1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት ለግብጽ የሰጠው የ7.4 ቢሊዮን ዩሮ ብድርና እርዳታ

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2016

የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ለግብጽ የ7.4 ቢሊዮን ዩሮ ብድርና እርዳታ ለመስጠት ተፈራርሟል።ከዚህ ብድርና እርዳታ ውስጥ የተወሰነው ወደ አውሮጳ የሚጎርፈውን ስደተኛ ለማስቆም የለመ ነው። ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ስደትን ለማስቆም ሰብዓዊ መብቶችን ባለመክበር ከሚወቅሷት ከግብጽ ጋር ኅብረቱ የሚያደርገውን ትብብር የመብት ተሟጋቾች ይተቻሉ።

EU-Kommissionspräsidentin von der Leyen in Ägypten
ምስል Egyptian Presidency/AFP

የአውሮጳ ኅብረት ለግብጽ የሰጠው የ7.4 ቢሊዮን ዩሮ ብድርና እርዳታ

This browser does not support the audio element.

«የጋራ ስልታዊ እና አጠቃላይ አጋርነት የተፈራረምንባት የዛሬዋ ቀን ታላቅ ታሪካዊ ሂደት የተመዘገበባት እለት ናት። ትብብሩ ለአውሮጳና ለግብጽ ስድስት የጋራ ጥቅሞችን መሠረት ያደረገ ነው። ይህም በመጪዎቹ አራት ዓመታት በአዲስ የ7.4 ቢሊዮን ዩሮ የፋይናንስ መዋዕለ ንዋ ፍሰት ማዕቀፍ የሚደገፍ መሆኑን ስገልጽ ደስታ ይሰማኛል። »
የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኡርዙላ ፎን ደር ላየን ከግብጽ ፕሬዝደንት አብደል ፋታኅ አል-ሲሲ ጋር ባለፈው እሁድ ካይሮ ውስጥ የ7.4 ቢሊዮን ዩሮ ወይም የ8 ሚሊዮን ዶላር የአጋርነት ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ካደረጉት ንግግር የተወሰደው ነበር ። ፎን ዴር ላየን ካይሮ የሄዱት ከቤልጅየም ከጣልያን ከኦስትሪያ ከግሪክ እና ከቆጵሮስ መሪዎች ጋር  ነበር። በፎን ዴርላየን መሪነት ወደ ግብጽ የሄዱት መሪዎች በካይሮ ቆይታቸው ከግብጹ ፕሬዝዳንት ጋር ሕገ ወጥ ስደትን መቋቋምን  ጨምሮ በሌሎች የጋራ ጉዳዮችም ላይ መወያየታቸውን የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ተናግረዋል።


«ውይይቶቹ በተለይ እጅግ ፈታኝ የሆነውን ሕገ ወጥ ፍልሰትን ጨምሮ ሌሎች የጋራ ተግዳሮቶችን መቋቋማችንን መቀጠላችን አስፈላጊ መሆኑን አንስተናል። ይህን ለመዋጋትም ቆርጠን መነሳታችንን አረጋግጠናል።»ከሰሜን አፍሪቃዊቷ አገር ግብጽ ጋር የሚካሄዱ ፖለቲካዊ ውይይቶችን የማጠናከር ዓላማ ያለው ይህ ስምምነት እስከ ጎርጎሮሳዊው 2027 ለግብጽ 5 ቢሊዮን ዩሮ ብድር መስጠትን ያካተ ነው ። ተጨማሪ 1.8 ቢሊዮን ዩሮ ደግሞ የኃይልና የመረጃውን ዘርፍ የመሳሰሉ የተለያዩ መስኮችን ለማልማት መታቀዱ ተገልጿል። ግብጽ በዚህ ስምምነት በአጠቃላይ የ600 ሚሊዮን ዩሮ እርዳታም ይሰጣታል ። ከዚህ ሌላ በተለይ አሸባሪነትንና ፍልሰትን ለመከላከል የሚያስችሉ ትብብሮች ይኖራሉ። ይህም በአንድ በኩል ሕግ ወጥ የሚባለውን ስደት መንስኤዎች መከላከልን በሌላ በኩል ደግሞ ወደ አውሮጳ የሚወስዱ ሕጋዊ የፍልሰት መንገዶች እንዲዘረጉ ማስቻልንም ያካትታል ተብሏል። ወደ አውሮጳ የሚደረገውን ፍልሰት ለመቆጣጠር ያለመው እነሱ የስደተኞች አስተዳደር ለሚሉት አሰራር የአውሮጳ ኅብረት ለግብጽ 200 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር በካይሮ ምስል Egyptian Presidency/AFP


በጀርመንን የውጭ ፖሊሲ ጉዳይ ማኅበረሰብ የፍልሰት መርኃ ግብር ሃላፊ ቪክቶሪያ ሪቲግ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት የአውሮጳ ኅብረት ከግብጽ ጋር በተለይ የፍልሰተኞች አስተዳደር የትብብር ስምምነት ሲያደርግ የእሁዱ የመጀመሪያው አይደለም። እርሳቸው እንደሚሉት የአውሮጳ ኅብረትና ግብጽ በዚህ ጉዳይ ላይ በትብብር ሲሰሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ኅብረቱና ግብጽ ከጎርጎሮሳዊው 2004 ዓም አንስቶ በዚህ ረገድ የሚኖራቸውን ግንኙነት የሚመለከት የጋራ ስምምነት አላቸው። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን እንደሚለው ወደ አውሮጳ የሚፈልሱ ስደተኞችን ለመቆጣጠር እስካሁን ለግብጽ በአጠቃላይ 171 ሚሊዮን ዩሮ ተፈቅዷል። ገንዘቡም ግብጽ ድንበሮቿን እንድታስተዳድር፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ሽግግርን እንድትከላከል፣እንዲሁም ስደተኞች በፈቃዳቸው ወደመጡበት እንዲመለሱ ለማበረታታት የሚውል መሆኑ ተገልጿል። የአውሮጳ ኅብረት የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከር መስማማቱ


የተመ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን እንደሚለው ግብጽ ውስጥ ቁጥራቸው ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዎች በስደተኝነት ተመዝግበዋል። ከዚህ በመነሳት ኅብረቱ አሁን ከግብጽ ጋር ስምምነት ሊያደርግ የበቃው ምናልባት ወደ አውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የሚያስገቡ መስመሮች ቁጥር ማደግ አንዱ ምክንያት ነውም ይባላል። ሪቲሽ እንደሚሉት ኅብረቱ በዚህ ረገድ ከግብጽ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱ እንደ ታላቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ግብጽ በበኩልዋ በሀገርዋ በኩል ወደ አውሮጳ የሚሄዱ ፍለሰተኞች ቁጥር ዝቅ እንዲል አድርጋለች። ይህም የተሳካላት  ችግሩን ለመከላከል የስደተኞችን መብት ማስከበርንም ሆነ  ጥበቃ ማድረግን ከግምት ውስጥ ሳታስገባ  ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ በመሆኑ ነው ይላሉ ሪቲሽ ።

«ከአውሮጳውያን እይታ አንጻር በፍልሰት ቁጥጥር ላይ ከግብጽ ጋር በትብብር መስራት  ከሌሎች ሀገራት ጋር ከተደረገው ስምምነት ጋር ሲነጻጸር ታላቅ ስኬት ነው። የዚህ ምክንያቱ የግብጽ አገዛዝ ከግብጽ ወደ አውሮጳ የሚነሱ (ስደተኞችን የጫኑ) ጀልባዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ እንዲሆን  ከሌሎች በተለየ ግብጽ እጅግ ኃይለኛ ቁጥጥር ተግባራዊ ታካሂዳለች። የግብጽ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭ ስለሆነ ችግሩን ለመከላከል ወታደራዊ መንገዶችን ነው የሚጠቀመው።  ስለ ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃም ሆነ ለስደተኞች ጥበቃ ማድረግን በሚመለከት ብዙም ደንታም የለውም።»
የጋራ ስምምነት የተባለው የግብጽና የአውሮጳ ኅብረት ውል ዓላማዎች ውስጥ የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን እንዳለው ዴሞክራሲ መሰረታዊ ነጻነቶች ሰብዓዊ መብቶችና የፆታ እኩልነትን ማራመድ እና ከፍልሰትና ከአሸባሪነት ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶችን መፍታት ይገኙበታል ።ሆኖም መቀመጫውን ዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ፍሪደም ሀውስ የተባለው የጥናት ድርጅት እንደሚለው ከጎርጎሮሳዊው 2014 ዓ.ም. አንስቶ አምባገነን በሚባሉት በአብዱልፈታህ አል ሲሲ  በምትመራው በግብጽ ስለሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሌም እንዳማረረ ነው። ድርጅቱ እንደሚለው በግብጽ ፖለቲካን መነሻ ያደረጉ እስሮች ይፈጸማሉ። በፕሬስ ነጻነት ላይና በመሰብሰብ መብቶች ላይ  ገደቦች ተጥለዋል።

ካይሮ ውስጥ ከአልሲሲ ጋር የተናገሩት የአስትሪያ መራኄ መንግሥት ካርል ኔማር፣የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትr ኪርያኮስ ሚትሶታኪስ፣የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽነር ኡርዝላ ፎን ዴር ላየን የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣የቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ኒኮስ ክሪስቶዱሊዲስ፣ የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ፣ የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ምስል Dirk Waem/Belga/picture alliance

የአውሮጳ የውጭ ጉዳዮች ምክር ቤት በምህጻሩ ECFR የተባለው የጥናት ተቋም  ከፍተኛ የፖሊሲ አጥኚ  አንተኒ ድዎርኪን የአውሮጳ ኅብረት በግብጽ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል። «በግልጽ እንደሚታወቀው በግብጽ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ እጅግ አስቸጋሪና አሳሳቢ ነው። የግብጽ መንግሥት በቅርቡ ሁኔታውን በተለየ መንገድ ለማቅረብ ሞክሯል። ሆኖም የአውሮጳ ሀገራት eህን ጉዳይ አይቶ እንዳላዩ, ማለፍ የለባቸውም። ይልቁንም ለውጥ እንዲመጣ ግፊት ማድረግ አለባቸው። »
የአውሮጳ ኅብረት በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ከሚተቹ ሀገራት ጋር መሰል ስምምነት ሲያደርግ የባለፈው እሁዱ የመጀመሪያው አይደለም።በጎርጎሮሳውያኑ 2023 ኅብረቱ ሰብዓዊ መብቶችን በማስከበር ረገድ ችግሮች ካሉባት ከቱኒዝያ እንዲሁም ከሞሪቴንያ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት አድርጓል። የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ጉባኤና የስደተኞች ጉዳይ 

ያም ሆኖ የአውሮጳ ኅብረት ከግብጽ ጋር ስምምነት ያደረገበት በቂ ምክንያት አለው።የፍልሰት ጉዳዮች ተመራማሪዋ ሪቲሽ እንደሚሉት ከስምምነቱ ከመልክዐ ምድራዊ ጥቅም ጋር የተያያዘው ባህርይ ይጎላል።«እኛ ከግብጽ ጋር ካልተባበርን ማን ከግብጽ ጋር ይተባበራል?  እኛ አውሮጳውያን ከሀገሪቱ ጋር የሚኖረን ትብብር አነስተኛ ከሆነ መልክዐ ምድራዊ ክፍተት ይፈጠራል። ይህ ክፍተት ደግሞ ከረዥም ጊዜ አንስቶ በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ባፈሰሱት በሩስያ ቻያናና በባህረሰላጤው አገራት የሚሞላ ነው የሚሆነው።»በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት IOM ለግብጽ የሚሰጠውን ብድር በ8 ቢሊዮን ለማሳደግ ተስማምቷል። ከዚያ ቀደም ሲል የተባበሩት አረብ ኤምሪቶች በግብጽ ኤኮኖሚ ላይ 35 ቢሊዮን ዶላር እንደምትወርት አስታውቃ ነበር። ግብጽ በአሁኑ ጊዜ በምጣኔ ሀብት ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን እጅግ ባሻቀበው የዋጋ ግሽበትም እየተሰቃየች ነው።በሊቢያ እና ስደተኞች ጉዳይ የመከረዉ የአዉሮጳ ኅብረት  


በሪቲሽ አስተያየት ከአውሮጳ ኅብረት ጋር የፈጸመችው የትብብር ስምምነት ለግብጽ ከበርካታዎቹ የአንዱ ነው። ድዎርኪን እንደሚያስቡት ስምምነቱ በዋነኛነት የኤኮኖሚ ስምምነት ነው። በዚህ ረገደም ግብጽ ይህ ማድረግ የሚያስችላት ትክክለኛው ጎዳና ላይ መሆንዋን ለማረጋገጥ የሚስችል መመዘኛ ያስፈልጋታል ይላሉ።«ይህን በሚመለከት ዋነኛው ጥያቄ ግብጽ በስምምነቱ በኤኮኖሚዋ ረገድ ለውጥ ማምጣት አለማምጣቷን ለማጤን  አስገዳጅ የሆነ መስፈርት መካተት አለማካተቱ ነው።» ይሁንና ግብጽ በአሁኑ ጊዜ ለአውሮጳ ኅብረት ትልቅ ስልታዊ መልክዐ ምድራዊ ጥቅም ያላት ሀገር ናት።ፎን ዴር ላየን ባለፈው እሁድ ባደረጉት ንግግር ሀገሪቱ ለምትገኝበትን አካባቢ መረጋጋትና ጸጥታ ወሳን የሚባለውን ሚና ትጫወታለች። በስተደቡብ ጋዛ የምታዋስናት ግብጽ የመካከለኛውን ምስራቅ ግጭት ለመሸምገል ትፈልጋለች። በእሁድ የካይሮ ጉብኝታቸው ፎን ዴር ላየን አል ሲሲ እስራኤልና ሀማስ ተኩስ እንዲያቆሙ በግል ላሳዩት ጽናት አድናቆታቸውን ቸረዋቸዋል። 

ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW