የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርዙላ ፎንደርላይን የመተማመኛ ድምፁ አገኙ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2017
የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርዙላ ፎንደርላይን የመተማመኛ ድምፁ አገኙ
የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርዙላ ፎንደርላይን በሀላፊነት ለመቆየት የሚያስችላቸውን ከፍተኛ የመተማመኛ ድምፅ አገኙ። የኅብረቱ ፓርላማ አባላት በአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ላይ ዛሬ የመተማመኛ ድምጽ የሰጡት ፣ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ፋይዘር ከተባለው የክትባት አምራች ኩባንያ ዋና ሃላፊ ጋር በግል የጽሁፍ መልእክት ተለዋውጠዋል፤ የአውሮጳ ህብረት የእርዳታ ገንዘብን አለአግባብ ተጠቅመዋል፤ በጀርመንና በሮማንያ ምርጫም ጣልቃ ገብተዋል የሚሉ ክሶች ከቀረቡባቸዉ በኋላ ነዉ። ዛሬ በህብረቱ ምክር ቤት በሚገኝበት በሽትራዝ ቡርግ ላይ በተካሄደዉ የድምፅ አሰጣጥ 175 አባላት ክሱን ትክክል ሲሉ፤ 360 አባላት ክሱን ዉድቅ አድርገዉታል። 18 አባላት ደግሞ ምርጫዉን በድምፀ ታዕቅቦ አልፈዉታል። ዛሬ የህብረቱ ምክር ቤት ባካሄደዉ የድምጽ አሰጣጥ ላይ ከ 719 የአዉሮጳ ህብረት ምክር ቤት አባላት መካከል 553 አባላት በምርጫዉ ተሳትፈዋል። እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው የአውሮጳ ህብረት ህግ አውጪዎች በእሳቸው ላይ የቀረበውን ወቀሳ ውድቅ አድርገዋል።
ኡርዙላ ፎንደርላይን - ሹመት
የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት፣ የህዝብ እንደራሴዎች ህብረት ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ያጫቸውን የኡርዙላ ፎን ዴር ላየንን ሹመት ያፀደቀዉ በጎርጎረሳዉያኑ ታህሳስ 2019 ነዉ። የጀርመን የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ፎን ዴር ላየን፣ ሳይጠበቅ እና ከተለመደው አሰራር በተለየ ለዚህ ኃላፊነት መታጨታቸው ሲያወዛግብ ነበር። በዚህ ምርጫም የጀርመን መከላከያ ሚኒስትር ወይዘሮ ኡርዙላ ፎን ዴር ላየንን የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት፣የቤልጂግ ጠቅላይ ሚኒስትር ቻርልሰ ሚሼልን የህብረቱ የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም የዓለም የገንዘብ ድርጅት በምህጻሩ IMF የበላይ እና የቀድሞ የፈረንሳይ የገንዘብ ሚኒስትር ወይዘሮ ክርስቲን ላጋርድን ለአውሮጳ ማዕከላዊ ባንክ ገዥ፣ እንዲሁም የስፓኝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፕ ቦሬልን ለህብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊነት አጭቷል። ሁለት ሴቶች ለነዚህ ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች መመረጣቸው ህብረቱ የሴቶች ተዋጽኦን ለማስተካከል ከዚህ ቀደም የገባውን ቃል አሳክቶለታል። ሆኖም መሪዎቹ በእጩዎቹ ስየማ ላይ የተስማሙት ሦስት ቀናት ከወሰደ ከባድ ክርክር በኋላ ነበር። የቀደመው ግምት መሪዎቹ በተለመደው አሠራር በአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ፣አብላጫ ድምጽ ያገኙትን የአውሮጳ ህዝቦች ፓርቲ በምህጻሩ የEPP ተቀዳሚ እጩ፣ ማንፍሬድ ቬበርን ይመረጣሉ የሚል ነበር። በቀደመው የአመራረጥ ስርዓት በምርጫው አብላጫ ድምጽ ያገኘ ፓርቲ ቀዳሚ እጩ ነበር ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት የሚታጨው። የቀድሞዋ ጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም የእህት ፓርቲያቸው የጀርመኑ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲ አባል ቬበር የኮሚሽኑ ሃላፊነቱን እንዲወስዱ ነበር የሚፈልጉት።