የአውሮጳ ህብረትና የቱኒዝያ ስምምነት
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 11 2015
የአውሮፓ ህብረት ከቱኒዚያ ጋር በዋናነት የሜዲትራኒያን ባህር አቁርጠው ወደ አውሮጳ የሚገቡትን ስደተኖችን ለመቆጣጠርና በሰው አዘዋዋሪ ወንጀለኞች ላይም እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የ200 ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ስምምነት ከቱኒዚያ ጋር ተፈራርሟል። ከዚህ ውስጥ 112ቱ ሚዮን ዩሮሮ ለድንበር ቁጥጥርና ጥበቃ ሲሆን፤ ሌላው ለቱኒዚያ ኢኮኖሚና የትምህርት ፕሮግርሞች መርጃ የሚሆን ነው ተብሏል። የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሪዝዳንት ኡርሱላ ቮንዴርለየን ስምምንነቱን የፈረሙትና የእርዳታውን መጠን ያስታወቁት ባለፈው ዕሁድ ከኔዘርላንድስና ጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር ቱኒዚያን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ በጎበኙበት ወቅት ነው። ወይዘሮ ፎንዴርሌየን በዚሁ ስነስራት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ እርዳታው ለሁለቱ ወገኖች የወደፊት የጋራ ዕድገት የሚውል መዋዕለ ንዋይ ወይም ኢንቨስትመንት ነው” በማለት ቱንዚያያና የአውሮፓ ህብረት በጋራ ታሪክና ጆግራፊ የተሳሳሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የአውሮፓ ህብረት በባህርም ይሁን በምድር የአውሮፓ ህብረትን ደንበር ጥሰው የሚገቡትን ስደተኖች ለመቆጣጠር የድንበር ጥበቃውን ማጠናከርና ክጎረቤት አገሮች ጋር ልዩ ትብብር ማድረግ ያለበት መሆኑን ከሚገፉት የአባል መንግስታት አገሮች መሪዎች ውስጥ ናቸው የሚባሉት የኔዘርላድስና የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትሮችም በዚሁ ወቅት በየብኩላቸው ስምምነቱን አድንቀው ወደ ህብረቱ የሚገቡትን ስደተኖች ለመግታት የሚያስችል እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በተለይ ጣሊያን የሜዲትራኒያን ባህርን በአደገኛ ሁኔታ በጀልባ አቋርጠው ወደ ህብረቱ የሚገቡ ስደተኖች ዋና መዳረሻ መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን፤ በዚህ አመት፤ ከጥር እስከ ሀምሌ ወር ድረስ ብቻ 75 ሺ ስልሳ አምስት ስደተኞች በዚሁ መንገድ እንደገቡ ተገልጿል። ይህ ቁጥርም ባለፈው አመት በተመሳሳይ ግዜ ከነበረው በእጥፍ የሚበልጥ ነው ተብሏል። ጸረ ሰደተኞች ከሆኑ ፓርቲዎች እንደመጡ የሚጠቀሱት የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስተር ሜሎኒ የድንበር ቍጥጥር ለማጥበቅ ብቻ ሳይሆን ስደተኞችን ወደ መጡባቸው ወይም ሌሎች ሶስተኛ አገሮች ለመመለስ ጭምር በተለየ ሁኔታ እንደሚሰሩ ነው የሚነገረው። ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለዚህ አላማቸው ከቱኒዚያና ሌሎች የህብረቱ አዋሳኝ አገሮች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን እየፈጠሩ ነው ይተባለ ሲሆን፤ በሚቀጥለው ዕሁድም ፕሬዝዳንት ሳይድን ጨምሮ ሌሎች መሪዎች የሚሳተፉበት በስደተኞች ጉዳይ የሚነጋገር ጉባኤ በሮም የሚካሄድ መሆኑን መናገራቸው ተገልጿል።
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የአውሮጳ ህብረትና አባል አገሮቹ በስደተኞች ጉዳይ ከአዋሳኝ አገሮች ጋር የሚያደርጓቸው ስምምነቶችና የሚፈራረሙዋቸው ውሎች፤ የስደተኞችን መብቶችና የአለማቀፍ ህግን የሚጥሱ ስለመሆናቸው ነው በሰፊው የሚነገረስ። የሰብአዊ መብትና የስደተኞች ድርጅቶች ያውሮፓ ህብረት በተለይ እንደ ሊቢያና ቱኒዚያ ከመሳሰሉ ስደተኞችን ቁምስቅል ከሚያሳዩ መንግስታት ጋር ስምምነት ማድረጋቸውን አጥብቀው አውግዘውታል። ታሪክ ሜጌርሲሲ የተባሉ በስደተኞች ጉዳይ ተመራማሪ ባለሙያ እንደሚሉት፤ ከቱንዚያም ሆነ ከሊሎች ጋር ስደተኞችን ለመቆጣጠር ስምምነት ማድረግ ችግሩን ያባብሰው ካልሆነ አያቃለውም ። “ የአውሮፓ ህብረት የስደተኖችን ጉዳይ እንዲይዙላቸው እራሳቸው የስደተኞችን መብት በመጣስ ለሚውገዙትና አቅሙና ፍላጎቱም ለሌላቸው እንደ ቱኒዝያና ሊቢያ ለመሳሰሉት አገሮች ከመስጠት ይልቅ፤ ህብረቱና አባል አገሮች እራሳቸው ጉዳዩን ቢይዙት ይሻል ነበር በማለት ህብረቱ ከቱኒዚያ ጋር ያደርገውን ስምምነት ነቅፈውታል።
የቱኒዚያ ተቃውሚዎችም፤ አገራቸውን ወደ አምባገነናዊ ስርዓት እየቀየሯት ነው የሚሏቸውን ፕሬዝዳንት ካይስ ሳይድን ከአውሮፓ በሚገኝ ገንዝብ ቱኒዚያን የድንበር ጠባቂ ዘብ እያደረጓት ነው በማለት ሲተቿቸው ተሰምቷል።
ገበያው ንጉሴ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር