል የባህር በር አገልግሎት ታገኛለች፡፡


በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮጳ እና አሜሪካ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክተር ዶ/ር ዳርእስከዳር ታዬ በተለይም ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ይህ ስምምነት ለሁሉም ወገኖች አሸናፊ ነው ይላሉ፡፡ “ስምምነቱ ከሁለቱ አገራት በተጨማሪ ለአደራዳሪዋ ቱርክም ጭምር አዎንታዊነትን ይዞ የመታ ነው፡፡ እሱም ቱርክ በዚህ የሰላም ሚናን በመጫወት አንድ ነጥብ አስመዝግባለች እንዲሁም በአፍሪቃ ቀንድ ለምታደርገው ተሳትፎም ጥሩ ድል ይሆናታል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ትልቁ ግብ የነበረው የባህር በር ማግኘት ነውና ያ ተሳክቷል፡፡ ከዚያም ባሻገር ጥያቄው ዓለማቀፍ እውቅና አግኝቷል፡፡ በሶማሊያ በኩል ደግሞ አገሪቱ ለውጥረቱ እልባት አግኝታ አሁን የውስጥ ጉዳይዋ ላይ ትኩረት እንድትሰጥ ይረዳታል” ብለዋል፡፡
ዶ/ር ዳርስከዳር በአንካራው ድክላረሽን ኢትዮጵያ ያገኘችው ጥቅም ከባህር በር እውቅናም እንደሚሻገርም አክለው ባነሱት አስተያየታቸው፤ “ሶማሊያውያን የኢትዮጵያ ሰራዊት ከያዝነው ወር መጨረሻ በኋላ ከአገራቸው እንደሚወጣ ስገልጹ ነበር፡፡ ባሁኑ ስምምነት ግን በዚያ ሆነን በተሟላ መልኩ ደህንነታችንን ለማስጠበቅ በዚ እንደምንቆ ስምምነቱ ያሳያል” ሲሉ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የሰጠውን ተጨማሪ ያሉት ጥቅም አንስተዋል፡፡

የአንካራው የኢትዮ-ሶማሊላንድ ስምምነት ምስል colourbox


የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት እጣፈንታ
በአንካራው ስምምነት ላይ ዝርዝር ይዘቶቹን በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰጠ ዝርዝር ማብራሪያ እስካሁን አልተሰማም፡፡ በተለይም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያኖረችውየመግባብያ ስምምነትንእጣፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ይሆን ወይ በሚል ጥያቄ ያነሱ በርካቶች ናቸው፡፡ ዶ/ር ዳርስከዳር ግን የአንካራው ስምምነት ስለሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነቱ ምንም እንደማይል በማስረዳት አሁን ላይ ስለተጨባጭ ጉዳዮች ማውራቱ ተገቢነቱ እንደሚጎላ አስተያየታቸውን አጋርተውናል፡፡ “ስለ ኢትዮ-ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት በዚህ የአንካራ ስምምነት ላይ ምንም የተባለ ነገር የለም” የሚሉት ዶ/ር ዳርስከዳር በተጨባጭ መሬት ላይ ስላለው ነገር ማውራቱ ተገቢ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ “መሬት ላይ በተጨባጭ ምን እየተሰራ ነው ብትል ይህ ስምምነት እየተደረገ ባለበት ሰዓት በዚያ በሶማሊላንድ የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ በነበረው የአዲሱ ፕሬዝዳንት በዓለስመት ላይ ኢትዮጵያ መሳተፏ ለሶማሊላንድ እውቅና እየሰጠች እንደሆነ ይቆጠራል” ብለዋል፡፡ “ከአንካራው ስምምነት አንድ ቀን ቀደም ብሎም ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ የባህር ትራንዚት ቢሮ መክፈቷ የሚሳየው የመግባቢያ ስምምነቱ (ከሶማሊላንድ ጋር የተደረገው) አለመታጠፉን የሚያሳይ ነው” በማለትም ትልቁ ምስል ያሉት የባህር በር የማግኘት አስቻይ ሁኔታ ላይ ማተኮሩ ግን እንደሚበልጥ አስረድተዋል፡፡ የአንካራው ስምምነት የሶማሊላንዱን የመግባቢያ ስምምነት አጣብቂኝ ውስጥ አይከትም ወይ የተባሉት ዶ/ር ዳርስከዳር እሱ በሶማሊያ ውስጥ በቀጣይ በሚወሰን ለውጥ (ለምሳሌም ሶማሊያ ከሶማሊላንድ ጋር በሚኖራቸው ቀጣይ ሁኔታ)  እንደሚወሰን ገልጸው የአምናው የኢትዮ-ሶማሊላንድ ምግባቢ ስምምነት ሶማሊያ አሁን ላይ የትዮጵያን የባህር በር በአንክሮ ማስፈለግ ላይ እውቅና እንድትሰጥ ማስገደዱን ግን በምልከታቸው አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አንካራ የደረሱበት ስምምነት እንደ የአፍሪካ ህብረት፣ የውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ባሉ ዓለማቀፍ ማህበረሰብ ተሞካሽቷል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ስምምነቱ በፍጥነት እንዲተገበር ስጠይቅ አሜሪካ በበኩሏ ስምምነቱን አበጀ በማለት በቀጣይነት በሁለቱ አገራት መካከል የሚደረግ ተጨማሪ ውይይት በአገራቱ መካከል መረጋጋትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አለው ብላለች፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW