1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረትና የአፍሪቃ ህብረት አጋርነት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 18 2012

ባለፈው የካቲት በአዲስ አበባ በተካሄደው የአውሮጳና የአፍሪቃ ህብረቶች 10ኛው የጋራ ምክክር ጉባኤ፣የአውሮጳ ኮሚሽን "አፍሪካን ከጦር መሳሪያ ድምጽ ነፃ ለማድረግ፣ሰላማዊት አፍሪቃን ለመገንባትና በአፍሪቃ ህብረት አባላት የተጀመረው ስራ እንዲሳካ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቶ ነበር:: ያ ግን በኮረና ምክንያት በሁሉም እየተተገበረ አይደለም

Äthiopien Addis Abeba Gipfeltreffen der Staatschefs der Afrikanischen Union
ምስል DW/M. Strauß

የአውሮጳ ህብረትና የአፍሪቃ ህብረት አዲስ አጋርነት ተስፋ

This browser does not support the audio element.

 

ባለፈው የካቲት ወር በአዲስ አበባ የአፍሪቃ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የተካሄደው 10ኛው የአውሮጳና የአፍሪቃ ህብረቶች የጋራ የምክክር መድረክ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2017 ዓ.ም ሁለቱ ህብረቶች በኮትዲቯሯ የወደብ ከተማ አቢጃን ላይ የደረሱበትን የጋራ ስምምነት ይኸውም በአፍሪቃ ዘላቂነት ያለው ዕድገትን ለማምጣት፣ በአህጉራቱ መካከል ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር ፣በቀጣናው ፀጥታና ደህንነት ፣በህገወጥ የስደተኞች ዝውውርና በአየር ፀባይ ለውጥ ዙሪያ የተደረሱትን ስምምነቶች ወደላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግና አዲሱን የንግድና የፖለቲካ አጋርነት ለማጠናከር ያለመ ነበር:: ጉባኤው በተለይም ካለፉት 13 ዓመታት ወዲህ በሰላምና ፀጥታ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንቅስቃሴ መከላከል፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትላቸው የጎርፍና የድርቅ ክስተቶች እንዲሁም የበረሃማነት መስፋፋት ችግሮች አፈታት፣በተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሌሎች የትብብር መስኮች በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሶ አፍሪቃውያን አሁን ላይ በጅማሮ ላይ የሚገኙትን የነፃ የንግድ ቀጣና ስርዓት እንቅስቃሴ ለማጠናከርና ለወጣቱ ትውልድ ተጨማሪ አማራጭ የስራ ዕድሎችን ለማመቻቸት በተጨማሪም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት የአውሮጳ ህብረት ድጋፍና አጋርነት ወሳኝ መሆኑ ማስገንዘቡ አይዘነጋም::

የመጀመሪያዋ ሴት የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ዴር ላየን ባለፈው የአውሮጳውያን ዓመት ማብቂያ ወደ ስልጣን ከመጡ ከ100 ቀናት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አፍሪቃ በመጓዝ ከሃያ የሚልቁ የኮሚሽኑን የልዑካን ቡድን አባላት መርተው በታደሙበት የአዲስ አበባው የአፍሪቃ ኮሚሽን ስብሰባ "ለአፍሪቃ ሁለንተናዊና ዘላቂነት ያለው እድገት መረጋገጥ በቅድሚያ ሰላማዊ አፍሪካን መገንባት" አስፈላጊ ነው ሲሉ በወቅቱ ገልፀው ነበር:: ፕሬዝዳንቷ በሁለቱ ህብረቶች መካከል ከአሁን ቀደም የነበረውን አጋርነት በተሻለ ሁኔታ የሚያጠናክር አዲስ ዕቅድ ይዘው መምጣታቸውንም ነበር አፅንዖት ሰጠተው በጉባኤው ላይ የተናገሩት:: ጋዜጠኛ ስትራውስ እንዳለችው " ፕሬዝዳንቷ ሁለቱንም ስብሰባዎች የአፍሪቃ አህጉር ለእርሳቸው ምን ያህል እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆነ ለማስረዳት በሚገባ ተጠቅመውበታል" ብላለች:: ይኸው የየካቲቱ የአዲስ አበባው ጉባኤ የሁለቱን ህብረቶች አዲስ የአጋርነት ስትራቴጂ ለማጠናከር በዚህ በግንቦት ወር ሩዋንዳ ኪጋሊ ውስጥ የአፍሪቃ ህብረትና የአውሮጳ ህብረትን የሚኒስትሮች ቀጣይ ስብሰባ ለማካሄድ ወስኖ ነበር::ከአውሮጳ ህብረት ዕይታ አንፃር ይህ ስትራቴጂ በዘንድሮው የፈረንጆቹ ዓመት ማገባደጃ አቅራቢያ ጥቅምት ወር ላይ በቤልጅየም ብራስልስ ይካሄዳል ለተባለውና ልዩ ልዩ ጠቃሚ ውሳኔዎች ያሳልፋል ተብሎ ለተወጠነው ቀጣዩ የአውሮጳና አፍሪቃ ህብረቶች የጋራ ጉባኤ ረጅም ጉዞ የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው ተብሎ ታምኖበታል:: ህብረቶቹ በኮሚሽኖችና በሚኒስትሮች ደረጃ በሁለቱም አህጉሮች የጋራ ጥቅምና ፍላጎቶች ላይ የተመሰረቱ ልዩ ልዩ ውይይቶና ምክክሮችም ላለፍትት ዓመታት ሲካሄዱ ቆይተዋል::ሆኖም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ሌላውን እንቅስቃሴ እንዳስተጓጎለው ሁሉ በሽታውን ተከትሎ በሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ በተጣለው እግድ ምክንያት ጉባኤውንም ለሌላ ጊዜ እንዲዛወር አስገድዷል::በመሰረቱ የሁለቱ አህጉራት አጋርነት ለሁለቱም ወገኖች እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ መሆኑን ማንም አይክድም:: ሆኖም ዋናው ጥያቄ የአህጉራቱ ተወካዮች እንዴት በፍጥነት ሥራቸውን መቀጠል ይችላሉ የሚለው ነው:: ብራስልስ የሚገኘው የአውሮጳውያን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ቡድን "ቲንክ-ታንክ" ዋና ሃላፊ ጌርት ላፖርቴ እንደሚሉት "በአውሮጳ ህብረት በኩል ስትራቴጂውን ወደፊት ለመግፋትና ለማስፈፀም ፍላጎት ያላቸው አሉ ::በሌላ ወገን ደግሞ የኮረና ወረርሽኝ ቀውስ ዳግም እንዲጤን የሚጠይቁም ይገኙበታል:: ከዚህ ሁሉ በተቃራኒው አዲስ ነው የተባለው የትብብር ስትራቴጂ ገና ከጅምሩ አሮጌና ጊዜ ያለፈበት ነው ሲሉ የሚሞግቱም መኖራቸው መታወቅ ይኖርበታል" በማለት ይገልፃሉ::

ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/M. Wondimu Hailu

ካለፈው የአውሮጳውያን ዓመት ታህሳስ ወር ጀምሮ ኮረና ዓለምን ያስጨነቀ ከባድ የጤና ወረርሽኝ እንደመሆኑ መጠን መላው የዓለም ማህበረሰብ ይህን ወረርሽኝ በመከላከሉ ተግባር ላይ ርብርብ በሚያደርግበት በአሁኑ ወቅት የአውሮጳ ህብረት ስትራቴጂና አጀንዳ ጊዜው አልፎበታል በሚለው ፅንሰ ሃሳብ ላይ የህብረቱ አባል ሀገራት ትኩረት ሰጥተው ያጤኑታል ተብሎ እንደማይታሰብም ተገልጿል:: በአንፃሩ በአፍሪቃ ሀገራት በኩል ከአውሮጳ ህብረት ጋር ያላቸውን ቀጣይ ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር አራት መሰረታዊ አንኳር ጉዳዮችን በቀዳሚነት ማስቀመጣቸው ታውቋል:: እነሱም የንግድ ትብብር፣ ህገወጥ የህዝቦች ፍልሰት፣ ፀጥታና ደህንነት እንዲሁም የአየር ፀባይ ለውጥ የሚሉት መሰረታዊ የትብብር አጀንዳዎች ሲሆን እነዚህም በአውሮጳ ህብረት ጭምር ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው:: በአውሮጳ ህብረት ጉዳዮች የአፍሪቃ ህብረት አማካሪ የሆኑት ፋቴን አጋድ በበኩላቸው የሁለቱ  ህብረቶች ስምምነት ከላይ ሲያዩት ቀላል የሚመስል ግን ደግሞ ውስጡ ብዙ ምስጢራዊ፣ የተደበቁና ውስብስብ ጉዳዮች ያሉበት መሆኑን ያስረዳሉ:: ለአብነትም የንግድ ትብብር ስምምነቶችን ያየን እንደሁ አውሮጳና አፍሪቃ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ትብብር እንደሚያስፈልጋቸው ያምናሉ:: አቀራረቡና አፈፃፀም ላይ ያየን እንደሁ ግን ፍፁም ከዚህ ተቃራኒ ሆኖ ነው የምናየው ሲሉ አስረድተዋል:: አፍሪቃ አህጉር በአሁኑ ወቅት ቀዳሚ ትኩረት የሰጠችው በ 54ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት መካከል ከስምምነት ለተደረሰበትና በመጪው ሀምሌ ወር በይፋ ይጀመራል ተብሎ ለታቀደው ፣ ለሚልዮኖች አፍሪቃውያን ተጨማሪ የስራ ዕድል ይፈጥራል ፈጣን የምጣኔ ሃብት ዕድገትንም ያስገኛል የሚል ዕምነትን ላሳደረው ግዙፉ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና መርሃግብር እንቅስቃሴ ቢሆንም በኮቪድ-19 ቀውስ ምክንያት ህብረቱ ፕሮጀክቱን ለማዘግየት ተገዷል:: ነፃ የንግድ ቀጣናው መርሃግብር በአፍሪቃ የበለጠ ብልፅግናን ያመጣል የሚል ዕምነት እንዳለው ይፋ ያደረገው የአውሮጳ ህብረትም ሂደቱን እንደሚደግፍ ቢገልፅም በተጓዳኝ የራሱንም "የኢኮኖሚና የንግድ አጋርነት" በአፍሪቃ ማስቀጠል ይፈልጋል::  ልዩ ልዩ ዓለማቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶችና የሲቭል ማብረሰብ አባላት ግን ከአውሮጳ በንግድ ትብብር ስም ወደ አፍሪቃ የሚገቡ ርካሽ የንግድ ሸቀጦች የአፍሪቃን የኢንዱስትሪ  ክፍለ ኢኮኖሚ ጨርሰው እያወደሙት ነው የሚል ጠንካራ ትችትና ወቀሳ እየሰነዘሩ ይገኛሉ:: የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ በ 79 ሀገራት መካከል የተፈረመውን የኮቶኑ ውል ለዚሁ ለኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነቶቹ እንደመደራደሪያ ያቀርባል::

ምስል Reuters/F. Bensch

 

እንደሚታወቀው በአፍሪቃ አህጉርና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለው ግንኙነትና የልማት ድጋፍ እንዲጠናከር ካደረጉ ስምምነቶች መካከል የሎሜ እና የኮቶኑ ስምምነቶች በዋነኘነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ስምምነቶቹ ሁለቱ አህጉራት በተለይም በምጣኔ ሃብትና በፖሊቲካው መስክ በትብብር መንፈስ እንዲሰሩ ያስቻሉ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ የሎሜ ስምምነት እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር  ከ1963 እሰከ 1975 ዓ.ም ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ የአፍሪቃ ሀገራትና የአውሮጳ ህብረት የትብብር ስምምነት ነው፡፡የስምምነቱ ዋነኛ ማዕቀፍ በቅኝ ግዛት ወቅት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት ከማሻሻል ሌላ ወደ አንድ ወገን ያደላውን የንግድ ግንኙነት ለመቀየር የሚስችልና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚፈፅሙ ጣልቃ ገብነቶችንም ለመቀነስ የሚያስችል ውልና ስምምነት እንደሆነም ይታመናል::  በሌላ በኩል የኮቶኑ ስምምነት በአዲስ መንፈስ ላይ በመመሰረት በ79 የአፍሪቃ ፣የካርቢያንና የፓስፊክ ሀገራት እንዲሁም በ15 የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት መካከል እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር  ጁን 2000 ዓ.ም በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ቤኒን የተፈረመ ስምምነት ነው፡፡ የዚህ ስምምነት አራት ዋነኛ አንኳር ምሰሶዎች  የፓለቲካ ድርድርን ማጠናከር ፣ በሀገራቱ ድህነትን ለመቀነስ የበለጠ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ ፣ ከዓለም የንግድ ድርጅት ጋር የሚጣጣም የንግድ ሥርዓትን መዘርጋትና የሲቪል ማህበራት፣የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲሁም ሌሎች ከመንግስት ውጪ ያሉ አካላትን በልማት ትብብሩ ሚናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ ነው፡፡

ምስል picture-alliance/dpa/European Commission/Eduardo Soteras

  "የኮቶኑ ስምምነት በዘንድሮው የአውሮጳውያን ዓመት ስለሚያበቃ እስከ ቀጣዩ ሚያዝያ ወር ድረስ አዲስ ሃሳብና ሌላ የመግባቢያ ስምምነት ወይም ሰነድ በጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት መቅረብ ይኖርበታል":: ይህን ሃሳብ የሚጋሩት በአውሮጳ ህብረት ፓርላማ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ እንደራሴና በህብረቱ የልማት ኮሚቴ የሶሻል ዲሞክራቶች ቃል አቀባይ ኡዶ ቡልማንም "የትብብሩን ፅንሰ ሃሳብ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ በተመለከተ አሁንም ብዙ ያልተፈቱ ጥያቄዎች አሉ :: ችግሩን ለመፍታት ተጨማሪ ውይይቶች ቢያስፈልጉም ይኸው ድርድር በኮቪድ-19 ምክንያት ከታቀደው በጣም ረዝም ያለ ጊዜን ሊወስድ እንደሚችል አሁን ግልፅ ነው" ሲሊ ተናግረዋል:: ተቺዎች ግን ስለመጪው አዲስ የድህረ ኮተኑ ውል የስምምነት ይዘት ብቻ ሳይሆን የትብብሩ አመሰራረት በራሱ መሰረታዊ የመዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገዋል ባይ ናቸው:: በአዲስ አበባ የፀጥታ ጥናቶች ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ሞሐመድ ዲታም " ዕውነታው የአውሮጳ ህብረት በኮቶኑ ውል መሰረት በተለይ ከደቡራዊ አፍሪቃ የልማት ማህበረሰብ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ ሀገራት ትብብር ጋር እንጂ መላውን አህጉሪቱን ከሚወክለው ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በቀጥታ ሲደራደር አይታይም::  " ነው ያሉት:: የአውሮጳውያን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ቡድን ሃላፊ ጌርት ላፖርቴም የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪቃ ካሪቢያንና ፓስፊክ ሃገራት ጋር መስርቶት ከቆየው የቀደመ ትብብር ይልቅ አዲስና የተሻለ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት ከአፍሪቃ ህብረት ጋር ማጠናከሩ ጠቃሚ ነው ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል::በአውሮጳ ህብረት የፊንላንድ የአረንጓዴ ፓርቲ የምክርቤት ተወካይ አልቪና አላሜሳም "በሚመለከታቸው አካላት መካከል አጠቃላይ ግልፅ ውይይት ማካሄድ የአህጉራቱን ትብብርን ለማሻሻልና ለማጠናከር ይረዳል:: በተለይም ከአፍሪቃ ህብረት ጋር በቀጥታ ትብብርን ማጠናከር በአህጉሪቱ ወሳኙን ሚያ የሚጫወት አካል በመሆኑ ፋይዳው እጅግ የላቀ ነው" ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል:: የአፍሪቃ ሀገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ፍትሃዊነት የንግድ ትብብር ፖሊሲዎችን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑንም አልሜሳ ያምናሉ ፡፡

ምስል Reuters/J. MacDougall

በአውሮጳ ህብረትና በኮሚሽኑ አባል ሀገራት በኩል የቀደሙት የአውሮጳ ቅኝ ግዛት ሀገራትን መልሶ የመገንባት ለሚደርሱ ችግሮች ፈጥኖ መርዳትና ምጣኔ ሃብታቸው እንዲያንሰራራ መደገፍ ግዴታና ኃላፊነት ነው የሚል ዕምነት አለ:: አንዳንድ ሀገራት በአሁኑ ወቅት የአውሮጳ ህብረትን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ይፈልጋሉ:: ነገር ግን ብዙዎቹ የአፍሪቃ ሀገራት የሚያሳስባቸው ጉዳይ  የህብረቱ ፍላጎት መጠቀሚያ ከሚያደርገው ከእንዲህ ዓይነቱ  አሳሪ ስትራቴጂ መቼ መላቀቅ እንደሚችሉ ነው:: ለአፍሪቃ ህብረት በአውሮጳ ጉዳዮች ዙሪያ አማካሪ የሆኑት ፋቴን አጋድ እንደሚሉት "የአፍሪቃና የአውሮጳ ህብረቶች ስለ አዲሱና መጪው የትብብር ስትራቴጂዎቹ ዓላማና ውጤት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው በግልፅ የሚነጋገሩበት ጊዜው አሁን ነው:: እንደ ከዚህ ቀደሙ ´ሀገራቱ ምን ለማድረግ እንዳሰቡ´ ሳይሆን ግባቸውን ´እንዴት ማሳካት እንደሚችሉ´ ጥልቅ ውይይት ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ አስረድተዋል:: የአውሮጳ ኮሚሽን ባለፈው ወር የአፍሪቃ እስያ ላቲን አሜሪካና ባልካን ሀገራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ 20 ቢልዮን ዩሮ ለመርዳት መወሰኑን ያስታወቀ  ሲሆን አባል ሀገራቱም በተለይም በህክምና ቁሳቁስ እጥረትና በጤና አገልግሎት አለመስፋፋት ስጋት ውስጥ ለምትገኘው አፍሪቃ ኮረናን ለመከላከል ከተለያዩ ዓለማቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ልዩ ልዩ የህክምና ቁሳቁሶችን ከፈረንሳይ ሊዮን አውሮፕላን ማረፊያ ወደ አፍሪቃ በማጓጓዝ ላይ እንደሚገኝም የኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ ፕሮግራም ሃላፊ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል:: የአውሮጳና የአፍሪቃ ህብረቶች በድጋፍ ሰጪ ትብብሮች ላይ የሚያተኩር ጠንካራ ስትራቴጂካዊና ፖለቲካዊ አጋርነትን ደረጃ በደረጃ ገንብተዋል:: ይህ አጋርነት ደግሞ ይፋ የሆነው እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ 2007 ዓ.ም ፖርቹጋል ሊዛቦን ውስጥ በተካሄደ ትልቅ ጉባኤ ሲሆን ዓላማውም የሁለቱን ህብረቶች ትብብር ለማጠናከርና ወደላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች ያካተተ እንዲሁም የጋራ ዕሴቶችና ፍላጎቶች ላይ የተመሰረተ ነው::

ማሪና ስትራውስ

እንዳልካቸው ፈቃደ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW