የአዉሮጳ ፊልም ፊስቲቫል በአዲስ አበባ
ሐሙስ፣ ጥር 29 2017
የአዉሮጳ ፊልም ፊስቲቫል አዲስ አበባ ላይ በድምቀት እየተካሄደ ነዉ
«የአውሮጳ ፊልም ፌስቲቫል፤ በየዓመቱ ሳይቋረጥ አዲስ አበባ ዉስጥ የተካሄደ ረጅሙ የፊልም ፌስቲቫል ነዉ ብለን እናምናለን። በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት እንኳ የአውሮጳ ፊልም ፌስቲቫል አዲስ አበባ ላይ ሳይቋረጥ ተካሂዷል። ይህ የፊልም ፊስቲቫል በየዓመቱ የሚካሄደዉ፤ የባህል ልዉዉጥን ለማድረግ፤ የአዉሮጳ ፊልሞችን ለኢትዮጵያዉያን ተመልካቾች ለማሳየት ነዉ።» ይህን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት በአውሮጳ ሕብረት ተልዕኮ፤ የአፍሪቃ ሕብረት የፕሬስ ባለሙያ አቶ ብሩክ ፈለቀ ናቸዉ።
የዘንድሮዉ የአውሮጳ ፊልም ፌስቲቫል ከአርብ ከጥር 23 ቀን 2017 ዓ . ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ሳምንታት በአዲስ አበባ ላይ መካሄድ ጀምሯል። የዘንድሮዉ የጎርጎረሳዉያን 2025 ዓመት የአውሮጳ ሕብረት እና ኢትዮጵያ ግንኙነት የጀመሩበት 50ኛ ዓመት የሆነበት እንዲሁም የአውሮጳ ሕብረት እና የአፍሪቃ ሕብረት ግንኙነት የጀመሩበት 25ኛ ዓመት የሞላበት በመሆኑ ኹነቱ በልዩ ኹኔታ እንዲከበር ምክንያት እንደሆነም ተመልክቷል።
በአውሮጳ ሕብረት ተልዕኮ የአፍሪቃ ሕብረት የፕሬስ ባለሙያ አቶ ብሩክ ፈለቀ ለዶቼ ቬለ የባህል ዝግጅት ክፍል እንደተናገሩት፤ አዲስ አበባ ላይ ለአምስት ሳምንት በሚቀጥለዉ የፊልም መድረክ ላይ ሁለት የኢትዮጵያ ፊልሞችን ጨምሮ 27 ከተተያዩ የአውሮጳ አገራት የመጡ ፊልሞች አዲስ አበባ በሚገኙት የጣልያን እና የፈረንሳይ የባህል ማዕከላት ለእይታ ይቀርባሉ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዚህ ዝግጅት አንዱ አጋር ሲሆን የፊልም ፊስቲቫሉ መክፈቻ ሥነ-ስርዓት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ ላይ መከበሩ ተመልክቷል። ይህ የአውሮጳ የፌልም ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት በየዓመቱ ተዘጋጅቷል ያሉት በአውሮጳ ሕብረት ተልዕኮ የአፍሪቃ ሕብረት የፕሬስ ባለሙያ አቶ ብሩክ ፈለቀ፤ የዘንድሮዉ ዝጅት ግን ከሌሎች ዓመታት ልዩ የሚያደርገዉ እዉነታ እንዳለ ገልፀዋል።
አቶ ብሩክ ፈለቀ፤ ይህ አዲስ አበባ ላይ ላለፉት 20 ዓመታት ሳይቋረጥ ተካሂዷል ያሉት የአዉሮጳ የፊልም ፌስቲቫል፤ ታዋቂ መሆኑንም ተናግረዋል። ለአምስት ሳምንታት የሚቀጥለዉ የአዉሮጳ የፊልም መድረክ በተለይ የልምድ እና የባህል ልዉዉጥ፤ ብሎም ትስስርን ለመፍጠር እንደሚካሄድ ገልፀዋል። ና መድረኩ የት ነዉ። ማለቴ የፊልም ፊስቲቫሉ።
በመክፈቻ ሥነ-ስርዓቱ ላይ አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ለዶቼ ቬለ የሰጡት በአውሮጳ ሕብረት የአፍሪቃ ሕብረት ልዑክ መሪ፤ አምባሳደር ያቪየር ኒኖ የፊልም መድረኩ ጠቃሚ ዝግጅት ነዉ ብለዉታል።
«ይህ በፖለቲካዉ ፤ በሥነ-ጥበቡ ብሎም ስሜታዊ ሁኔታዎችን ያካተተ በጣም ጠቃሚ ዝግጅት ነዉ እላለሁ። ዘንድሮ የአዉሮጳ ፊልም ፊስቲቫል ሲዘጋጅ ለ 20ኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ። በዚህ ዓመት ከአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት እና ከአራት የእንግዳ አጋር አገሮች የተዉጣጡ 28 ፊልሞችን እናሳያለን። ይህን እያደረግን ያለነው ፤ ፊልም፤ በተሻለ መንገድ የእርስ በእርስ መግባባትን፤ ያጎለብታል፤ በጋራ እንድንሰራ ለማበረታታት አቅም ይሰጣል ብለን አጥብቀን ስለምናምን ነው።»
ምስቅልቅ በበዛበት በዛሬዉ ዓለም፤ ይህ የጥበብ መድረክ አንድነታችን የሚያሳይ ነዉ ሲሉ፤ በአውሮጳ ሕብረት የአፍሪቃ ሕብረት ልዑክ መሪ፤ አምባሳደር ያቪየር ኒኖ አክለዋል።
«በኢትዮጵያም ሆነ በስፔን፣ በአውስትራሊያም ሆነ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በሰዎች ላይ የሚደርሰው መከራ፣ የሰው ልዶች የደስታ ስሜት እና ተስፋ፣ ብሎም የብስጭት ስሜት አንድ ዓይነት መሆኑን እንረዳለን። እንዳልኩት ፊልሞች ይህን እንድንረዳ ወይም በቀላል መንገድ ለማስረዳት አቅም አላቸዉ። በዓለማችን አሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች በብዙ ቦታዎች ጦርነት መኖሩን፣ የንግድ እና የኤኮኖሚ ስጋት መከሰቱን በስጋት ያስባሉ። እና በዚህ የፊልም ፊስቲቫል ሁላችንም አንድ ላይ ነን ማለት እንፈልጋለን።»
አምባሳደር ያቪየር ኒኖ ይህን ሲሉ ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ የአዉሮጳ ተቋማትን ሁሉ እንደሆነ ዘርዝረዋል።
«ይህ የአውሮጳ ሕብረት ፤ አባል አገሮችን፣ የጣሊያን የባህል ተቋምን ፣ የፍራንኮ-ኢትዮጵያ ጥምረትን፣ የጀርመኑ የጎተ-ተቋምን፣ ሰርቫንቴስ-ተቋምን፣ ፖርቱጋል እና የጀርመን ማዕከላትን ሁሉ ያካትታል፣ ። ስለዚህ ሁላችንም በጋራ ሰዎችን ከሰዎች ለማስተሳሰር እንሞክራለን። ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ለምሳሌ በፊልም መድረኮች፤ በፌንድቃ ባህላዊ የሙዚቃ መድረክ ወይም ዉብ በሆኑትየኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብመድረኮች የእርስ በርስ መግባባትን እንፈጥራለን።»
አዲስ አበባ ላይ ለአምስት ሳምንታት በሚዘልቀዉ በአዉሮጳ የፊልም ፊስቲቫል ላይ የኢትዮጵያ የፊልም ባለሞያዎች ይሳተፋሉ፤ ሁለት የኢትዮጵያ ፊልሞች እንደሚቀርቡ በአውሮጳ ሕብረት ተልዕኮ የአፍሪቃ ሕብረት የፕሬስ ባለሙያ አቶ ብሩክ ፈለቀ ተናግረዋል።
አቶ ብሩክ ፈለቀ፤ በፊልም ፊስቲቫሉ ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ዲፕሎማቶች፤ ታዋቂ አትሌቶች በተለይ በመክፈቻ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተገኙ አቶ ብሩክ ተናግረዋል። በእርግጥ በፊልም ጥበቡ ረገድ ከአዉሮጳ ሃገራት ለልምድ ለባህል ልዉዉጥ የሚመጡት ፊልሞች ጥሩ ቢሆንም ቅሉ፤ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዉያን የተሰሩ ፊልሞችን፤ ተቋሙ ለአዉሮጳዉያን ለማስተዋቅ ወደ አዉሮጳ ሃገራት ይዞ የሚሄድበት መንገድ እስካሁን እንደሌለ ተናግረዋል። ይሁንና እንደ ብሩክ ፈለቀ፤ ይህ አይነቱ ጥያቄ በፊልም ፊስቲቫል መድረኩ ላይ መቅረቡን እና ጥሩ ሃሳብ እንደሆነም ተናግረዋል።
ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ