የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፍያ ጥገና ተደረገለት
ሰኞ፣ ሰኔ 3 2016የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፍያ ጥገና ተደረገለት
በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት ወድመው የነበሩ እና ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቾች እየተመለሱ ነው። ትላንት በአክሱም የሚገኘው አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፍያ ጥገና ተደርጎለት የመጀመሪ በረራ አስተናግዷል። ዛሬ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ 4G የኢንተርኔት አገልግሎት በትግራይ በይፋ አስጀምሯል። የመንገዶች ግንባታ እና ጥገና በበርካታ የትግራይ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል።
በትግራዩ በጦርነት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው በክልሉ የሚገኙ ተቋማት መካከል በአክሱም ከተማ የሚገኘው አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፍያ አንዱ ነው። ይህ አውሮፕላን ማረፍያ በዋነኝነት በመንደርደሪያ ስፍራው በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ላለፉት አራት ገደማ ዓመታት ከስራ ውጭ ሆኑ፥ ከቱሪዝም በሚገኝ ገቢ በዋነኝነት የምትጠቀመው አክሱም ከተማም እንቅስቃሴዋ ተስተጓጉሎ ቆይቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዳስታወቀዉ 290 ሚልዮን ብር ወጪ አድርጎ የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፍያ አሳድሶ ትላንት ወደ ስራ የመለሰ ሲሆን ከ3 ዓመት ከ8 ወር በኃላ ደግሞ አውሮፕላን ማረፍያው ትላንት በረራ አስተናግዷል።
ከጦርነቱ በኃላ በትግራይ የወደሙ መሰረተ ልማቶች ግንባታ እየተከወነ ይገኛል። ከስራ ውጭ የነበሩ ጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች አድሶ ወደ መደበኛ ስራ መመለስ፣ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲሁም የውሃ እና ኤሌክትሪክ ዝርጋታ ተከውነዋል፥ በሂደት ላይ ያሉም አሉ። ከቴሌኮም አገልግሎት ጋር በተያያዘ በጦርነቱ ወቅት ተቋርጦ የነበረው አገልግሎት ከመቀጠል አልፎ፥ በኢትዮጵያ ስራ ከጀመረ የሰነበረው ሳፋሪኮም፥ በትግራይ የራሱ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዘርግቶ የመደበኛ ጥሪ እና የ4G ኢንተርኔት አገልግሎት በትግራይ ጀምሯል። ዛሬ በመቐለ በይፋ ስራ መጀመሩ ያስታወቁት የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ስራ አስፈፃሚ ዊም ቫንሄልፑት አስካሁን ባለው በትግራይ ለአንድ ሺህ ገደማ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩም አስታውቀዋል። ስራ አስፈፃሚው ዊም "በራሳችን 125 ታወሮች መገንባት ችለናል። ይህ በአጭር ግዜ በስድስት ወር ብቻ የተከወነ ነው። በትግራይ የዘረጋነው የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሰረተ ልማት ሙሉበሙሉ በራሳችን የተገነባ፣ ነፃ እና የሌላ ቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ጥገኛ የማያደርገን ነው" ብለዋል።
ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር በተያያዘ በመቐለ ጨምሮ በትግራይ የተለያዩ ከተሞች የአስፋልት መንገዶች ግንባታ በስፋት እየተከወኑ ነው። በመቐለ ዓመታት ያገለገሉ እና እጅግ አርጅተው የነበሩ የከተማዋ መንገዶች ፈርሰው ዳግም እየተገነቡ ይገኛሉ። በትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር የመሰረተ ልማት ካቢኔ ሴክሬታሪያት ወይዘሮ ያለም ፀጋይ የህዝቡ ጥያቄዎች ለመመለስ አስተዳደሩ ጥረት ላይ መሆኑ ያነሳሉ።
ወይዘሮ ያለም "ድርቅ እና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም ጭምር ካለው መስራት እንችላለን በሚል፣ ህዝብ ተባብሮ እየተሰራ ያለ እና ለሌላም ምሳሌ የሚሆን ነው። በውሃ፣ በመንገድ፣ ኤሌክትሪክ እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች የህዝብ ጥያቄ አለ። መንግስት ይህ ለመፍታት በቀጣይነት ይሰራል" ብለዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ