የአውሮጳ ኅብረት የመስፋፋት እቅድና አንድምታው
ማክሰኞ፣ መጋቢት 6 2014ከዩክሬኑ ጦርነት ወዲህ የአውሮጳ ኅብረት የመስፋፋት እቅድ እንደገና ያንሰራራ ይመስላል። የኅብረቱ የውጭ ጉዳዮች ፖሊሲ ሃላፊ በተለይ የምዕራብ ባልካን ሀገራት ኅብረቱን መቀላቀላቸው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በዚህ ሳምንት ገልጸዋል። የአውሮጳ ኅብረት በተለያዩ ጊዜያት የአባላቱን ቁጥር በማሳደግ እየተስፋፋ ነው። የኅብረቱ መነሻ የሆነው የአውሮጳ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ የተመሰረተው በጎርጎሮሳዊው ጥር አንድ 1958 በቤልጅየም ጀርመን ፈረንሳይ ኢጣልያ ሉክስምበርግና ኔዘርላንድ የሮሙ ውል በስራ ከተተረጎመ በኋላ ነው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የአውሮጳ ኅብረት እየሰፋ ዛሬ አባላቱ 27 ደርሰዋል። ከመካከላቸው የኅብረቱ አዲስ አባል የምትባለው በጎርጎሮሳዊው 2013 ኅብረቱን የተቀላቀለችው ክሮኤሽያ ናት።
በአሁኑ ጊዜ አምስት ሀገራት የአውሮጳ ኅብረት አባል ለመሆን በድርድር ሂደት ላይ ናቸው አልባንያ ከጎርጎሮሳዊው 2020 አንስቶ ፣ሞንቴኔግሮ ከ2012 አንስቶ ፣ሰሜን መቄዶንያ ከ2020 አንስቶ፣ ሰርቢያ ከ2014 አንስቶ ፣እንዲሁም ቱርክ ከ2005 ዓም አንስቶ የኅብረቱ አባል ለመሆን በመደራደር ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው። ከቱርክ በስተቀር አራቱ የምዕራብና ባልካን ሀገራት ናቸው ።ከመካከላቸው ሰርቢያና ሞንቴኔግሮ በጎርጎሮሳዊው 2025 የኅብረቱ አባል ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የቀደሙት የኅብረቱ ሃላፊዎች ተናግረዋል ።ከዚህ ሌላ ቦስንያ ሄርዞጎቪና በ2016 ለአባልነት ማመልከቻ አስገብታ እየተጠባበቀች ነው። ሩስያ በዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተች በኋላ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮልዲሚር ዜሌንስኪ ሀገራቸው የአውሮጳ ኅብረት አባል እንድትሆን በይፋ የሚጠይቅ ማመልከቻ ፈርመዋል። ከዚያ ቀደም ሲል ደግሞ የቀድሞ የሶቭየት ኅብረት ግዛት የነበሩት ጆርጅያና ሞልዶቫ የኅብረቱ አባል ለመሆን እንደሚያመለክቱ አስታውቀዋል።ሞልዶቫ ማመልከቻውን ፈርማለች። የአውሮጳ ኅብረትም በተለይ ከዩክሬኑ ጦርነት ወዲህ ለኅብረቱ መስፋፋት ለየት ያለ ትኩረት የሰጠ መስሏል። በዚህ ሳምንት ሰሜን መቄዶናያ የነበሩት የኅብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል የኅብረቱ መስፋፋት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። «አሁን አውሮጳ ነቅቶ መገኘት ያለበት ወቅት ነው ። ይህ ወቅቱ የምዕራብ ባልካን ሀገራት በአውሮጳ ኅብረት እንዲታቀፉ የኅብረቱ መስፋፋት ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ወቅት ነው።»
የኅብረቱ አባል ለመሆን በመጠባበቅ ላይ ከሚገኙት ሀገራት ውስጥ ስድስቱ የምዕራብ ባልካን ሀገራት ናቸው።ለኅብረቱ አባልነት ያገቡት ማመልከቻበተለያየ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። ሰሞኑን በባልካን ሀገራት ጉብኝት ያደረጉት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አነ ሌና ቤርቦክ በሰርቢያ ጉብኝታቸው ሰርቢያ የህብረቱ አባል እድትሆን ሆን የሀገራቸው ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል። «ሰርቢያ ወደፊት የአውሮጳ ኅብረት ሙሉ፣ እኩል እና ነጻ አባል እንድትሆን እንፈልጋለን።ሰርቦች በአውሮጳ የጋራ ቤታችን በነጻነት የመኖር ፣ የደኅንነት የዴሞክራሲና የመበልጸግ መብት እንዳላቸው እናምናለን።በማንኛውም ጊዜ ሰርቢያን አስፈላጊ በሆኑ የተሀድሶ እርምጃዎች በተለይም የህግ የበላይነትን በማስፈን ሂደት በሙሉ አቅማና በቅንንነት እንደግፋለን።»
የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራትና የኅብረቱ መሪዎች ሰሞኑን ኅብረቱ እንዲስፋፋ በተለይም የምዕራብ ባልካን ሀገራት በኅብረቱ እንዲታቀፉ ያሳዩት የተለየ ፍላጎት አንድምታ ምንድነው ስንል የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋን ጠይቀናቸዋል። መስፋፋቱን« ችግርን ከደጅ ለማራቅ መፈልግ ብለውታል» ዶክተር ለማ።
በማስትሪቹ ስምምነት መሰረት ኅብረቱ ተጨማሪ አባላት ማስገባት የሚችለው እያንዳንዱ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገርና የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ሲስማሙ ነው። የኅብረቱ አባል መሆን ከሚያስችሉት መስፈርቶች ውስጥ በኮፕንሀገኑ ስምምነት መሰረት የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ሁኔታዎች ይገኙበታል። አንድ ሀገር የአውሮጳ ኅብረት ብረቱ አባል ለመሆን የሕግ የበላይነትንና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ነጻነቶችንና ተቋማትን የሚያከብር የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሊኖረው ይገባል። የአባል ሀገራት መንግሥታት የአባልነት ማመልከቻ ተቀባይነት ቢያገኝም ኅብረቱን ለመቀላቀል መካሄድ ያለበት ድርድር ዓመታት ሊወስድ ይችላል።
ሙሉውን ዝግጅት በድምፅ ከታች ከሚኘውን የድምጽ ማዕቀፍ ማድመጥ ይቻላል።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ