1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ሺዎችን አፈናቀለ፤ ቤትና ሰብልም አጠፋ

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 1 2017

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሰበታ ሀዋስ ወረዳ አዋሽ በሎ ነዋሪ የሆኑት እመጫት እናት በአከባቢው ካሉ መኖሪያ ቤቶች አንዱም ሳይቀር በወጣው የአዋሽ ወንዝ ሙላት ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በደጃፋቸው አስፓልት ዳር በተወጠረ ሸራ ውስጥ አራስ ልጃቸውን ይዘው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ተመልክተናቸዋል

የአዋሽ ወንዝ ካጥለቀለቃቸዉ አካባቢዎች አንዱ።ወንዙ አለቅጥ ሞልቶ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አራት ወረዳዎችን በማጥለቅለቁ ወደ 10 ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ አፈናቀለ
የአዋሽ ወንዝ ካጥለቀለቃቸዉ አካባቢዎች አንዱ።ወንዙ አለቅጥ ሞልቶ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ አራት ወረዳዎችን በማጥለቅለቁ ወደ 10 ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ አፈናቀለምስል፦ Seyoum Getu/DW

የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ሺዎችን አፈናቀለ፤ ቤትና ሰብልም አጠፋ

This browser does not support the audio element.


የአዋሽ ወንዝ አለቅጥ ሞልቶ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሶስት ወረዳ እና በምዕራብ ሸዋ ዞን አንድ ወረዳን ማጥለቅለቁ ተነግሯል፡፡ባለፈዉ ቅሳሜ ሌሊት ገደፉን ጦሶ የወጣዉ ዉኃ በአራቱ ወረዳዎች በሰብል የተሸፈኑ ማሳዎችን አጥለቅልቋል።በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤታቸው አፈናቅሏልም።በአደጋዉ ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳደር አስታዉቋል።

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የሰበታ ሀዋስ ወረዳ አዋሽ በሎ ነዋሪ የሆኑት እመጫት እናት በአከባቢው ካሉ መኖሪያ ቤቶች አንዱም ሳይቀር በወጣው የአዋሽ ወንዝ ሙላት ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በደጃፋቸው አስፓልት ዳር በተወጠረ ሸራ ውስጥ አራስ ልጃቸውን ይዘው ወዲያ ወዲህ ሲሉ ተመልክተናቸዋል፡፡ እንደሳቸው ቤታቸው በውሃ በመሙላቱ መኖሪያቸውን ለውሃ ትተው የወጡ ሁሉ ምግብ እንኳ የሚያበስሉባቸው ማዕድ ቤታቸው በውሃው ብዛት ተውጧልና ደጅ ወጥተው ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ በሚወስድ አውራጎዳና አስፓልት አጠገብ ምግባቸውን ለማብሰል ተገደዋል፡፡
የአዋሽ በሎ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ፤ “አዋሽ በዚህ ደረጃ የመጣብን አሁን ከአምስት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ውሃው ሌሊት ስምንት ሰዓት ነው ሰብሮ ቤታችን የገባው፡፡ እንደምትመለከተው ከዚህ የምንወጣበት ምንም አቅም የለም፡፡ ከብቶች ብቻ ነው ያወጣን እህል እንኳ ለማውጣት ጊዜ አልሰጠንምና ቤታችን ፈራርሶ ሰው መንገድ ላይ ወጥቷል” ብለዋል፡፡

ሌላኛውም አስተያየት ሰጪ ቀጠሉ፤ “ሰው ሁሉ በዚህ መንገድ ላይ ነው በጣም ተቸግሯል፡፡ የሚበላ የለም፡፡ ለከብቶች የሚሰጥ ገለባ እንኳ የለም በውሃው ተውጧል፡፡ አሁን ከአምስት ዓመት በኋላ ነው እንዲህ ሞልቶ ሰብሮ የገባብን በጣብ ከባድ ችግር ነው” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ብርሃኑ መራዊ የሚባሉ የአዋሽ በሎ ገበሬ ማህበር አስተያየት ሰጪ በፊናቸው ወንዙ የሚፈስበት ቦይ በወቅቱ አለመጠገን ለደረሰባቸው ችግር ምክንያት ነው ይላሉ፡፡ “ይህ የአዋሽ ውሃ ዛሬ አይደለም ይህን ችግር ማድረስ የጀመረው፡፡ በተፋሰስም የታወቀ ስለሆነ ሰኔና ሃምሌ ላይ እየመጡ ከመነካካት ይልቅ ወንዙ ውሃ ሳይዝ ብሰራ በቂ አፈር ስለሚያገኙ ቶሎ መጠገን ነበረበት፡፡ አሁን እንዳለ አስፓልት መንገድ ላይ ነው ለአዳራችንም ያለነው” በማለት የችግሩን ክብደት ገልጸዋልም፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በተሰራው የወንዙን ቦይ የመጠገን ስራ ላለፉት አምስት ዓመታት ወንዙ ማህበረሰቡ ላይ ጉዳት ስያደርስ እንዳልነበር ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ ወ/ሮ ኤቢሴ ተርፋ፤ ዘንድሮም የአዋሽ ተፋሰስ ድርጅት ጥገናውን ብያደርግም ውሃ ሙላቱ ግን ከፍተኛ በመሆኑ ወንዙ ተፈጥሯዊ ማፋሰሻውን ሰብሮ በመውጣት ጉዳት አድርሷል ነው ያሉት፡፡ 
ቅዳሜ ሌሊት 8፡00 ሰዓት ወንዙ ሰብሮ በመውጣት አከባቢውን ማጥለቅለቁን ተከትሎ ከእሁድ ጀምሮ የነፍስ አድን ርብርብ ማድረግ መጀመሩንም በመግለጽ፤ እስካሁን ከንብረት ውጪ ሰው ላይ ብያንስ የሞት አደጋ አለመከሰቱን ገልጸዋልም፡፡ ከምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄርሳ ለፎ በተጨማሪ በዚህ ዞን ሶስት ወረዳዎች በውሃ ማጥለቅለቁ መጎዳታቸውን አክለዋል፡፡ “ችግሩ ያለው ሶስቱ ወረዳ ላይ ነው፡፡ ዳዎ፣ ሰበታ ሀዋስ እና ኢሉ ወረዳዎች፡፡ አሁን የፈደራል መንግስትም ትኩረት ሰጥቶት የአገር መከላከያ ትናት በጀልባ ሰዎችን ስያወጣ ነው የዋለው፡፡ ሰዎችን ወደ ትምህርት ቤቶች እና ከተማ እያስጠለልን ነው፡፡ የምግብና ውሃ አቅርቦትም እየተደረገ ቢሆንም ይህ ግን በቀጣይ የሁሉም ትብብር የሚፈልግ ነው፡፡ ጥገና ተደርጎ ውሃውን ወደ ተፈጥሯዊ ማፋሰሻው ለመመለስም ማሽን ይመጣል ተብሎ እየጠብቅን ነው” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የአዋሽ ወንዝ ካጥለቀለቃቸዉ አካባቢዎች አንዱ።ነዋሪዎች እንዳሉት የአዋሽ ወንዝ በኦሮሚያ ክልል በርካታ አካባቢዎችን ሲያጥለቀልቅ ከአምስት ዓመት ወዲሕ የዘንድሮዉ ከፍተኛዉ ነዉምስል፦ Seyoum Getu/DW

በኢሉ ወረዳ ብቻ ከዘጠኝ ሺኅ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ያረጋገጡት ሃላፊዋ በሰበታ ሀዋስ እና ዳዎ ወረዳም አስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ብለዩም ቁጥሩ ግን ከቀን ቀን እየጨመረ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ፀሐይ ጫኔ 
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW