የአውሮጳ መሪዎች ስብሰባ በጋራ መከላከያ ላይ
ማክሰኞ፣ ጥር 27 2017
መሪዎቹ ሕብረቱ የራሱን ደኅንነት የሚያረጋግጥበት የመክላከያ ተቋም መገንባት ከሚያስፈልግበት ጊዜ መደረሱን በማመን ለጋራ የመከላከያ ግንባታ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከመንግሥታትና ከግሉ ዘርፍ ማግኘት ስለሚቻልባቸው ስልቶችና አሰራሮች ተወያይተው ለዝርዝር እቅዶች መነሻ ሀሳቦች ያቀረቡ መሆኑ ተገልጿል።
የጋራ መከላከያ ያስፈለገባቸው ምክንያቶች
የካውንስሉ ፕሬዝደንትና የስብሰባው መሪ አንቶኒዮ ኮስታ ከስብሰባው በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት ሕብረቱ የጋራ መክላከያ ሀይል እንዲኖረው ያስፈልገባቸውን ምክንያቶች ሲያስረዱ፤ «የዩክሬኑ ጦርነት፣ የሳይበር ጥቃቶችና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ፤ አውሮጳ የራሱ የሆነ ጠንካራ ሀይል እንዲገነባ አስገድደውታል» በማለት የስብሰባው ትኩረትም በአቅም ግንባታ፣ በጀትና አጋር ማበጀት ላይ መሆኑን ዘርዝረዋል። በአባል አገሮችና በሕብረቱ የመከላከያ ኤጀንሲ የተጠቀሱት ጉድለቶች ላይ ትኩረት እንዲደረግም ማሳሰቢያ የተሰጠ መሆኑን በመጥቀስ፤ መሪዎቹ በስብሰባቸው በዋናነት ያስተላልፉት መልክት፤ «በአውሮጳ የመከላከያ እንዱስትሪ ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑን ነው» በማለት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችን በፍጥነት ማምረት መቻል አለብን ብለዋል።
የሚያስፈልገው የገንዘብ ምንጭ
ለዚህ የመካላከያ ሀይል ግንባታ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በሚመለክትም የተወያዩ ሲሆን፤ የሕብረቱ የመከላከያ ወጭ ከ2022 እስከ 2024 በ30 ከመቶ ማደጉ ተገልጿል። የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ከሆኑት የሕብረቱ አገሮች ውስጥ 23ቱ የመከላከያ በጀታቸውን ከጠቅላላ ገቢያቸው ሁለት ከመቶ ማድረሳቸው የሚያበረታት ቢሆንም፤ ብቃት ያለው የጋራ መከላከያ ሀይል ለመገንባት ግን የበለጠ የሕዝብና የግል መዋዕለ ንዋይ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል። በዚህ በኩልም ጥረት መደረግ እንዳለበት መሪዎቹ አምነውበታል ተብሏል።
የአውሮጳ ጋራ መከላከያ ወቅታዊነት
የአውሮጳ የጋራ መከላከያ ፕሮጀክት፤ አሜሪካ ከምትመራው የስሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ጥገኝነት መላቀቅ አስፈላጊነት ጋር ተያይዞ ሲነሳ ቆይቷል። ይህም በተለይ በአሁኑ ወቅት ወደፊት የመጣው ግን አሜሪካ ላይ ዳግም ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተገማች ያልሆነ ፖሊስ ምክንያት እንደህነ ነው ብዙዎች የሚያምኑት። ያም ሆኖ የሚቋቋመው የአውሮጳ የጋራ የመከላከያ ሀይል የስሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ጋር እንደሚተባበርና ከአሜሪካ ጋር ያለው ትብብርና ወዳጅነትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈለግ መሆኑን ነው የስብሰባው መሪ ያስታወቁት።
በአውሮጳ ላይ ሊጣል በሚችል ቀረጥ ሊወሰድ የሚችል የአጸፋ እርምጃ
የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዑርዙላ ፎንዴርንም፤ አሜሪካ የአውሮጳ ዋና አጋርና ወዳጅ መሆኗን ጠቅሰው፤ በሚታዩ ልዩነቶች ላይ ገምቢ ውይይቶችን በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት ሕብረቱ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል። ሆኖም ግን አሉ ወይዘሮ ፎንዴር ላየን በመግለጫቸው፤ «ትክክል ባልሆነ መንገድ ሕብረቱ ኢላማ ከተደረገ የአውሮጳ ሕብረትም የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል» በማለት ባለፉት ቀናት በፕሬዝዳንቱ እርምጃ ምክንያት በሜክሲኮና ካናዳ ብሎም በአሜሪካ ጭምር የተፈጠረውን ማስታወስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
በጋራ መከላከያ ግንባታ ላይ ያተኮረው የመሪዎች ስብሰባ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአውሮጵ ላይም እጥለዋለሁ በሚሉት ቀረጥና በዩክሬን ጦርነት ላይ በሰፊው እንደተወያዩ ተገልጿል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአውሮጳ ጋር በኔቶ ወጭም ሆነ በንግድ ያለው ግንኙነት የተዛባ ነው በማለት በአውርጳ ሸቀጦች ላይ ታክስ መጭመርን አክሎ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስዱ ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።
አሜሪካ በተለይ በአውሮጳ ላይ የምትወስደው እርምጃና የምትጥለው ቀረጥ ግን ሁለቱንም የሚጎዳና በአንጻሩ የጋራ ጠላቶችቸውን የሚጠቅም መሆኑን በማስረዳት ፕሬዝዳንቱን ማግብባት ያስፈልጋል የሚሉ ሀይሎች፤ የሚቋቋመው የመከላከያ ሀይል ግንባታም ከአሜሪካ በሚገዙ መሣሪዎች ጭምር እንዲሆን ይመክራሉ።
ተጋባዥ እንግዶች
በስብሰባው የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስተር ኪር ስታርመርና የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩት ተግኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስተር ስታርመር ብሪታኒያ ከሕብረቱ ክወጣች በኋላ በሕብረቱ የመሪዎች ስብሰባ የተገኙ የመጀመሪያው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስተር ሲሆኑ፤ ይህም ብሪታኒያና ሕብረቱ በመከላከያና ንግድ ለመቀራረብ ያላቸውን ፍላጎትና ተነሳሽነት የሚያመላክት ሆኖ ተወስዷል።
ገበያው ንጉሤ
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ