1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአካል ጉዳተኞችን ተግዳሮትና ተስፋ

ሐሙስ፣ ኅዳር 26 2017

ከዓለም ሕዝብ 16 በመቶ የሚሆኑት የአካል ጉዳተኞች መሆናቸውን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ10 ዓመታት በፊት የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ከአጠቃላዩ ሕዝብ ከ17 በመቶ በላይ መሆኑ ነው የተገለጸው። በሕግ የሰፈሩ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት የሚሰጡ መመሪያዎች ቢኖሩም ተግባራዊነታቸው ዛሬም ምላሽ ይሻል የሚሉ ወገኖች አሉ።

በዊልቸር የተቀጠች አዳጊ
አካል ጉዳተኞችን ያገናዘቡ ምቹ መሠረተ ልማቶች ያስፈልጋሉ ፎቶ ከማኅደር ምስል davit85/Pond5 Images/IMAGO

የአካል ጉዳተኞችን ተግዳሮትና ተስፋ

This browser does not support the audio element.

 

የዓለም ባንክ በመላው ዓለም ከአንድ ቢሊየን በላይ ሰዎች የአካል ጉዳተኝነት እንደሚያጋጥማቸው ያመለክታል። በዚህ ረገድ በተለይ በአዳጊ ሃገራት የእነዚህ ወገኖች ቁጥር ከፍ እንደሚልም ይገልጻል።  የዓለም ባንክ አክሎም አካል ጉዳተኞች ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ተሳትፏቸው ውሱን እንደሆነ ነው የሚገልጸው። በአዳጊ ሃገራት የሚገኙት ትምህርት፣ ተገቢ የጤና አገልግሎት፣ እና የሥራ ቅጥር እድሎች ስለማያገኙ ለከፍተኛ ድህነት መጋለጣቸውንም አመልክቷል። ድህነት ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እንዳያገኙ ስለሚያደርግም ለአካል ጉዳተኝነት የመጋለጥ አጋጣሚን ሊያስከትል ይችላልም ባይ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በብሔራዊ ደረጃ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንደማይታወቅ ነው የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጊጆ የገለጹልን። ሆኖም ግን ከ13 ዓመታት በፊት የዓለም ባንክ እና የዓለም የጤና ድርጅት በጋራ ያወጡት መረጃ ከመላው የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥር 17,6 በመቶው አካል ጉዳተኞች መሆናቸውን ይህም ማለት ከ20 ሚሊየን በላይ እንደማለት መሆኑንም አቶ አባይነህ አመልክተዋል።

በዚህ ስሌት መሠረት ወደ 20 ሚሊየን የሚሆን የአካል ጉዳተኛ ባለባት ኢትዮጵያ ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ የተለያዩ አገልግሎቶች ምን ያህል እነሱን ታሳቢ ያደረጉ ናቸው የሚለው በየጊዜው ዋነኛ መነጋገሪያ እንደሆነ ነው ያነጋገርናቸው ወገኖች የገለጹልን። ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተገናኘ ጥሩ ጥሩ ሕጎች እንዳሉ የገለጹልን ዓይነስውር መምህርት ተግባራዊነቱ ግን አሁንም ይቀራል ባይ ናቸው።

ቅጥርን በሚመለከት በአንዳንድ መሥሪያ ቤቶች በይፋ የሚነገር ሆኖም አካል ጉዳተኞችን ወደጎን የሚገፋ አሰራር እንደሚያጋጥም ሁሉ አንዳንዶቹ እንደውም ቅድሚያ የሚሰጡ መኖራቸውንም አንስተዋል።  

በሰው ሠራሽ አስተውህሎት የሚሠራ የዓይነስውር በትርምስል WeWALK

እሳቸው እንደሚሉት ለምሳሌ ሕንጻዎች የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው እንደሚገነቡ እየተነገረ፤ የእግር ጉዳት ያላቸው ወገኖች የሚንቀሳቀሱባቸውን ተሽከርካሪዎች ይዘው በአንዳንድ ወሳኝ ቦታዎች ካሰቡበት ለመድረስ የሚቸገሩበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም። በየመንገዱ ያለማመላከቻና መከለያ የሚከናወኑ ቁፋሮዎችም ለዓይነስውሮች ፈተናዎች መሆናቸው አልቀረም።

የአካል ጉዳተኞች የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮቶች ሊገነዘብ የሚችለው የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን በሚመለከት የወጡት ሕጎች የቆዩ መሆናቸውን ሆኖም አሁን የተሻሻለ ሕግ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ይናገራሉ ።

ሰዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ነው ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ,ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የታሰበውን የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልከት ይፋ የሆኑ የተመድ ዘገባዎች ያመለከቱት ነው። በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆናቸውም ተገልጿል። በጎርጎሪዮሳዊው 1992 ዓ,ም የተመድ በወሰነው መሠረት የአካል ጉዳተኞች ቀን በየዓመቱ ይታሰባል። የዘንድሮው መሪ ቃል የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ አቅም አጎልብተን የመሪነት ሚናቸውን እንዲጫወቱ በማስቻል ዘላቂ የልማት ግብን እናሳካለን የሚል ነው።

ሸዋዬ ለገሠ 

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW