የአክሱም ቅርሶች ለብልሽት ተጋልጠዋል
ዓርብ፣ ሐምሌ 14 2015
ሰሜን ኢትዮጵያ አክሱም ከተማና አካባቢዉ የሚገኙት የአክሱም ሐወልቶችና ሌሎች በርካታ ቅርሶች ባስቸኳይ ካልተጠገኑ በቀላሉ እንደሚበላሹ የአክሱም ከተማ ባለስልጣናት እና የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች አስታወቁ።ባለሙያዎች እንደሚሉት ሐዉልቶቹም ሆኑ ቅርሶቹ እንደሚጠገኑ ከዓመታት በፊት ቢነገርም እስካሁን አልተጠገኑም።ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ ጦርነት በተደረገበት ወቅት ከአክሱም ከተማ በርካታ ቅርሶች መዘረፋቸዉንም የከተማይቱ ባለስልጣናትና ባለሙያዎች አስታዉቀዋል።
ለዓመታት የጥገና ስራ ይደረግላቸዋል እየተባሉ የቆዩ የጥንታዊ ስልጣኔና ኪነ ህንፃ ማሳያ የሆኑ የአክሱም ሐወልቶች፥ እስካሁን ድረስ ጥገና አለማግኘታቸው ተከትሎ በከፍተኛ የመውደቅ አደጋ ላይ መሆናቸው የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ይገልፃሉ። በአክሱም ከተማ ተገኝተን እንደተመለከትነው፥ ሐወልቶቹን የተሸከመዉ እና ከስር ያለው ጥንታዊ የመቃብር ስፍራ በክረምት ዉሃና ሌሎች ምክንያቶች በስፋት ፈርሶ የሚታይ ሲሆን፥ ከዓመታት በፊት ከጦልያን የመጣው በባለሙያዎች ቁጥር ሶስት ተብሎ የሚታወቅ ሐወልት በብረት ምሶሶዎች ተደግፎ ዘሞ ይታያል። በአክሱም ቱሪዝም ፅሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ ባለሙያ አቶ አላይ ወልደስላሴ የአክሱም ሐወልቶች ከመውደቅ አደጋ ለመታደግ ተጀምሮ የነበረ የጥገና ቅድመ ዝግጀት በጦርነቱ ምክንያት መስተጓጎሉ የሚያነሱ ሲሆን፣ በዚህም ባለፉት ዓመታት የአደጋው መጠን በጅጉ ጨምሯል ብለዋል።
በተለይም በጦርነቱ ወቅት በሐወልቶቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የሚያነሱት የቅርስ ጥበቃ ባለሙያው አቶ አላይ ወልደስላሴ፥ ሐወልቶቹ በአስቸኳይ መጠገን አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑ ያስረዳሉ።
በዋነኝነት የሐወልቶቹ አስተዳደር እና ጥገና ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ልኡካን ወደ አክሱም በመላክ ያለው ሁኔታ መመልከቱ እንዲሁም ለዩኔስኮ የሚላክ የጥናት ውጤት መዘጋጀቱ ከአክሱም ቱሪዝም ቢሮ ሰምተናል። ከአክሱም ሐወልቶች በተጨማሪ በዓመት እስከ 25 ሺህ የሚገመቱ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ይመልከቱት ነበር የተባለው ከአክሱም ሐወልቶች አቅራብያ የሚገኝ ሙዝየም በበኩሉ በጦርነቱ ወቅት ተዘርፏል።
በሐወልቶቹ ጥገና ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል መንግስት ተቋም የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ ዳይሬክተሩ ብንደውልም ስልካቸውን ሊነሳ አልቻለም። የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ኮምኒኬሽን ሐላፊ የተባሉ ደግሞ "ከሐወልቶቹ ጥገና ጋር በተያያዘ ለግዜው ምንም አዲስ ነገር የለም፣ ሲኖር እናሳውቃለን" በማለት አጭር መልስ ሰጥተዋል። ባለፈው ግንቦት ወር በትግራይ ጉብኝት አድርገው የነበሩ በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር ጨምሮ ሌሎች ልኡካን በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የአክሱም ሐወልቶች ለመጠገን የሚደረግ ቅድመ ዝግጅት ለማስቀጠል እንደሚሰራ መናገራቸውን የክልሉ መንግስታዊ መገናኛ ብዙሐን ዘግበው ነበር።
ሚሊዮን ኃይለ ስላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር