1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የኤርትራ ጦር ከትግራይ ይዉጣ» የአዉሮጳ ሕብረት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10 2016

የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ልኡክ የመሩት ሚስ ኢዛቤ ዋይዝለር በበኩላቸው አሁንም በትግራይ ያሉ የኤርትራ ሐይሎች እንዲወጡ፣ በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀመው ወንጀሎችም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ማድረግ የአውሮፖ ሕብረት ፓርላማ አቋም መሆኑ ገልፀዋል።

ብራስልስ የሚገኘዉ የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት
የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት-ብራስልስምስል Dwi Anoraganingrum/Future Image/IMAGO

የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ የአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት ጠየቀ

This browser does not support the audio element.

               

የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ አባላት በትግራዩ ጦርነት ወቅት ለተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ አስታወቁ።ትግራይን የጎበኙት  የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ልኡካን እንደሚሉት አሁንም በትግራይ ክልል የሰፈሩ  የኤርትራ ወታደሮችአካባቢዉን ለቅቀዉ መዉጣት አለባቸዉ።መልዕክተኞቹ መቀሌ ዉስጥ ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋልም።

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት የእስካሁን አፈፃፀም እና የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ለመታዘብ ትላንት በመቐለ የተገኙት የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ልኡካን ከትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በርካታ ነጥቦች መነሳታቸው የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ፅሕፈት ቤት አስታውቋል። የሰላም ስምምነቱ መሰረት ግጭት ቆሞ በትግራይ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑ ተስፋ ሰጪ መሆኑ በትግራይ ክልል አመራሮች በኩል ለአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ልኡካን የተገለፀ ሲሆን ይሁንና እስካሁን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው የሚመለሱበት ሁኔታ አለመመቻቸቱ፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ሐይሎች አሁንም ከተለያዩ የትግራይ ክፍሎች በውሉ መሰረት አለመውጣታቸው፣ የተለያዩ ታጣቂዎች ባሉበት እና የክልሉ የአስተዳደር መዋቅር ባልተዘረጋበት፥ በነዚሁ አካባቢዎች ሪፈረንደም የማድረግ ዝንባሌ በፌደራል መንግስቱ መታየቱ ተቀባይነት እንደሌለው ለሕብረቱ ፓርላማ ልኡካን መገለፁ ተነግሯል። 

የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ልኡክ የመሩት ሚስ ኢዛቤ ዋይዝለር በበኩላቸው አሁንም በትግራይ ያሉ የኤርትራ ሐይሎች እንዲወጡ፣ በጦርነቱ ወቅት ለተፈፀመው ወንጀሎችም ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ማድረግ የአውሮፖ ሕብረት ፓርላማ አቋም መሆኑ ገልፀዋል። ኢዛቤል ዋይዝለር "በአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ በኩል ያለው አቋም ግልፅ ነው። በሰሜን በኩል ያሉት የኤርትራ ሐይሎች ከተቆጣጠሩት ቦታ መውጣት አለባቸው። ሌላኛው አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ደግሞ አጥፊዎች መጠየቅ መቻል አለባቸው። የተጠያቂነት ጉዳይ አስፈላጊ ስለሆነ እንደ የሰብአዊ መብት ኮሚቴ በአትኩሮት የምንመለከተው ነው" ብለዋል።

አቶ ጌታቸዉ ረዳ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ ርዕሰ-መስተዳድርምስል Million Haileselassie/DW

ልኡኩን ያነጋገሩ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ የአውሮፖ ሕብረት በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ህዝብ ላይ ይፈፀም የነበረ ወንጀል በማውገዝ የያዘው አቋም በማድነቅ አመስግነዋል። አቶ ጌታቸው "በትግራዩ ጦርነት ወቅት፥ የአውሮፓ ሕብረት ተቋማት በአጠቃላይ፥ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ደግሞ በተለየ በህዝባችን ላይ ይፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎች በማውገዝ አቋም ይዛቹሃል። ወንጀሎቹ ከማውገዝ በተጨማሪ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ጠንካራ አቋም አንፀባርቋል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የሰላም ስምምነቱ በሙሉእነት እንዲተገበር በማገዝ ላይ የአውሮፓ ሕብረት ሚናው እንዲወጣ አቶ ጌታቸው ረዳ ጥሪ አቅርበዋል።"ዘላቂ ሰላም ፍላጎታችን ነው። ይህ እንዲሆን ያልተፈፀሙ ተግባራት ሊከወኑ ይገባል። በዚህ ጉዳይ ዙርያም የአውሮፓ ሕብረት ተቋማት ሚናቸው እንደሚወጡ ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

ከትምሕርት ቤትነት ወደ መጠለያ ጣቢያነት የተለወጠዉ ትምህርት ቤት-መቀሌምስል Million Hailesillassie/DW

በልዑኩ እና የትግራይ አስተዳደር ባለስልጣናት ውይይት ዙርያ ዝርዝር ፅሑፍ ያወጣው የትግራይ ፕሬዝደን ፅሕፈት ቤት ሰብአዊ ድጋፍ በመቋረጡ በትግራይ የቆየው ችግር እንዳባባሰው፣ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ስራ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እክል ገጥሞት እንዳለ ለአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ መገለፁ አውስቷል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW