1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአንድ ዓመቱ ጦርነት፣ ዩክሬን እና የዓለም ኤኮኖሚ ኪሳራ

ረቡዕ፣ የካቲት 15 2015

ሕይወታቸው የተጎሳቆለ ሰዎች፣ የፈረሱ መኖሪያ ቤቶች፣ የወደሙ መሠረተ-ልማቶች በመጪው አርብ አንድ ዓመት የሚደፍነው ጦርነት ለዩክሬን መለያ ናቸው። ጦርነቱ የዓለም ኤኮኖሚ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳያገግም በዋጋ ንረት፣ የምግብ ዋስትና መጓደል እና የኃይል እጥረት የራሱን ሚና ተጫውቷል።

Ukraine Bachmut | Ukrainische Artillerie
ምስል፦ Bulent Kilic/AFP/Getty Images

የአንድ ዓመቱ ጦርነት፣ ዩክሬን እና የዓለም ኤኮኖሚ ኪሳራ

This browser does not support the audio element.

ዩክሬን ከምድር እና ከሰማይ የሚምዘገዘጉ የሩሲያ ሚሳይሎችን ውርጅብኝ በአንጻራዊነት ተቋቁማ እስከ ዛሬ መዝለቅ ብትችልም ጦርነቱ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ሕይወት ነጥቋል። በሚሊዮኖች ሲፈናቀሉ የዩክሬን ከተሞች እና መሠረተ-ልማቶች ወድመዋል። ለዚህ በምሥራቃዊ ዩክሬን ክራስኖሆሪቭካ ከተማ በሚገኝ የፈረሰ ሆስፒታል የሚኖሩት ወይዘሮ ምስክር ናቸው። ወይዘሮዋ ቫለንቲያ ሞዝጎቫ ከጦርነቱ በፊት በላብራቶሪ ባለሙያነት ያገለግሉበት የነበረ ሆስፒታል በሩሲያ ከባድ መሳሪዎች ድብደባ እንዳልነበረ ሆኗል።

ውጊያው በርትቶ ባልደረቦቻቸው ሲሸሹ ወይዘሮዋ ለ40 ዓመታት ገደማ ባገለገሉበት ሆስፒታል በጥበቃ ሠራተኝነት ተቀጠሩ። ቫለንቲያ ሞዝጎቫ የሚጠብቁት ሆስፒታል የተለያዩ ሕክምናዎች ይሰጥባቸው የነበሩ ክፍሎች ፈርሰዋል። እንዲህ አይነቶቹ ጥቃቶች ወይዘሮዋን እጅግ የሚያብሰለስሉ ናቸው።

ቫለንቲያ ሞዝጎቫ "ለምንድነው ከተሞቻችንን የሚያወድሙት? ስለምን ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች እና መሠረተ-ልማቶች ያወድማሉ? እኛን በኃይል ለማስወጣት? አላውቅም። ወይስ ፑቲን የጅምላ ግድያ መፈጸም ይፈልጋሉ?" እያሉ ይጠይቃሉ።

በዩክሬን ሆስፒታሎች፣ የመኖሪያ ሕንጻዎች፣ እንደ ባቡር ያሉ መጓጓዣዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የኃይል ማመንጪያዎች እና የንግድ ተቋማት ከሰማይ እና ከባህር በሚምዘገዘጉት የሩሲያ ሚሳይሎች ለብርቱ ጉዳት ተዳርገዋል።ምስል፦ Genya Savilov/AFP(Getty Images

እንዲህ ወይዘሮ ቫለንቲያ ሞዝጎቫን ለሐዘን እና ለቁጭት የሚዳርጉ የሩሲያ ድብደባዎች የተፈጸሙት በአንድ ከተማ ወይም በአንድ ሆስፒታል ላይ ብቻ አይደለም። አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀሩት ጦርነት ከ700 በላይ የጤና ተቋማት ላይ ሩሲያ ጥቃት መፈጸሟን አምስት የዩክሬን ድርጅቶች ያጠናቀሯቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገው ሰነድ ላይ እንደሰፈረው ሩሲያ በጤና ተቋማት ላይ በፈጸመቻቸው 750 ጥቃቶች 101 ሰዎች ተገድለዋል። የዩክሬን የጤና ሚኒስትር 1,200 የጤና ተቋማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መውደማቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 173 ሆስፒታሎች ተመልሰው ሊጠገኑ በማይችሉበት ደረጃ የፈረሱ ናቸው።

በዩክሬን የጤና ተቋማት ይዞታ ላይ የሚሰራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በተባባሪነት ያቋቋሙት ፓቭሎ ኮቭቶንዩክ "ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ከተሞች በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ናቸው። ይኸ ማለት አንድ ወይም ተደጋጋሚ ስህተት የሚፈጽመው አንድ ዕዝ አይደለም። አንድ ጨካኝ ወታደራዊ አዛዥ ሊኖር ይችላል። ይኸ ግን በሶስት የተለያዩ ቦታዎች፤ በሶስት የተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች የተፈጸመ ነው። ይኸ ደግሞ ሆን ብለው የሚከተሉት የጦርነት ስልት እንደሆነ ይጠቁማል" ሲሉ ተናግረዋል።

የጦርነቱ ሰለባ የሆኑት የጤና ተቋማት ብቻ አይደሉም። የመኖሪያ ሕንጻዎች፣ እንደ ባቡር ያሉ መጓጓዣዎች፣ ኢንዱስትሪዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የኃይል ማመንጪያዎች እና የንግድ ተቋማት ከሰማይ እና ከባህር በሚምዘገዘጉት የሩሲያ ሚሳይሎች ለብርቱ ጉዳት ተዳርገዋል። የኪየቭ የኤኮኖሚ ትምህርት ቤት እስካለፈው ታኅሳስ ወር ብቻ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ኪሳራ 137.8 ቢሊዮን አድርሶታል። 

በዶንባስ ግዛት ሶሌዳር ከተማ የሚገኘው ይኸ የጨው ማቀነባበሪያ በሩሲያ ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ይታያል። ዶንባስ ሩሲያ ይገባኛል ከምትላቸው የዩክሬን አካባቢዎች አንዱ ነው። ምስል፦ Alex Chan/ZUMA/IMAGO

የዩክሬን ጦርነት እና የስንዴ ሸማቾች ቅርቃር

ዩክሬን በለም ጥቁር አፈሯ "የአውሮጳ የዳቦ ቅርጫት" የሚል ስም የተጎናጸፈች አገር ነች። ባለፈው ዓመት ዩክሬን 106 ሚሊዮን ቶን እህል አምርታ በሰኔ እና ሐምሌ ወራት ብቻ 43 ሚሊዮን ቶኑን በዓለም ገበያ ሸጣለች። ይኸ ግን አልዘለቀም። የዩክሬን የጥቁር ባሕር ወደቦች አሁን ዝግ ናቸው፤ አሊያም ከዚህ ቀደም በነበረ አቅማቸው ልክ ወደ ሌላው ዓለም የሚጓጓዝ እህል ወደ መርከቦች አይጭኑም።

በርካታ ገበሬዎች እንዳሻቸው በእርሻ ማሳዎቻቸው ሥራዎቻቸውን ማከናወን አይችሉም ወይም ገበሬዎቹ ራሳቸው የውጊያው ተሳታፊ ሆነዋል። በዚህ ሳቢያ የተከተለው ዳፋ ታዲያ ባህር እና ድንበር ተሻግሮ በዓለም ገበያ ሁሉ የታየ ነው። በአውሮጳ የምግብ ዋስትና ጥያቄ ባይነሳም በጦርነቱ የተስተጓጎለው የኃይል አቅርቦት እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የኑሮ ውድነት አስከትሏል።

በዓለም ገበያ የታየው የእህል ዋጋ ውድነት 50 በመቶ ገደማ ምግባቸውን ከሩሲያ እና ከዩክሬን በሚሸምቱ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አገራት ብርቱ የምግብ ዋስትና ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋትም አለ። ሱዳን ከዓለም ገበያ ከምትሸምተው ስንዴ 87 በመቶው በዩክሬን እና በሩሲያ የተመረተ ነው። ጎረቤቷ ግብጽ ባለፈው ዓመት ከሸመተችው ስንዴ 80 በመቶው አሁን ጦርነት የገጠሙት የሁለቱ አገሮች ገበሬዎች ያመረቱት ነበር።

በዚህ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ክራማቶርስክ በተባለ አካባቢ የተነሳ ፎቶ ግራፍ አንድ የዩክሬን ገበሬ በአየር ድብደባ ሳይፈጠር እንዳቀረ ከሚገመት ጉድጓድ አጠገብ ማሳውን ሲያርስ ይታያል። ምስል፦ Miguel Medina/AFP/Getty Images

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ለተቸገሩ ሰዎች እርዳታ የሚያቀርበው የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ግማሽ ያክል ሸቀጡን የሚሸምተው ከዩክሬን ነበር። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ባለፈው ዓመት ኪየቭን ከጎበኙ በኋላ "በዓለም ዙሪያ 125 ሚሊዮን ሰዎች ለመመገብ ከሚያስፈልገን እህል 50 በመቶውን የምንሸምተው ከዩክሬን ነበር። ለዓለም ገበያ የሚቀርበው 30 በመቶ ስንዴ፤ 20 በመቶ በቆሎ፤ 20 በመቶ የሱፍ አበባ ዘይት በዩክሬን እና በሩሲያ አካባቢ የሚመረት ነው። ስለዚህ በዓለም ዙሪያ አስከፊ ተጽዕኖ ይኖረዋል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ጦርነቱ እንደተጀመረ በአሜሪካ እና የአውሮጳ ኅብረት የሚመራው የምዕራባውያን ጥምረት በሩሲያ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ማዕቀቦች እያከታተለ በመጣል ጫና ለማሳደር ሞክሯል። በዚህም ሳቢያ የሩሲያ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ሩብል ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን ተዳከመ፤ የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔውን በእጥፍ ሲያሳድግ የሞስኮ የአክሲዮን ገበያ ለቀናት ለመዘጋት ተገደደ።

ማዕቀቦቹ ምን ፈየዱ?

የአውሮጳ ባለሥልጣናት ማዕቀቦቹ "ግዙፍ እና ኃይለኛ ተጽዕኖ" የሚያሳድሩ ለመሆናቸው እምነት ነበራቸው። የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎችም በማዕቀቦቹ ጫና የሩሲያ ኤኮኖሚ እንደሚያሽቆለቁል ጠብቀዋል፤ ወይም ተንብየዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በጥር 2015 ይፋ ያደረገው ትንበያ የሩሲያ ኤኮኖሚ በዩክሬን ጦርነት እና ጦርነቱን ተከትሎ በተጣሉበት በርከት ያሉ ማዕቀቦች የገጠመውን ፈተና ተቋቁሞ መዝለቁን አሳይቷል። ድርጅቱ ቀደም ብሎ በጎርጎሮሳዊው 2023 የሩሲያ ኤኮኖሚ በ2.2 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል የሰጠውን ትንበያ ከልሶ እንዲያውም በ0.3 በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ይፋ አድርጓል።

የኤኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት የነዳጅ እና ጋዝ ሽያጭ ባለፈው ዓመት የሩሲያን ኤኮኖሚ ታድጓል። ምስል፦ Dmitry Dadonkin/TASS/Sipa USA/IMAGO

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን "ምዕራባውያኑ ጦራቸውን በማዝመት እና በመረጃ ብቻ ሳይሆን በኤኮኖሚው ግንባርም ዘመቻ ከፍተውብናል። ነገር ግን ምንም አላሳኩም፤ ወደፊትም ምንም አያሳኩም። ከዚህ በላይ ግን የማዕቀቦቹ አመንጪዎች በየአገራቸው የዋጋ ንረት፣ የሥራ አጥነት፣ የንግድ መደብሮች መዘጋት እና የኃይል እጥረት ቀውስ በመፍጠር ራሳቸውን ቀጥተዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የሩሲያ ኤኮኖሚ ከተጠበቀው የተሻለ እንዲሆን ያደረጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ቀዳሚው አገሪቱ የምታመርተው ነዳጅ እና ጋዝ ነው። የአውሮጳ ኅብረት ካለፈው አመት አብዛኛዎቹን ወራት የሩሲያን ነዳጅ እና ጋዝ ሲሸምት የቆየ ሲሆን የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት ከወደ ቻይና እና ሕንድ አዳዲስ ደንበኞች አግኝቷል። ማዕቀቦቹም ቢሆኑ ሩሲያ ክሬሚያን ከዩክሬን ከገነጠለችበት ከጎርጎሮሳዊው 2014 ጀምሮ የተለማመደቻቸው ናቸው። ሩሲያ ከሕንድ እና ቻይና ጋር ያላትን የንግድ ልውውጥ ማጠናከሯ ደግሞ ማዕቀቦቹን ለመቋቋም ሁነኛ መንገድ አበጅቷል።

ከዓመት ጦርነት በኋላስ?

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የጦርነቱ ባለቤት እየተባሉ እንደሚከሰሱ ሁሉ እርሳቸውም ምዕራባውያን ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ። ፑቲን ምዕራባውያንን አጥብቀው በተቹበት የዕለተ ሰኞ ንግግራቸው አገራቸው ሩሲያ በመጪዎቹ ዓመታት ግንኙነቷ ከአውሮጳ እና አሜሪካ እየራቀ እንደሚሔድ ጥቆማ የሰጠ ነው።

ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን “ከታኅሳስ 2021 ሲነጻጸር በዓለም አቀፍ ክፍያዎቻችን የሩሲያ ሩብል ድርሻ ወደ አንድ ሶስተኛ ከፍ ማለቱን መጥቀስ እፈልጋለሁ። የተረጋጋ ደሕንነቱ የተጠበቀ፣ ከዶላር እና ሌሎች የምዕራባውያን መገበያያ ገንዘቦች የተላቀቀ ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓት ከአጋሮቻችን ጋር ማበጀታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

አውሮጳ በአብዛኛው ከሩሲያ ነዳጅ እና ጋዝ ጥገኝነት መላቀቅ ችሏል። የኅብረቱ አባል አገራት ባለፈው ታኅሳስ በሩሲያ ነዳጅ ላይ የተመን ገደብ የሚያኖር ማዕቀብ ይፋ አድርገዋል። የፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥት የዩክሬን ወረራውን እንዲያቆም ለማስገደድ አውሮጳም ሆነ አሜሪካ ተጨማሪ ማዕቀብ ሊጥሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርሱላ ፎን ደር ለይን "ሩሲያ፣ ሩሲያውያን እና የአገሪቱ ኤኮኖሚ እኛ በጣልናቸው ምዕቀቦች ምክንያት ከባድ ዋጋ እየከፈሉ ነው" ሲሉ ተጽዕኖውን ባለፈው ወር በዩክሬን ከፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጋር በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

በአሜሪካ እና የአውሮጳ ኅብረት የሚመሩት ምዕራባውያን በቢሊዮን ዩሮ የሚቆጠር ሰብዓዊ፣ ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ለዩክሬን ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ምስል፦ Metin Aktas/AA/picture alliance

ፎን ደር ለይን የጦርነቱ አንደኛ ዓመት በሚታሰብበት የካቲት 17 ተግባራዊ የሚሆን ማዕቀብ እንደሚኖርም ጥቆማ ሰጥተዋል። "ይኸ ማዕቀብ ወደ 10 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ ሲሆን እንደቀደሙት እጅግ ግዙፍ ነው። ዕቅዱ ሩሲያ ልትጠቀምባቸው የምትችል ቴክኖሎጂዎች ላይ ያነጣጠረ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ከማዕቀቦቹ በተጨማሪ የሩሲያ ወረራ ከተጀመረ ወዲህ ብዙ የምዕራባውያን መሪዎች “ከዩክሬን ጋር ለመቆም” ቃል ገብተው ከፍተኛ ወታደራዊ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል። የጀርመኑ ኪየል የዓለም ኤኮኖሚ ጥናት ማዕከል ይፋ ባደረገው ስሌት መሠረት አሜሪካ በአጠቃላይ 73.1 ቢሊዮን ዩሮ የሰብዓዊ፣ ወታደራዊ እና የገንዘብ ድጋፍ ለዩክሬን ለመስጠት ቃል ገብታለች። የአውሮጳ ኅብረት አሜሪካንን በመከተል በ54.9 ቢሊዮን ዩሮ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጀርመን በተናጠል 6.15 ቢሊዮን ዩሮ በአውሮጳ ኅብረት በኩል ደግሞ  7.2  ቢሊዮን ዩሮ ትሰጣለች።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW