የአውሮጳ ኅብረትና ዩክሬን ያልመከሩበት የአሜሪካ ሩስያ የዩክሬን ጦርነት ማስቆሚያ እቅድ
ሐሙስ፣ ኅዳር 11 2018
ማስታወቂያ
ዩናይትድ ስቴትስ እና ሩስያ የዩክሬኑን ጦርነት ሊያስቆም ይችላል የተባለ እቅድ መንደፋቸው ተሰምቷል። አንድ ለጉዳዩ ቅርበት አላቸው የተባሉ ሰውን ጠቅሶ አሶስየትድ ፕሬስ እንደዘገበው እቅዱ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ በትላልቅ ጉዳዮች ላይ በሰጥቶ መቀበል እንዲስማሙ ጥሪ ያቀርባል።
የአውሮጳ ዲፕሎማቶች ግን ይህን መሰሉ እቅድ የአውሮፓ ኅብረትና ዩክሬንን ባልተሳተፉበት የትም አይደርስም ሲሉ ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። የኅብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ዛሬ የኅብረቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ብራሰልስ ውስጥ ስብሰባ ከመቀመጣቸው በፊት በሰጡት አስተያየት ሩስያ ሰላም ፈላጊ ከሆነች ቀደም ባሉት ጊዜያት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ታደርግ ነበር ሲሉ ተናግረዋል። የፖላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ኅብረቱ የሰላም ጥረቶችን እንደሚደግፉ አስታውቀው በጉዳዩ ላይ እኛም መምከር አለብን ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ዛሬ ከሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአሜሪካንሩስያ የሰላም እቅድ ዋነኛው ነው። የሱዳን ጉዳይ ቤልጀየም የሚገኘውን የሩስያ ገንዘብ ለዩክሬን መስጠትና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ይገኙበታል ። የብራሰልሱን ዘጋቢያችንን ገበያው ንጉሴን በዛሬው ስብሰባ ትኩረት በተሰጣቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አነጋግረነዋል።
ገበያው ንጉሴ
ኂሩት መለሰ