የአውሮጳ ኅብረት እና የኢትዮጵያ የ50 ዓመታት ግንኙነት
ማክሰኞ፣ መጋቢት 2 2017
የአውሮፓ ሕብረት እና የኢትዮጵያ የ50 ዓመታት ግንኙነት
የአውሮፓ ሕብረት በአማራ ክልል ያለው ግጭት ሊቆም እንደሚገባ እና ትግራይ ክልል ውስጥ የሚስተዋለው ሽኩቻ በውይይት እንዲፈታ ፍላጎቱ መሆኑን ገለፀ። ባለፉት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ ድህነትን በመቀነስ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላከናወነችው ተግባር እውቅና ሰጥተናል ያሉት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም፤ ሀገሪቱ አልሸባብን ለመዋጋት እና ቀጣናውን ለመጠበቅ አደረገች ያሉትን ጥረትም በበጎ ጠቅሰዋል። አምባሳደሯ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ሕብረት እና አባል አገሮች የኢትዮጵያ ጠንካራ እና አስተማማኝ አጋር መሆናቸውን ገልፀዋል። ዩናይትድ ስቴስት ይሰጥ የነበረውን ከፍተኛ ድጋፍ ማቋረጡን ተከትሎ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ድጋፍ በማድረግ ረገድ የአለም ማህበረሰብ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲሉም ከአባል ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ቀጣዮቹን 50 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርበን ለመሥራት እንጠባበቃለን
የአዉሮጳ ፊልም ፊስቲቫል በአዲስ አበባ
የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር የሚጋራቸው ብዙ ፍላጎቶች አሉ ያለው ሕብረቱ ከነዚህም ሰላምና ደህንነት፣ ሽብርተኝነትን መከላከል ብሎም ቀጣናዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ማሳለጥ ይገኙበታል። በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም የአውሮፓ ሕብረት እና የኢትዮጵያ የ50 ዓመትታት የግንኙነት ምዕራፍን አስመልክተው ከአባል ሀገራቱ አምባሳደሮች ጋር ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ "የአውሮፓ ሕብረት እና አባል ሀገሮቻችን የኢትዮጵያ ጠንካራ፣ አስተማማኝ አጋር ናቸው" ብለዋል። ሕብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርገው የጋራ ትብብር በየዓመቱ በልዩ ልዩ መስኮች የሚገለጥ 1 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ የትብብር ሥራ እንዳላቸው አስታውቀዋል። የአውሮፓ ሕብረት በናይል ወንዝ ላይ የያዘው አቋምና ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአውሮፓ ሕብረት ዋነኛ አጋሮች መካከል አንዷ ነበረች ሆናም ቀጥላለችም ብለዋል። አጋርነታቸውም በልማት ትብብር እና ምቹ የንግድ ሁኔታዎች ላይ ሆኖ "ከጦር መሣሪያ በስተቀር በሁሉም ነገር" ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰዋል። "ባለፉት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያ ድህነትን በመቀነስ፣ በኢኮኖሚ እድገት እና በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ለምታከናውነው ተግባር እውቅና ሰጥተናል።
ኢትዮጵያ በመላው አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ላይ የምታደርገውን ገንቢ ሚና ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን። በ2020 እና 2022 መካከል የነበረው የኢትዮጵያ አሳዛኝ ግጭት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችንን ፈትኖታል። የሆነ ሆኖ የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን ሕዝብ አልተወም። በችግሩ አካባቢዎች ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አድርጓል። የአውሮፓ ሕብረት የሀገሪቱን የሰላም ሂደት በንቃት ደግፏል። እናም ለትጥቅ ማስፈታት፣ ለሽግግር ፍትሕ እና ለሀገራዊ ምክክር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በፍጥነት ተንቀሳቅሰናል።" ብለዋል። የሰመጉ እና የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን ውይይት
አምባሳደሯ አሁንም በአማራ ክልል ያለው ግጭት ሊቆም እንደሚገባ እና ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ሽኩቻም በንግግር እንዲፈታ የሕብረቱ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሰዋል። "ስለ አማራ ክልል፣ የአማራ ጥቃት መቆም አለበት የሚለውን መልእክት በሁሉም አማራጬች እየገለጽን ነው። በተጨማሪም ተዋናዮችን ወደ ውይይት ለማምጣት የሚሞክሩ አንዳንድ ሂደቴች ቢኖሩም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሁከት መፍትሔ አይሆንም። በትግራይ ክልል ያለው ችግርም በውይይት ብቻ መፍታት እንዳለበት መልዕክቱን በማስተላለፍ ላይ ነን። ብጥብጥ መፍትሔ አይሆንም።"
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው መረጋጋት እና ደህንነት የአውሮፓ ኩባንያዎች ሀብት ፈሰስ ለማድረ እንዲችሉ፣ ሥራ ለመፍጠር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አውስተዋል። በዚህ ሁከት በነገሠበት ባሉት ጂኦ ፖለቲካዊ ዘመን ይህ ከመቼውም ጊዜ በላይ ያስፈልጋልም ብለዋል። ወሳኝ ድርሻ የነበረው የአሜሪካ ድጋፍ መቋረጥን በተመለከተ ሕብረቱ የሚያደርገውን የተጠየቁት አምባሳደራ ዓለም ለዚህ ምላሽ ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል።
"እኛ እንደ አውሮፓ ሕብረት ዘላቂ ልማትን ለማበረታታት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀውስን ለመቅረፍ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን በመደገፍ ግንባር ቀደም ነን። ነገር ግን አሁን ያለው የዓለም አቀፍ ፍላጎቶች ስፋት እና ውስብስብነት ብሎም አሁን እንደ ዓለምአቀፋዊ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያም በእርግጥ የጋራ ምላሽ የሚሻ ነው። እናም ሁሉም የዓለም ማህበረሰብ ክፍተቶቹን በገንዘብ በመደገፍ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ማረጋገጥ አለብን እላለሁ።"
በቅርቡ ደግሞ ያህል ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሲቪክ ምህዳር እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል። አምባሳደሯ ይህንን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "ምህዳሩ ሊከፈት ይገባል፣ የወጣቶችን የተለያዩ ድምጾችም ማድመጥ ያስፈልጋል" ብለዋል። ሕብረቱ በኢትዮጵያውያን ላይ የጣለውን ጥብቅ የቪዛ አሰጣጥ ሥርዓት ለማላላት እየሰራንበት ነው ያሉት አምባሳደር ሶፊ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና በአውሮፓ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አውሮፓ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህንንም ጉዳይ በቅርበት እየተከታተልነው እንገኛለን ሲሉም መልሰዋል። በመግለጫው ላይ የተገኙ የኢትዮጵያ ተወካይ አውሮፓ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቀጣናዊ ደህንነት እና በዓየር ንብረት ለውጥ ላይ በላቀ እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ