1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

የአካል ጉዳተኞችን ህይወት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች

ፀሀይ ጫኔ
ረቡዕ፣ ግንቦት 13 2017

ባለንበት የዲጅታል ዘመን የአካል ጉዳተኞች የሚያጋጥሟቸውን ልዩ ልዩ ፈተናዎች ለማቃለል የተነደፉ በርካታ አጋዥ ቴክኖሎጂዎች አሉ። እነዚህ ቴክኖሎጂዎች እንቅስቃሴን እና ተግባቦትን በማሳደግ ፣እንዲሁም የዕለት ተዕለት ህይወትን በማቃለል ለአካል ጉዳተኞች የተለዬ እድል እየሰጡ ነው። ከነዚህ ቴክኖሎጂዎች መካከል ጥቂቶቹን አነሆ።

ሚዲማፕስ መተግበሪያ ማየት የተሳናቸው ሰዎችን ያግዛል።
ሚዲማፕስ መተግበሪያ ማየት የተሳናቸው ሰዎችን ያግዛል።ምስል፦ BindiMaps

የአካል ጉዳተኞችን ህይወት የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች

This browser does not support the audio element.

እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት 1ነጥብ 3 ቢሊዮን ሰዎች ወይም ከጠቅላላው የዓለም ህዝብ 16 በመቶ ከአካል ጉዳት ጋር ይኖራል።
ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት ሰዎች አንዱ ተሽከርካሪ ወንበር የሚጠቀም ወይም መስማት የተሳነው አሊያም የማየት ችግርን የመሳሰሉ ከፍተኛ የአካል ጉዳቶች ያጋጥመዋል ተብሎ ይገመታል።
አጋዥ ቴክኖሎጂዎች እነዚህን አካል ጉዳተኞች ከሰዎች ጋር ያላቸውን መስተጋብር በማሻሻል ፣ራሳቸውን ችለው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ  የዕለት ተዕለት ኑሯቸው የተቃና እንዲሆን መንገድ እየከፈቱ ነው።  ተመራማሪዎች ለአካል ጉዳተኞች አጋዥ መሳሪያዎችን ለማዘጋጀት ለረጅም ጊዜ ሲሞክሩ ቆይተዋል፣ እና ባለፉት አመታት ብዙ ጠቃሚ እድገቶች ታይተዋል። ይህም አካል ጉዳተኞች ሙሉ እና ትርጉም ያለው ህይወት እንዲኖሩ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። 

የሙዚቃ ኮንሰርት መስማት ለተሳናቸው

ከነዚጅም መካከል ሚክ አቢሊንግ አንዱ ሲሆኑ ላለፉት 15 ዓመታት በርካታ አጋዥ ቴክኖሎጅዎችን ሰርተዋል።አቢሊንግ እና ቡድናቸው « ኖት ኢምፖሲብል ላብ »በተባለው ፕሮጀክታቸው  ለአካል ጉዳተኞች  አዲስ መንገድ በመክፈት ላይ ነው። ይህ የሙዚቃ ፕሮጀክት ከብዙዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን፤በዚህ ፕሮጀክት በጀርባ በሚታዘል ጃኬት መሳይ ነገር በመስራት ፤መስማት የተሳናቸው  ሰዎች የሙዚቃ ኮንሰርት እንዲታደሙ ዕድል ሰጥቷል። ይህ ጃኬት መስማት የተሳናቸውም ሆነ መስማት የሚችሉ ሰዎች በቆዳቸው አማካኝነት የሙዚቃ  እና ንዝረትን  እንዲሰሙ የሚያስችል  ቴክኖሎጂን ይዟል።ሚክ አቢሊንግ  እንደሚሉት በዚህ ቴክኖሎጂ ቆዳ የጆሮን ስራ ተክቶ ይሰራል

«ቆዳ፤ የጆሮ ታምቡርን በመተካት የመስማት ስራን ይሰራል። በዚህም መስማት ለተሳናቸው ሰዎች፣ የእነዚያ ንዝረቶች ስሜት እና ፍጹም ተመሳሳይነት ባልተለመደ እና አስደሳች በሆነ መልኩ የመሰማት ችሎታን ሰጥቷቸዋል። አስገራሚው ነገር መስማት የተሳናችውም ሆነ  መስማት የሚችሉ ሰዎች የሙዚቃን ልብስ ለብሰው ነበር። ያ ደስ የሚል ገጠመኝ ነበር። ሰዎች አንተን እያዩ ፤ኦ አምላኬ በጣም አስደናቂ ነው።ይላሉ። »

አዲሱ ቴክኖሎጂ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች የሙዚቃ ኮንሰርት እንዲታደሙ አድርጓል። ምስል፦ Not Impossible Labs

ይህ ዲጅታል ጃኬት ለወገብ ፣ ለእጅ እና ለእግር  የሚሆኑ 28 ሞተሮች ተዘጋጅቶለታል። እነዚህም እያንዳንዳቸው ልዩ ምልክቶችን ይልካሉ። ይህም ማለት እያንዳንዱ መሳሪያ ለጊታር ወይም ለከበሮ ሙሉ ለሙሉ የተለየ ስሜት ይሰጣል።በቀላል ክብደት ያለው ይህ ጃኬት ሰዎች እንደ ሰውነት መጠናቸው ማስተካከል እንዲችሉ ተደርጎ የተሰራ ነው።ቴክኖሎጂው ለአጠቃቀም  ቀላል ሆኖ መሰራቱን ይገልፃሉ።
«ማንኛውንም ነገር ቀላል አድርገህ ከሰራኸው። ሰው በትክክል እንዲጠቀምበት ለማድረግ የበለጠ እድል ትሰጣለህ።አንድን ነገር ይበልጥ በተወሳሰበ  ቁጥር፣ለመጠቀም የበለጠ አስቸጋሪ ይሆናል።እና እኔ እንደማስበው በፕሮጀክቱ ያንን ነው ያደረግነው። እና ለዛ ይመስለኛል ሰዎች በሚኖሩበት ቦታ ይህን ነገር ለመስራት ቀላል ጊዜ የነበራቸው »

አጋዥ የማዳመጫ ቴክኖሎጂዎች/Assistive Listening Systems/

ይህ ቴክኖሎጂ የመስማት ችግር ያለባቸውን ወይም መስማት አቅማቸው የቀነሱ ሰዎችን  የሚያግዝ  ነው። ይህ አጋዥ ቴክኖሎጂ  ብዙውን ጊዜ ተማሪዎች በትምህርት ቤት  ውስጥ የሚሰጥ ትምህርትን  ለማዳመጥ ይጠሙበታል።መሣሪያው በተጠቃሚው ዙሪያ ያለውን ድምጽ  በመሰብሰብ  ወደ ጆሮዎቻቸው የሚያመጣ ሲሆን፤ ይህም በአካባቢያቸው ምን እየተከናወነ እንዳለ እንዲሰሙ ያስችላቸዋል።እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ለአካል ጉዳተኞች ትልቅ ግብአት ናቸው።

ፅሁፍን ወደ ድምፅ የሚቀይሩ ሶፍትዌሮች

መስማት ለተሳናቸው ሰዎችን ከሚያግዙ ቴክኖሎጅዎች ባሻገር ማየት ለተሳናቸው የሚያግዙ በርካታ ቴክኖሎጂዎች አሉ።ከነዚህም መካከል ፅሁፍን ወደ ድምፅ የሚቀይሩ ሶፍትዌሮች ይገኙበታል።ፅሁፍን ወደ ድምፅ የሚቀይሩ ሶፍትዌሮች /Screen Readers/ማየት ለተሳናቸው ወይም የዕይታ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሰዎች የሚረዱ የሶፍትዌር ፕሮግራሞች ናቸው።ይህ ቴክኖሎጂ በማንኛውም ዲጅታል ቴክኖሎጂ ስክሪን ላይ የሚታየውን ፅሁፍ ወይም ምስል  ወደ ድምፅ  ወይም  ወደ ብሬይል  ፅሁፍ በመቀየር ማየት የተሳናቸው ሰዎች በቀላሉ እንዲረዱት የሚያስችል ነው።በዚህ ሁኔታ ስክሪን አንባቢዎች/Screen Readers/ ማየት ለተሳናቸው ወይም እይታቸው ለቀነሰ ሰዎች ኮምፒተር ላይ  እንዲሰሩ  እና የዘመኑን ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ ዕድል ይሰጣሉ።

ሌላው «ቢንዲማፕስ»የተሰኘው  መተግበሪያ ማየት የተሳናቸው ሰዎች በትልልቅ ህንጻዎች ውስጥ አንድን የተለዬ ቦታ ለማግኘት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ነው።ምስል፦ Artlist

ኢትዮጵያዊው  ባልከው ዓለሙ ማየት የተሳነው የሁለተኛ ደረጃ መምምህር ነው።ከመምህርነቱ በተጨማሪ  ድምፃዊም ነው። ባልከው በ2014 ዓ/ም «የኔ ዓለም« የተሰኘ  የሙዚቃ አልበም ለአድማጭ ጀሮ አድርሷል። ለዚህ ስራው  ታዲያ ቴክኖሎጂ ትልቅ እገዛ እንዳረገለት ይገልጻል።
ኮምፒዩተርን እና ተንቀሳቃሽ ስልክን በቀላሉ በመጠቀምም ለሌሎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው የሚረዱ መተግበራዎችን ይጠቀማል።
ያም ሆኖ እንደ «ስማርት ኬን» ወይም ዘመናዊ የመንገድ መሪ ምርኩዞች ያሉ ጠቃሚ ቴክኖሎጂዎች አካባቢን ግንዛቤ ያላስገቡ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ለአጠቃቀም ምቹ እና ውጤታማ አለመሆናቸውን ገልጿል።በመሆኑም ሀገር በቀል የፈጠራ ሰዎች  አካባቢን መሰረት ያደረጉ እና ለአካል ጉዳተኞች አጋዥ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እንዲያለሙ ባለሀብቶች እና መንግስት ድጋፍ ቢያደርጉ መልካም ነው ይላል።

ብሬል የሚያትም ማሽን/Braille Embossers/

ማየት ለተሳናቸው ሰዎች ብሬይልን በመጠቀም ሰነዶችን የሚያትሙ የማተሚያ ማሽኖች ናቸው። ፅሁፎችን በብሬይል መልክ ለማተም መሳሪያዎቹ በቀላሉ ከኮምፒተር ጋር ይገናኛሉ።በዚህም ቀለም ከመጠቀም ይልቅ ሰነዶችን ማየት ለተሳናቸው ሰዎች ተደራሽ ለማድረግ በወረቀቱ ላይ ከፍ ያሉ ነጠብጣቦችን ይፈጥራሉ።

ፅሁፎችን በብሬይል መልክ ለማተም የሚያግዙ ማሽኖች የአካል ጉዳተኞችን ህይወት እያቀለሉ ነው።ምስል፦ Solomon Muche/DW

«ቢንዲማፕስ»/ BindiMaps/አቅጣጫ ጠቋሚ መተግበሪያ  

ሌላው «ቢንዲማፕስ»/ BindiMaps/የተሰኘው  መተግበሪያ  ማየት የተሳናቸው ሰዎች በትልልቅ ህንጻዎች ውስጥ አንድን የተለዬ ቦታ ለማግኘት የሚረዳ ቴክኖሎጂ ነው።«ቢንዲማፕስ» የጎግል ካርታዎችን ቤት ውስጥ ይጠቀማል። በዚህም ቢንዲማፕስ  30 ሴንቲሜትር ርቀት ድረስ ትክክለኛ ቦታን ይመራል። ያ ማለት ፖስታ ቤት ገብተው  የፖስታ ቤት  ማህተሙ የት እንደሚገኝ እንኳን በትክክል ሊነግረዎት ይችላል። ዓይነ ስውራን ወይም ዝቅተኛ የማየት ችሎታ ያለው ሰው በድምጽ ሊጠቀምበት ይችላል። በመጀመሪያ፣ ካርታ፣ ከዚያም በድምፅ የሚነገሩ አቅጣጫዎችን ያቀርባል።
የመተግበሪያው መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ አና ራይት  የመተግበሪያው ሀሳብ ቤት ውስጥ የሚገኙ ውስብስብ  ቦታዎችን በቀላሉ ለማግኘት ነው ይላሉ።
«ሁሉም ሰው በቤት ውስጥ የሚፈልገውን ነገር የሚያገኝበትን አካባቢ ነው የፈጠርነው።ይህም ትምህርት ሊሆን ይችላል፣ በኋላ ደግሞ ስራ  ቦታ ወይም ከጓደኞች ጋር ወደ ሱቆች  ወይም መዝናኛ ቦታ መሄድ  ሊሆን ይችላል።ለሰዎች እንቅፋቶችን እየቀነስን ነው። እና ያ በጣም ያስደስተኛል።»  
የመተግበሪያው ስለተቀመር ሰውሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም በአንድ ጊዜ መፈለግ እና ካርታ መስራት ያስችላል።ከዚያም  በአንድ ህንፃ  ውስጥ  ፈጣን በሆነ መንገድ ቦታን ለማግኘት ይሰራል። ይህም ሰዎች በተለይም ማየት የተሳናቸው ከአንድ ጫፍ ወደ ሌላ ጫፍ ያለምንም ችግር  እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል።
ይህ  መተግበሪያ በአፕ ስቶር ውስጥ የሚገኝሲሆን፤ አና ራይት እንደሚሉት አውስትራሊያ ውስጥ ወደ 90 በሚጠጉ አካባቢዎች ጥቅም ላይ ውሏል። በጎርጎሪያኑ 2022 ዓ/ም ቴክኖሎጂው በሃንጋሪ የቡዳፔስት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያም መተግበሪያው ተጭኗል። አሰራሩን እንዲህ ያስረዳሉ።  «ስለዚህ የወለል ካርታ ያስፈልገናል። የምንጠቀመውን ካርታ  እና ወደ መተግበሪያችን የሚገቡ በጣም የሚያምሩ ዲጂታል ካርታዎችን ለመፍጠር። በዚያ ላይ እኛ ማድረግ ያለብን ፤ ሄደን ቦታውን ቪዲዮ ማንሳት አለብን። እና የአካባቢያችንን ሁኔታ በዚህ መንገድ እናዘጋጃለን። ከዚያ ውሂቡን ከቪዲዮዎቹ እንወስድ እና እንደ ዲጂታል መንትያ አይነት ነገር እንፈጥራለን።»

በእግር የሚሰራ የኮሚፒዩተር ማውዝ

መስማት እና ማየት የተሳናቸውን ሰዎች ከሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች  በተጨማሪ መንቀሳቀስ የማይችሉ ሰዎችን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች አሉ።ከነዚህም መካከል በእግር የሚሰራ የኮሚፒዩተር ማውዝ/Footmouse/ አንዱ ነው።በእግር የሚሰራ የኮሚፒዩተር ማውዝ ስሙ እንደሚያሳየው በእግር የሚሰራ ነው። ይህም እጃቸው መንቀሳቀስ ለማይችሉ ወይም የጣት አንጓ ችግር ላለባቸው ሰዎች  በእግራቸው አማካኝነት ኮምፒውተርን መጠቀም እንዲችሉ ያደርጋል።ይህም ለአካል ጉዳተኞች  አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ ውጤታማነትም ይጨምራል።

መንቀሳቀስ የማይችሉ ሰዎችን ከሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች መካከል በተለዬ ሁኔታ የሚሰሩ የኮምፒዩተር ኪቦርዶች ይገኙበታል።ምስል፦ Claudio di Vizia/Pond5 Images/IMAGO

አማራጭ ኪቦርዶች/Alternative Keyboards/

አማራጭ ኪቦርዶች ከመደበኛዎቹ  ኪቦርዶች በአሰራራቸው የተለዩ ሲሆኑ፤አካል ጉዳተኞች ኮምፒዩተርን በቀላሉ ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው። እነዚህ ኪቦርዶች የተለያዩ አወቃቀሮች ያሏቸው እና በተገደበ የእጅ እና የጣት እንቅስቃሴ ምክንያት መደበኛ ኪቦርዶችን መጠቀም ለማይችሉ ሰዎች በተለዬ ሁኔታ የተሰሩ ናቸው። እነዚህ ኪቦርዶች ትልቅ ፣ትንሽ እና «ኤርጎኖሚክ» የሚባሉ አማራጮችም አሏቸው።በዚህ ሁኔታ አጋዥ ቴክኖሎጂዎች እንደ ናይጄሪያዊው ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ መስራች ኦፑሉቫ አኮኖላ ላሉ አካል ጉዳተኛ ባለሙያዎች ዕድል ሰጥተዋል።
«ወጣት ተመራቂ በነበርኩበት ጊዜ ሥራ እፈልግ ነበር። ጥሩ ብቃት ነበረኝ፣ ግን ማንም አይቀጥረኝም ነበር። ምክንያቱም ያኔ ዓይነ ስውራን መደበኛ በሆነ ቢሮ ውስጥ መሥራት አይችሉም ብለው ያምኑ ነበር። እና ቴክኖሎጂ ያንን እንቅፋት ሊሰብር እንደሚችል ተረዳሁ።» መምህር እና ድምፃዊ ባልከው ዓለሙም ይህንኑ  ሀሳብ ያጠናክራል።

አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ማድረግ

በአሁኑ ጊዜ በአደጉ ሀገራት  በእድሜ የገፉ ሰዎች መብዛት፤ በአዳጊ ሀገራት ደግሞ  በሽታ እና ጦርነት  ለአካል ጉዳት መጨመር  አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።ስለሆነም በዓለማችን ተጨማሪ ዲጂታል የመርጃ መሳሪያዎች በዚያው ልክ ያስፈልጋታል። እነዚህ ቴክኖሎጂዎችም ለሁሉም ሰው በሚመች መልኩ መስራት  እና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ወሳኝ መሆኑ ይነገራል።ያ ማለት ቴክኖሎጂዎቹን ከመስራት ባሻገር ሁሉን አቀፍ፣ ተደራሽ እና ተመጣጣኝ ማድረግ አስፈላጊ ነው።


ፀሀይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ  

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW