1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የአንዳራቻ ነዋሪዎች ሥጋት

ዓርብ፣ ኅዳር 20 2017

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሻካ ዞን አንዳራቻ ወረዳ ከጋምቤላ ክልል የተሻገሩ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በሚፈጸሙት ጥቃት ከአካባቢው መፈናቀላቸውን ነዋሪዎች ገለጹ። በወረዳው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ አንድ የቀበሌ ሊቀመንበርን ጨምሮ 20 ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውን ነዋሪዎቹ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሰገን ዙሪያ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሻካ ዞን አንዳራቻ ወረዳ በምትገኘው ሸኬቢዶ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደሚሉት የፀጥታ ሥጋት ገጥሟቸዋል። ፎቶ ከማኅደር ደቡብ ኢትዮጵያ ሰገን ዙሪያ ምስል privat

የአንዳራቻ ነዋሪዎች ሥጋት  

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሻካ ዞን አንዳራቻ ወረዳ በምትገኘው ሸኬቢዶ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደሚሉት የፀጥታ ሥጋት ገጥሟቸዋል። በቀበሌው ከቅርብ ወራት ወዲህ በታጣቂዎች እየተፈጸመብን ይገኛል ባሉት ጥቃት ሰዎች እየሞቱ ፤ መሠረተ ልማቶችም እየወደሙ ይገኛሉ። ከአጎራባች የጋምቤላ ክልል ተሻግረው ገብተዋል ያሏቸው ታጣቂዎች ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ የቀበሌውን አስተዳዳሪ ጨምሮ 20 ሰዎችን መግደላቸውን ሦስት የዐይን እማኞች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የታጣቂዎቹ ጥቃት

በአንዳራቻ ወረዳ ሸኬቢዶ ቀበሌ ባለፈው አንድ ሳምንት ታጣቂዎች አደረሱት በተባለው ጥቃት ሰዎች መሞታቸውን የቀበሌው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ወደ ወረዳው የገቡት ከአጎራባች የጋምቤላ ክልል የመዣንግ ብሔረሰብ ዞን በመነሳት መሆኑን የጠቀሱት የዐይን እማኞቹ «በጥይት ከተገደሉት መካከል አብዛኞቹ አርሶአደሮች ናቸው። ከሟቾቹ መካከል ገዛኸኝ ወንድሙ የተባሉ የሸኬቢዶ ቀበሌ አስተዳዳሪ ይገኙበታል። የሟቾቹን አስክሬን ማንሳትና መቅበር የቻልነው የፌዴራል ፖሊስ ወደ አካባቢው ከገባ በኋላ ነው። አሁን ላይ የፌዴራል የፀጥታ ሀይል በቀበሌው ቢኖርም አዘናግተው ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸሙ ይችላሉ በሚል ሥጋት አካባቢውን ለቀን ወጥተናል» ብለዋል።

ወረዳው ምን ይላል ?

በአንዳራቻ ወረዳ የታጣቂዎች ጥቃትዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የጋምቤላን ክልል ከሚያዋስኑ ቀበሌያት በኩል ተደጋጋሚ ክስተቶች መኖራቸውን የወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ አየለ አገሎ ይናገራሉ። የዚህ ሳምንቱ ጥቃት ፈጻሚዎች ከጋምቤላ ክልል መዣንግ ብሔረሰብ ዞን የተነሱ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው «ታጣቂዎቹ አርሶ አደሮችንና የቀበሌው አስተዳዳሪን ገድለዋል። አሁን የፌደራል የፀጥታ አካላት ወደ አካባቢው ቢገቡም ችግሩ ግን ዘላቂ መፍትሄ የሚያስፈልገው ነው። ጉዳዩ በወረዳው አቅም የሚፈታ አይደለም። ይህንንም ለሻካ ዞን እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር በደብዳቤ አሳውቀናል» ብለዋል።

ጥቃት አድራሾቹ ከጋምቤላ ክልል ተሻግረው የመጡ መሆናቸው ነው የተገለጸው።ፎቶ ከማኅደር፤ ጋምቤላ ከተማ ምስል Negassa Desalegn/DW

የጋራ መፍትሄ  

ዶቼ ቬለ የሻካ ዞን እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር ሃላፊዎች ለማነጋገር ያደረገው ጥረት  አልተሳካም። የታጣቂዎቹ መነሻ ነው የተባለው የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎ ግን በአካባቢው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ መኖሩን ተናግረዋል። «በእነሱ በኩል ብቻ ሳይሆን በእኛም በኩል ሁለቱ ክልሎች ተጎራብተው በሚኖሩባቸው ቀበሌያት ተመሳሳይ የፀጥታ ሥጋት አለ» ያሉት አቶ ኡጁሉ «አሁን ወሰን ተጋርተው የሚገኙ የቀበሌያቱ ነዋሪዎችን ሰላም በጋራ ለመጠበቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በመጪው ሳምንት የሁለቱ ክልል መስተዳድር አመራሮች በጉዳዩ ላይ በመምከር የሰላም እና የፀጥታ በጋራ ለማከናወን የሚያስችል የውይይት መድረክ ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል» ብለዋል።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW