የአውሮጳ ገበሬዎችን ያሰጋው የአእምሮ ህመም
ማክሰኞ፣ የካቲት 26 2016
በአውሮጳ ምድር የተሻለ ኑሮ ያላቸው፤ በየሀገራቸውም የሚከበሩና በቂ ምርት የሚያመርቱ ገበሬዎች ነበሩ። ክረምት ከበጋ ወቅቱን ጠብቀው ቅስም ሰባሪው ቅዝቃዜና ናላ የሚያናውዘው ሙቀት ሳይበግራቸው በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች እየታገዙ ያመርታሉ። ሀገር መጋቢዎቹ ገበሬዎች በአሁኑ ጊዜ በመንግሥታት ፖሊሲ ምክንያት ተቆጥተዋል። አደባባይም መጥተው ተቃውሟቸውን መግለጽ ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል። ትራክተሮቻቸውን ሳይቀር አደባባይ ይዘው ተቃውሞ የቀጠሉት የአውሮጳ ሃገራት ገበሬዎች ለጭንቀትና ለአእምሮ ህመም መጋለጣቸውን አንድ ጥናት አመልክቷል።
የገበሬዎች ተቃውሞ በአውሮጳ
የአውሮጳ ሃገራት ገበሬዎችን ወደ አደባባይ ተቃውሞ የገፉ ምክንያቶች እንደየ ሃገራቱ የተለያዩ መሆናቸው ነው የሚነገረው። የጀርመን ገበሬዎች በከፍተኛ ቁጣ በ16ቱም ፌደራል ግዛት ዋና ከተሞች እንዲሁ የፍጥነት አውራ ጎዳናዎች ላይ ትራክተሮቻቸውን ከመደርደር አልፈው የከብቶች ፍግ እንዲደፉ ከገፏቸው ምክንያቶች መካከል በመንግሥት ሲደርግላቸው የኖረው ድጎማ መቅረትና ሚዛናዊ አይደለም ያሉት የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ይጠቀሳሉ። የጎረቤት ኔዘርላንድ ገበሬዎችም መንግሥታቸው ለከባቢ አየር ብክለት ግንባር ቀደሙን የናይትሮጂን ጋዝ ልቀት ለመቀነስ ሦስት አራተኛውን የሀገሪቱን የእንስሳት እርባታ ዘርፍ ለመዝጋት መወሰኑ አስቆጥቷቸዋል። የፈረንሳይ ገበሬዎችን ለተቃውሞ ያስነሳው ጉዳይ ውስብስብ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዋጋ እና የግብር ክፍያ መናር፣ ቢሮክራክሲ፤ መጠነ ሰፊ የአካባቢ ተፈጥሮ ደንቦች እንዲሁም በርካሽ የሚገቡ የምግብ ምርቶች ጋር የገጠማቸው ውድድር የጀርመን፤ የፈረንሳይ፤ የቤልጂየም፤ የኔዘርላንድ፤ የፖላንድ፤ ስፔን እንዲሁም የጣልያን እና ግሪክ ገበሬዎችን ለተቃውሞ አነሳስቷል። ምንም እንኳን በየሃገራቱ የገበሬዎቹ ተቃውሞ መነሻ የተለያየ ቢመስልም በአውሮጳ ደረጃ ግን አንድ የሚያደርጓቸው የጋራ ጉዳዮችም አሉ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ተጽዕኖ
የምሥራቅ አውሮጳ ሃገራት ገበሬዎች ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች ወዲህ የአውሮጳ ሕብረት የዩክሬንን ምርት በብዛት እንዲገዙ በየሀሃራቱ ላይ የጣለው ኮታ አስከፍቷቸዋል። በዚህም ምክንያት የፖላንድ ገበሬዎች ከዩክሬን ጋር የሚያገናኘውን መንገድ በመዝጋታቸው ኪየቭ ከሩሲያ የሚሰነዘርብኝን ጥቃት የመከላከል አቅሜ ላይ ጫና እድርጎብኛል እያለች ነው። የቼክ ገበሬዎችም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። ገበሬዎቹ ከዩክሬን የሚገቡት የእርሻ ምርቶች የገበያው ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደራቸው በላይ የአውሮጳን የአካባቢ ተፈጥሮ ደንቦችን ያልጠበቁና የጥራት ደረጃቸውም ዝቅተኛ እንደሚሆነም ይናገራሉ። ለተቃዋሚዎቹ ከወጡ የፖላንድ ገበሬዎች እንዱ፤
«የዛሬው ተቃውሞ የሚካሄደው ከዩክሬን እና ሩሲያ ወደ አውሮጳ ብቸኛ ገበያ እየጎረፈ ላለው እህል ትኩረት እንዲሰጥ ለማድረግ ነው። ምክንያቱም ይህ እህል ወደእኛ ሀገር ይገባል ሊቱኒያ እና ላቲቪያ ደርሷል፤ ሰነዶቹ ተለውጠው ምርቱ ሁሉንም የጥራት ደረጃዎች ያሟላነው በሚል በመላው አውሮጳ እንደ አውሮጳ ምርት ይከፋፈላል፤ ነገር ግን የንጽሕና ደረጃዎችን አያሟሉም።»
የሚሉትም የግድ ምርቶቹ ይግቡ ከተባለ የጥራት መስፈርቶችን ማሟላት አለባቸው ነው።
«ከዩክሬን የሚመጡ ምርቶችን ለማስቆም ካልሆነም በጣም ውሱን እንዲሆኑ እንፈልጋለን፤ እነዚህ ምርቶች እንዲገቡ የሚፈቀድ ከሆነም ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፤ የፖላንድ ገበሬዎች የሚያመርቷቸውን ምርቶች የጥራት ደረጃ ማሟላት ይኖርባቸዋል።»
ምርቶቹ ወደየሀገራቸው እንዳይገቡ ለማድረግ መንገድ መዝጋት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። የተቃውሞ እርምጃቸው ቶሎ ምላሽ እንዲያገኝም እያሳሰቡ ነው። በፖላንድ እና ጀርመን ድንበሮች አቅራቢያ በጥምረት በሚካሄደው የሁለቱ ሃገራት ገበሬዎች ተቃውሞ የተዘጋው መንገድ አፋጣኝ አዎንታዊ ምላሽ ካላገኘ ለወር ሊዘልቅ እንደሚችል ነው ከተቃውሞው አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት የፖላንድ ገበሬ ስቴፋን ቮይቺክ ባለፈው እሑድ ዕለት የተናገሩት።
«እዚህ ለአጭር ጊዜ ማለትም ለ24 ሰዓታት እንደምንቆይ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ የማስጠንቀቂያ ተቃውሞ ነው። ከመነሻው ለ30 ቀናት ነበር ለማድረግ ሃሳብ ያቀረብነው፤ ሆኖም የመጓጓዣው ዘርፍ ይህን መተላለፊያ እንድንከፍት ጠይቆናል፤ በዚህ የጀርመን ፖላንድ ድንበር መተላለፊያ ክፍት ነው። ዛሬ እሑድ ዕለት ቅሬታችንን አሳይተናል። ለ24 ሰዓት የሚቆይ ተቃውሞ ነው፤ ውጤት የማያመጣ ከሆነ ግን ለረዥም ቀን መቆየቱ አያጠራጥርም።»
ስፔን ውስጥ ለተቃውሞ የወጡት ገበሬዎች ከፖሊስ ጋር የተጋጩባቸው አካባቢዎችም አሉ። በዚህም ምክንያት የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ሀኪም ቤት የገቡ መኖራቸው ተነግሯል። በሀገሪቱ የአየር ንብረትን አስመልክቶ የወጣው ደንብ ገበሬዎቹን አስቆጥቷል።
«እዚህ የምንገኘው ተቃውሟችንን ለመግለጽ ነው፤ ምክንያቱም የእርሻው ዘርፍ ሊንኮታኮት በቋፍ ላይ ይገኛል። ነገሮች እንዲለወጡ ፖለቲከኞች እንዲያደምጡን እንፈልጋለን።»
የገበሬዎች ለአእምሮ ሕመም መጋለጥ
ከፖሊሶች ጋር የአውሮጳ ሕብረት ጽሕፈት ቤት መዲና በሆነችው ብራስልስ ሳይቀር የተጋጩት የአውሮጳ ሃገራት ገበሬዎች ጉዳያችን ትኩረት አላገኘም በሚል ከንዴት ባለፈ ለስነልቡና ቀውስ መዳረጋቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ጀርመናዊው ገበሬ ዩርገን ዶንሀውዘር ብዙ ድካም የሚጠይቀውን የግብርና ሕይወት ለመግፋት አቅም አጥተዋል። የልጃቸው የእርሻ ስፍራ በምሥራቅ ኑረንበርግ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ከቤተሰባቸው ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ነው። ሆኖም ከዓመታት በፊት በቤተክርስቲያን ውስጥ የአባትነት ሚና በመውሰድ ሌላ አገልግሎት ሲጀምሩ በርካታ ገበሬዎች ወደ እርሳቸው በመምጣት የነገሯቸው ታሪክ አስደንግጧቸዋል።
አንዳንዶቹ ለመተኛት የግድ አልክሆል መጠጥ መውሰድ አለባቸው፤ ሃሳባቸውን በመጠጡ ከጭንቅላታቸው አጥበው ለማስወገድ። አንዳንዶቹ አንደውም የባሰው ከመጣ በቃ እራሳቸውን በአቅራቢያቸው በሚገኝ ዛፍ ላይ አንጠልጥለው ሕይወታቸውን መቅጨት እንደሚመኙ ሁሉ እንደነገሯቸው ነው ዶንሀውዘር ለዶቼ ቬለ የገለጹት። «ለ10 እና 15 ትውልድ በቤተሰብ ቅብብሎሽ የመጣ የእርሻ ዘርፍን መዝጋት ማለት ከባድ አደጋ መሆኑን በማመልከትም፤ ገበሬዎች የደረሰባቸውን ጫና «ጭካኔ» የተሞላበት ነውም ይላሉ።
እንዲህ ያለው ችግር ጀርመን ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ተመራማሪዎች ብዙ ያልተነገረላቸውን መሰል ታሪኮች እየመዘገቡ ነው። የሚያቀርቧቸው የመፍትሄ ሃሳቦችም ገበሬዎቹን ወደ አደባባይ የገፏቸው እንደ የአየር ንብረት ፖሊሲ፣ የተለያዩ ደንጋጌዎች፤ የተለያዩ የክፍያ ጭማሪዎች እና የወረደው የምርት ሽያጭ ዋጋ አሳሳቢ የአእምሮ ህመም እንዳስከተለ አመላክተዋል። 250 የአየርላንድ ገበሬዎች ላይ የተካሄደ ቅኝት 20 በመቶዎቹ እራስን የማጥፋት ሙከራ ማድረጋቸውን ያሳያል፤ 40 በመቶዎቹ ደግሞ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንዳሉ አመላክቷል። ቤልጅየም ውስጥም በተመሳሳይ በጥናቱ የተካተቱ 600 ገበሬዎች፣ ሥራቸው ለአእምሮ ውጥረት እንደዳረጋቸው ተናግረዋል። ጀርመን እና ኦስትሪያ ውስጥም ከሚገኙ ገበሬዎች ከአንድ አራተኛ እጅ የሚበልጡት የአእምሮ መዛል እና ለሥራ አቅም የማጣት ስሜት እንዳስቸገራቸው ነው ጥናቱ ያመለከተው።
የአየር ንብረት ፖሊሲና የገበሬዎች ምሬት
አብዛኞቹ ገበሬዎች በተለይም በጀርመን እና ፈረንሳይ ለእርሻው ዘርፍ የሚደረገው ድጎማ ይቆማል መባሉ አደባባይ እንዳስወጣቸው ይናገራሉ። ውሳኔውንም «የግመሏን ወገብ በሸክም እንደመስበር ነው» ሲሉም ይገልጹታል። በዚያም ላይ ገበሬዎቹ በመገናኛ ብዙሃን እንስሳስን እንደምናሰቃይ፤ ነፍሳትም እንደምንገድል ተደርገን መቅረባችን አስመርሮናል ነው የሚሉት።
ዶንሀውዘር «ያለማሰለስ እየተተቸን ነው፤ ይህ ደግሞ ያደክማል» ብለዋል። በደብሊን ዩኒቨርሲቲ የስነልቡና ፕሮፌሰር እና በአየርላንድ በገበሬዎች ላይ የተካሄደው ጥናት ተባባሪ መሪ የሆኑት ሉዊስ ማክሀግ፤ «ገበሬዎቹ ለአየር ንብረት ቀውስ በተዛባ መልኩ ሚናቸው ጎልቶ በየጊዜው መነገሩ ጭዳ እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓል» በማለት የገበሬዎቹን ስሜት ይጋራሉ። በመፍትሄነትም ለሚታየው የአየር ንብረት ቀውስ አንዳች ለውጥ ለማምጣት የገበሬዎቹን ድምጽና ስሜት ማካተት እንደሚበጅ መክረዋል። ከምንም በላይ ደግሞ በቀጣይ ዓመታት ሁላችን በመላው ዓለም ለምንጋፈጠው እውነታ ለአእምሮ ጤና ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል።
የአውሮጳ ገበሬዎች የአደባባይ ተቃውሞ ወደ እስያም ተዛምቶ በተለይ የሕንድ ገበሬዎች መሪዎቻቸው የምርታቸውን ዋጋ ልፋታቸውን ባገናዘበ መልኩ እንዲተምኑ እየጠየቁ ነው። አንድ ወቅት በረሀብ ስሟ በመላው ዓለም የተጠራው ሕንድ በተከተለችው ገበሬዎችን ያማከለ የግብርና ፖሊሲ ምክንያት ዛሬ እህል ከሚልኩ ሃገራት ተርታ ገብታለች። ገበሬዎቿ የማይቀበሉትን የዋጋ ጣሪያ መወሰኗ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ውሎ አድሮ የሚታይ ይሆናል።
ሸዋዬ ለገሠ /ካትሊን ሹስተር
ነጋሽ መሐመድ