የአውሮጳ ህብረት መሪዎች ፓሪስ ውስጥ ሊገናኙ ነው
እሑድ፣ የካቲት 9 2017
የመሪዎቹን መሰብሰብ ያረጋገጡት የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጄን ኖኤል ባሮት የትኞቹ ሃገራት ይገኛሉ የሚለውን ግን ከመግለፅ ተቆጥበዋል። በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኤማኑኤል ማክሮ ጋባዥነት የሚካሄደው የመሪዎቹ ስብሰባ የአውሮጳ ህብረት የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው የስምምነት ሂደት የድርሻቸውን ለመወጣት ያለመ ስለመሆኑ የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ጠቅሶ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዲፒኤ ዘግቧል።
በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መካከል የስልክ ንግግር ከተደረገ ወዲህ የአውሮጳ ህብረት እና ዩክሬን ከሰላም ስምምነቱ እንገለል ይሆን ሲሉ ስጋት ገብቷቸዋል። ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያ ጋር በሚደረገው ድርድር ውስጥ አውሮጳውያኑ እንዲሳተፉ አይፈልጉም የሚል ስጋትም ተፈጥሯል።
የሩስያ ዩክሬን ጦርነትን ለማብቃት የሚደረገው ጥረት በተጠናከረበት በዚህ ጊዜ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሩስያ ከፍተኛ የልዑክ ቡድን ጋር በቀጣዩ ሳምንት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል።
በሙኒክ የጸጥታ እና የደህንነት ጉባኤ ላይ አውሮጳውያኑ በድርድሩ ላይ ስለሚኖራቸው ሚና የተጠየቁት በዩክሬን የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ኪት ኬሎግ ጨዋነት የጎደለው ምላሽ መስጠታቸው ተሰምቷል።
በስብሰባዉ ተሳታፊ የነበሩት የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ አሜሪካ ከዩክሬን ጀርባ ከሩሲያ ጋር ሥምምነት እንዳትፈጽም ትናንት ቅዳሜ ባደረጉት ንግግር አስጠንቅቀዋል ። ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው “ዩክሬን ያለ እኛ ተሳትፎ ከጀርባችን የሚፈጸም ሥምምነትን በፍጹም አትቀበልም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ዜሌንስኪ ለተግባራዊ እርምጃ እና አኅጉሩ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ላቀረቡት ጥሪ የአውሮፓ መሪዎች ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ታምራት ዲንሳ