1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ ጦር ከማሊ መዉጣት መጀመርና የሽብር ስጋት  

ቅዳሜ፣ የካቲት 12 2014

ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሃገር ማሊ ያሰፈረችዉን ጦር ማስወጣት መጀመርዋን አስታዉቃለች። በማሊ ሰፍረዉ የሚገኙ የአውሮጳ ወታደሮች ሀገሪቱን ጥለዉ መዉጣት መጀመር በሳህል ክልል አካባቢ ሃገራት ላይ የደህንነት አደጋ ስጋት መጨመሩን አመላካች ነዉ።

UN-Minusma Mali-Mission | Französische Truppen
ምስል Speich Frédéric/Maxppp/dpa/picture alliance

ፈረንሳይ በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሃገር ማሊ ያሰፈረችዉን ጦር ማስወጣት መጀመርዋን አስታዉቃለች። ጀርመን ጦርዋን ስለማስወጣት አለማስወጣትዋ እስካሁን ግልፅ አይደለም። እንድያም ሆኖ በማሊ ሰፍረዉ የሚገኙ የአውሮጳ ወታደሮች ሀገሪቱን ጥለዉ መዉጣት መጀመር በሳህል ክልል አካባቢ ሃገራት ላይ የደህንነት አደጋ ስጋት መጨመሩን አመላካች ነዉ። የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ከሳህል ሃገራት ጋር የበለጠ አንድነት እና ትብብር እንዲፈፀም ጠይቀዋል።
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት "በአፍሪቃ ሰላምና ደህንነት ከሌለ ዓለም ሰላምና ደህንነት አይኖረውም" ሲሉ ፈረንሳይ እና የአውሮጳ አጋሮቻቸው ወታደሮቻቸውን ከማሊ እንደሚያስወጡ ከማሳወቃቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ከ DW ጋር ባካሄዱት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል።
የወቅቱ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበር ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል"ዓለም አቀፍ በሚካሄደዉ በሽብር ላይ ጦርነት አፍሪቃ ቀላል ዒላማ እየሆነች ነው" ሲሉ አክለዋል። 
ፕሬዚዳንት ሳል በተጨማሪ በምዕራብ ሳህል ከሴኔጋል እና ከሞሪታንያ አንስቶ እስከ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኒጀር እና ቻድ ድረስ ባለው ሰፊ ከፊል በረሃማ ክልል እየተባባሰ ለመጣው ዓመፅና ጥቃት ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የሰጠውን ምላሽ ጥያቄ አንስተዉበታል። 
« በሶሪያና በሊቢያ ሽብርተኝነት ተሸነፈ፤ ከዝያም ወደ አፍሪቃ እተዛዋወረ መጣ። ይህ ርምጃ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚደረገው ትግል ደካማ እየሆነ መሄዱን ያሳያል። ወደ አፍጋኒስታን ስንመጣ ደግሞ ከ 100,000 በላይ ወታደሮችን ያሳተፈ ዓለም አቀፍ ጥምረት መገንባት ችለናል።»
ይሁን እንጂ አሉ ፕሬዚዳንቱ ይሁን እንጂ ከሳህል አካባቢ ሃገራት ጋር በተያያዘ ሁኔታዉ በጣም የተለየ ነው።
«ከአፍሪቃ፣ ከሳህል አካባቢ ሃገራት ጋር በተያያዘ፣ የበለጠ ድጋፍ እንዲኖር  እና  ጠንካራ  ተልዕኮ እንዲኖር ለማድረግ ለ10 ወይም ለ12 ዓመታት የደህንነት ምክር ቤቱን ስንደግፍ ቆይተናል። ማቋቋም ግን አልተቻለም። በተጨማሪም በአህጉሪቱ ሰላም ለማስፈንና ሰላም ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት በገንዘብ ለማገዝ እንቸገራለን።»
ፈረንሳይና የአዉሮጳ ተባባሪ ሃገራት ማሊ ዉስጥ ያሰፈሩትን ጦራቸዉን ከምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሃገር ማሊ ማስወጣት መጀመራቸዉን ያስታወቁት በዚሁ ሳምንት ሃሙስ ነዉ። ፈረንሳይና ተባባሪ የአዉሮጳ ሃገራት መንግስታት አሸባሪዎችን የሚወጋ በሽዎች የሚቆጠር ጦር ኃይል ማሊ ዉስጥ ካሰፈሩ አስር ዓመት ሊሆናቸዉ የቀራቸዉ ጥቂት ወራት ነዉ። የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ ከትናንት በስትያ ሃሙስ እለት እንዳllute እንዳሉት ጦሩ እስከ 6 ወራት ባለዉ ጊዜ ከማሊ ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ይወጣል።
«ሰሜናዊ ማሊ ዉስጥ የሚገኙ ጦር ሠፈሮችን መዝጋት ጀምረናል።በፍጥነት መዝጋታችንን እንቀጥላለን።ጦር ሰፈሮቹን ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት ከ4 እስከ 6 ወራት ጊዜ ይፈጃል።ጦር በሚወጣበት ወቅት አደጋ እንዳይደርስበት የሚከላከልና አወጣጡን የሚቀላጥፍ ኃይል እንመድባለን።ከዚሕም ጋር ማሊ ለሠፈረዉ ለተባበሩት መንግስታት ሠራዊት ድጋፍ መስጠታችንም ይቀጥላል።»
የፕሬዚዳንቱን መግለጫ ተከትሎ ወደ 300 የሚጠጉ የጀርመን ወታደሮችን ያካተተውን የአዉሮጳ ሕብረት የወታደራዊ ስልጠና ተልኮ « EUTM» (ኢዩቲም) የወደፊት ዕጣ ጥያቄ አስነስቶአል።

ምስል Kristin Palitza/dpa/picture alliance
ምስል Sarah Meyssonnier/AP Photo/picture alliance

የማሊ ወታደሮች ባለፈው ሚያዚያ ለሁለተኛ ጊዜ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን መያዛቸዉ የሚታወስ ነዉ። ወታደራዊዉ ሁንታ አመራር መጀመሪያ ላይ በጎርጎረሳዉያኑ የካቲት 2022 ዓ.ም  ምርጫ ለማካሄድ ከተስማሙ በኋላ ስልጣኑ ሲቪል መንግሥት የሚሸጋገርበት ጊዜ እንደሚያዘገይና በጎርጎረሳዉያኑ 2026 ዓ.ም ምርጫ ለማካሄድ ማቀዳቸዉን ማስታወቃቸዉ ይታወቃል።   

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ካትያ ኬውል ሃሙስ እለት ይፋ ባደረጉት መግለጫ የባማኮዉ መንግሥት ወደ ዲሞክራሲ ለመመለስ ሁነኛ ምልክት እያሳየ አይደለም። የማሊ የሽግግር መንግሥት የፓርላማ ጸሐፊ አማዱ ማይጋ ለረጅም ጊዜ አጋር የሆነችው ጀርመን በማሊ መገኘቷን እንደምትቀጥል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።  
«ማሊ እራሷን ዳግም ማግኘት፣ ራሷን ማሻሻል አለባት።  በሃገሪቱ የሚታየዉን ያለመረጋጋትም መዋጋት ይኖርባታል። ጀርመን ከወንድም ሃገር ማሊጎን ለረጅም ጊዜ ቆማ ስትረዳ ቆይታለች።» 
በአሁኑ ወቅት  ጀርመን በማሊ የተመድ ወታደራዊ ተልዕኮ ስር 1,020 ወታደሮች አሏት። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈረንሳይ ጦርዋን ወደ ኒጀር ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ለማዛወር እየፈለገች መሆንዋም ተመልክቶአል። 
ይሁንና ኒጀር ተጨማሪ የፈረንሳይ ወታደሮችን መቀበል ለኒጀር ፕሬዚደንት ሞሐመድ ባዙም አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የመብት ተሟጋች ሙሳ ታቻንጋሪ ያስጠነቅቃሉ።

ምስል Etat-major des armées / France

«አዳዲስ የውጭ አገር ወታደሮችን አምኖ መቀበላቸው ለፕሬዘዳንት ሞሐመድ ባዙም ለአደጋ ሊያጋልጣቸዉ ይችላል። አገዛዙ ይህን መልሶ የማደራጀት ሥራ ከተቀበለ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ጦር ሰራዊቱ  በሳህል እና በአጠቃላይ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት  ወደ ስልጣን መምጣቱ አካባቢዉ ላይ ያለመረጋጋት እና ቀጣይ የህልዉና አደጋ መደቀኑን እያየን ነዉ።» 

በሳህል የኒጀር መንግስታት ድርጅት የሰላምና ደህንነት ተግባር መሪ መሃማዱ አይድደር አልጋቢድ እንደሚሉት ደግሞ የተልዕኮ ጦር ሰራዊትን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማጣወሩ  "በእሳቱ ላይ ነዳጅ መጨመር" ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።

ምስል Blondet Eliot/ABACA/picture alliance

"እንዲህ ያለው ወታደሮችን ከቦታ ማንሳት ጉዳይ በእሳት ላይ ነዳጅ የመጨመር ርምጃ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ ቀደም ሲል በተዛቡ መረጃዎች የተመረዘውን አካባቢ ይበልጥ ሊያቀጣጥለው ይችላል።" 
ፈረንሳይና ተባባሪ የአዉሮጳ ሃገራት  ጦራቸዉን አሁን ከማሊ ለማስወጣት የወሰኑት  የማሊን ስልጣን በመፈንቅለ መንግሥት የተቆጣጠረዉ ከወታደራዊ ሁንታና ደጋፊዎቹ ከሆኑት የሃገሪቱ ሕዝብ ከፍተኛ ተቃዉሞ ስለገጠማቸዉ ነዉ።

አዜብ ታደሰ 
ሸዋዩ ለገሠ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW