1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረት፤ የመካከለኛው ምስራቅ፣ ዩክሬይን እና የሳህል አካባቢ አጀንዳዎች

ማክሰኞ፣ የካቲት 12 2016

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለህብረቱ ወስኝና ፈታኝ ሆነው በቀጠሉት የመካከለኛው ምስራቅ፣ ዩኪረንና የሳህል አካባቢ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተዋል። ሚኒስትሮቹ በእስርቤት ህይወታቸው ያለፈውን የፕሬዝደንት ፑቲን መንግስት ዋና ተቃዋሚ የነበሩትን ሚስተር አሌክሲ ናቫልንይን ባለቤት ተቀብለው አነጋግረዋል ድጋፋቸውም እረጋግጠዋል።

የአዉሮጳ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ እና የአሌክሴይ ናቫልኒ ባለቤት
የአዉሮጳ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ እና የአሌክሴይ ናቫልኒ ባለቤትምስል European Union/Sierakowski Frederic

የአዉሮጳ ህብረት የሚኒስትሮች በመካከለኛዉ ምስራቅ እና በዩክሬይን ጉዳይ ላይ ይበልጥ መክረዋል

This browser does not support the audio element.

የአውሮፓ ህብረት የየካቲት ወር ስብሰባ ዋና ዋና አጀንዳዎች

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሳምንቱ መጀመርያ ሰኞ  ብራስልስ በነበራቸው መደበኛ ስብሰባ በወቅቱ ለህብረቱ ወስኝና ፈታኝ ሆነው በቀጠሉት የመካከለኛው ምስራቅ፣ ዩክሬይን እና የሳህል አካባቢ አጀንዳዎች ላይ ተወያይተዋል። ሚኒስትሮቹ በስብሰባቸው መሀል በቅርቡ በእስርቤት ህይወታቸው ያለፈውን የፕሬዝደንት ፑቲን መንግስት ዋና ተቃዋሚ የነበሩትን ሚስተር አሌክሲ ናቫልንይን ባለቤት ወይዘሮ ዩሊያ ናቫልናያን  ተቀብለው እንዳነጋገሯቸውና ድጋፋቸውም እንደማይለያቸው እንዳረጋገጡላቸው ተገልጿል።

በራፋህ የታቀደው ዘመቻ እንዳይካሄድ የቀረበ ጥሪ

በመካከለኛው ምስራቅ አጀንዳ ላይ ሚኒትሮቹ፤ በተለይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ጦርነቱ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሊቆም ስለሚችልበትና፤ ከሁሉም በላይ ግን እስራኤል በራፋህ ልትክፍተው ባቀደችው ጦርነት ላይ ትኩረት ሰተው መወያየታቸው ታውቁል። ራፋህ በደቡባዊ ጋዝ የምትገኛና ከሁሉም የጋዛ መንደሮች የተፈናቀሉ  ከ 1.2 ሚሊዮን ባላይ ህዝብ የተከማቸባት ከተማ ከተማ ስትሆን፤ ህዝቡ ሌላ መሄጃ የሌለው በመሆኑ ጦርነት  ከተክፍተ ሊደርስ የሚችለውን እልቂት በማሰብ፤  እስራኤል ይህን ከማድረግ እንድትቆጠብ ከየአቅጣቸው ጥሪ እየቀረበ  መሆኑ ታውቋል።  ባለፈው ሳምንት መጨረሽ የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ሚስተር ቦርየል  በቢሯቸው በኩል የእስራልን የራፋህ የዘመቻ ዕቅድ በመቃወም ያወጡትን መግለጫም ከተሰበሰቡት 27 ሚስትሮች 26ቱ የደገፉትና ተመሣሳይ ጥሪም በጋራ ማስተልለፋቸውን  ሚስተር ቦርየል አስታውቀዋል ። “በራፋ የሚከፈት ጦርነት ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ የሚያባብስና እርዳታም እንዳይገባ የሚከለክል በመሆኑ የእስራኤል መንግስት ይህን ጦርነት ከመክፈት እንዲቆጠብ ጠይቀናል በማለት ከአንድ አባል አገር ሚኒስተር በቀር ሌሎቹ  በዚህ ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም ያራመዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዓለምአቀፉ ፍርድቤት ያስተላለፈው ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዴሆን መጠየቁ

ሚኒስትሮቹ የእስራኤል መንግስት የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለማረጋገጥና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስም ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ አሳስበዋል። በተጨማሪም የዓለምአቀፉ ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ ያስተላለፈው ትእዛዝ ተግባራዊ እንዲሆን ለመጠየቅ የተስማሙ መሆኑን ሚስተር ቦርየል በመግለጫቸው አክለው አስታውቀዋል። “ ሚኒስትሮቹ በጃኗሪ 26 የአለማአቀፉ ፍርድ ቤት ያስተለለፈው ውሳኔ አስገዳጅ መሆኑን በማስታወስ፤ ተግባራዊ እንዲሆን የእስራኤልን መንግስት ለመጠየቅ ተስማምተዋል” በማለት የአለምአቀፉ ፍርድ ቤትን ውሳኔ አስገዳጅነት ጠቁመዋል።  

በጋዛ የመንግስታቱ ድርጅትን የሰባዊ እርዳታ አስተባባሪ በስብሰባው በመጋበዝም፤ ባሉት ችግሮችና በተለይም መንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም መርጃ ድርጅት የሚያገኘው ድጋፍ ከቀነሰ ወይም ከተቋረጠ ሊደርስ ስለሚችለው ችግር በጥልቀት የተወያዩ መሆኑም ተገልጿል። እስራኤል  አንዳንድ የድርጅቱ ሰራተኞች ሀማስ በክፈተው ጥቃት ተሳትፈዋል በማለት ባቀረበችው ክስ ምክንያት አሜሪካና ጥቂት የህብረቱ አገሮች የሚስጡትን እርዳታ ለግዜው ማቆማቸው የሚታወቅ ነው።  

የአሌክሴይ ናቫልኒ ባለቤት በአዉሮጳ ህብረት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይምስል Dirk Waem/Belga/dpa/picture alliance

 ለዩክሬን የሚሰጠው እርዳታ ቀጣይነት

በዩክሬን አጀንዳ ላይ ሚኒስትሮቹ ባደረጉት ውይይት የህብረቱ ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በአንጻሩ በሩሲይ ላይ የሚወስዱ ተጨማሪ የማዕቀብና ሌሎች እርምጃዎችንም እንዲቀጥሉ የተስማሙ መሆኑ ተገልጿል። የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ቀናት የቀሩት ቢሆንም፤ አሁንም ግን ይህ ጦርነት በቅርቡ ይቆማል በአካባቢውም ሰላም ይስፍናል ተብሎ እንደማይታሰብ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት።

በሳህል የሰባዊ እርዳታው ይቀጥላል

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹበሳህል አካባቢላይም ተወያይተው ውስናኔዎችን  ያሳለፉ መሆኑን ሚስተር ቦርየል በጋዜጣዊ መግለጫቸው ጠቅሰዋል፤ “ ለቻድ፤ ማውሪታኒያና፤ ጊኒ  የምናቀርበውን የሰባዊ እርዳታ ለመቀጠል ወሰነናል” በማለት ከኦኮዋስ ጋር የሚደረገው ትብብር እንደሚቀጥልና በሌሎቹም መፈንቅለ መንስት በተካሂደባቸው የሳህል አገሮች የሰባዊ እርዳታ ሊደርሥ በሚችልበት ሁኒታ መወያየትቸውን  አስታውቀዋል፡፤

በቀይ ባህር የህብረቱ የባህር ሀይል ስምሪት

የውጭ ጉዳያ ሚኒስትሮቹ በስብሰባቸው መጀመሪያ፤ በቀይ ባህር ላይ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያውኩ የየመን ሀይሎችን ለመከላከል ህብረቱ የራሱን  የባህር ሀይል እንዲያሰማራ የወሰኑ መሆኑም ተገልጿል። 

ገበያዉ ንጉሴ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW