1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2016 ዓ.ም የአውሮፓ ዋንጫ መክፈቻ እና የጀርመን ድል

ቅዳሜ፣ ሰኔ 8 2016

አንጋፋ እና ወጣት ተጫዋቾችን አጣምሮ የተጫወተው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዩሊያን ናግሊስማን ጅምሩ ሰምሮለታል። ከጨዋታው በኋላ በሰጠው መግለጫም ተጫዋቾቹን አሞግሶ፣ ስኮትላንድ በማጣሪያው ከነበራት ጥንካሬ አንጻር ባሳየችው ደካማ እንቅስቃሴ መደነቁን ግን አልሸሸገም።

ጀርመንና ስኮትላንድ በመክፈቻ ጨዋታ ላይ
ጀርመንና ስኮትላንድ በመክፈቻ ጨዋታ ላይምስል Andrew Milligan/empics/picture alliance

የአውሮጳ ዋንጫ

This browser does not support the audio element.

የትናንትናው የአውሮፓ ዋንጫ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በግዙፋ አሊያንስ አሬና፥ በሙዚቃ፣  እንዲሁም በርችት ታጅቦ ነው የተካሔደው። ጀርመን ታሪክ እና ባህሏን ከማሳየትም ሌላ በዚሁ የፈረንጆች ዓመት በሞት የተለየውን ፈራንስ ቤከንባወር አስባበታለች። የተጫዋቹ ባለቤት ከ1980 የአውሮፓ ዋንጫ አሸናፊ በርናርድ ዲትስ እና ከ1996 ሻምፒዮን ዩርግን ክሊንዝማን ጋር የውድድሩን ዋንጫ በመያዝ ወደ ሜዳ ገብታለች።

ስታዲየሙን ከአፍ እስከ ገደፉ ከሞላው ተመልካች በተጨማሪም በሙንሽን አደባባዮች በትልልቅ ስክሪኖች ይህንን ሁነት የተከታተሉት አያሌ ነበሩ።

የአገሬውን ተመልካች ደስታ ይበልጥ ከፍ ያደረገው ደግሞ የውድድሩ አዘጋጅ ጀርመን ስኮትላንድን በሰፊ የጎል ልዩነት ማሸነፏ ነው። አምስት ለአንድ በተጠናቀቀው በዚሁ ጨዋታ ወጣቶቹ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የደመቁበት ሆኗል።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልጹምስል Andrew Milligan/empics/picture alliance

ዘንድሮ ከክለቡ ሊቨርኩሰን ጋር የጣምራ ዋንጫ አሸናፊው፥ ፍሎሪያን ቪርትስ በ10ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። ይህም በ21 ዓመት ከ41 ቀኑ ግብ ያስቆጠረ ወጣት ጀርመናዊ አድርጎታል። ከቪርትስ ብዙም በእድሜ የማይበልጠው ሌላው ወጣት ኮከብ ጀማል ሙሲያላ በ19ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

የጨዋታው አጋማሽ ላይ ካይ ሃፈርትስ በፍጹም ቅጣት ምት የጀርመንን ሶስተኛ ግብ አስቆጥሮ እረፍት ሆኗል። በኢካይ ጉንዶሃን ላይ በሰራው ጥፋት ለፍጹም ቅጣት ሰበብ የሆነው የስኮትላንዱ ራያን ፖርትየስ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ስኮትላንዶች በጎዶሎ ተጫዋች ደክመው በተገኙበት ሁለተኛው አጋማሽ፣ ጀርመን ሁለት ተጨማሪ ግቦችን በ68ኛው እና በ93ኛው ደቂቃ በማስቆጠር መክፈቻውን አድምቃለች። ተቀይረው የገቡት አንጋፋው አጥቂ ኒክላስ ፉልክሩግ እና ኤምሬ ቻን የግቦቹ ባለቤቶች ናቸው።

 

ስኮትላንድ በባዶ ከመሸነፍ ያላዳናትን ግብ በ87ኛው ደቂቃ የጀርመኑ ተከላካይ አንቶኒዮ ሩዲገር በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል።

አንጋፋ እና ወጣት ተጫዋቾችን አጣምሮ የተጫወተው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዩሊያን ናግሊስማን ጅምሩ ሰምሮለታል። ከጨዋታው በኋላ በሰጠው መግለጫም ተጫዋቾቹን አሞግሶ፣ ስኮትላንድ በማጣሪያው ከነበራት ጥንካሬ አንጻር ባሳየችው ደካማ እንቅስቃሴ መደነቁን ግን አልሸሸገም።

የስኮትላንድ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ስቲቭ ክላርክ በበኩሉ፣ የቡድኑን ደካማ እንቅስቃሴ ከጀርመን ጋር በማነጻጸር፥ “አልተመጣጠንም” ብሏል።

ወጣቱ ጀማል ሙሲያላ የጨዋታው ኮከብ ሲባል፣ ካሻገራቸው 102 ኳሶች 101ዱ የተሳኩለት አንጋፋው የመሐል ሜዳ ሞተር ቶኒ ክሩዝ በኳስ ወዳጆች ዘንድ እየተደነቀ ነው። ቶኒ ክሩዝ ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን ራሱን አግልሎ ቆይቶ ዘንድሮ መመለሱ ይታወቃል።

ምስል Alessio Marini/IPA Sport/ZUMAPRESS.com/picture alliance

እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ፖርቹጋል እና ስፔን የዋንጫ ግምት የተሰጣቸው አገራት ሆነዋል። ሃያ አራት አገራትን ይዞ መካሔድ የጀመረው እና ለአንድ ወር ያህል የሚቆየው የአውሮፓ ዋንጫ ፍጻሜውን በመጪው ሐምሌ 7/2016 ነው የሚያደርገው። በ10 የጀርመን ከተሞች የሚስተናገደው ይህ ውድድር ጀርመን ራስዋን ለአለም በበጎ የምታስተዋውቅበት አጋጣሚዋም ጭምር ነው ተብሎለታል።

መሳይ ወንድሜነህ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW