የአውሮፓ ኅብረት የ2023 የዓመቱ የመጨረሻ የመሪዎች ጉባኤ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 5 2016
የ27ቱ የአውሮፓ ኅብረት የጎርጎሳዊው ዓመት 2023 የመጨርሻ ጉባኤ ትናንት ሐሙስ ማለዳ ጀምሮ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረብት ዓርብ ከቀትር በኋላ ድረስ ብራስልስ ላይ እየተካሄደ ነው። ዩክሬንና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ መሪዎቹን የሚያከራክሩና ምናልባትም ጉባኤው ከታሰበለት ቀን እንዲገፋ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ሲነገር ቆይቱል። ጉባኤው ከዚህ ቀደሞቹ ስብሰባዎች በተለየ ሁኒታ ወሳኝና አስጨናቂ ስለመሆኑ ከሚናገሩት ውስጥ የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስተር ሚስተር ሊኦ ቫራድካር ይገኙበታል። « ባለፉት ስድስትና ሰባት ዓመታት የአውሮፓ ኅብረትን ጉባኤ ተሳትፌያለሁ ይሁንና እስካሁን ከተገኘሁባቸው ጉባኤዎች በተለይ በዩክሬን በሚተላለፈው ውሳኔ ምክኒያት ይኸኛው ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው» በማለት ዩክሬን የኅብረቱን መግቢያ ንግግር እንድትጀምር የቀረበውን ጥያቄ በአዎንታዊ መቀበል አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናገረዋል።
የዩኪረን የመግቢያ ንግግር Accession talks)ጥያቄና የሀንጋሪ ተቃውሞ
ላለፉት ሀለት ዓመታት ከሩሲያ ጋር በጦርነት ውስጥ የምትገኘው ዩክሬን ባለፈው ስኔ ወር የኅብረቱን እጩ አባልነት ደረጃ ያገኘች ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የመግባቢያ ድርድር እንድትጀምር የሚያስችላትን መስፈርት ስላሟላች እንዲፈቀድላት ነው ለጉባኤ የቀረበው ጥያቄ። ሆኖም ግን ሀንጋሪ ዩክሬን ቅድመ ሁኔታዎችን ሳታሟላ በተለየ ሁኒታ የመግቢያ ንግግሩን እንድትጀምር መፈቀዱ ትክክል አይደለም በማለት ስትቃወም ቆይታለች።
በመግቢያ ንግግሩ ጥያቄ ላይ የተስጠው ውሳኔ አንደምታ
በዚህ ሁኔታ በውጥረት የተጀመረው ጉባኤ ሲካሄድ ውሎ ምሽት ላይ ግን የጉባኤው ሰብሳቢ ሉዊ ሚሸል ጉባኤውን አቋርጠው ወደ ጋዜጠኖች በመዝለቅ «ይህ ታሪካዊ ኁነት ነው። የአውሮፓ ኅብረትን ተአማኒነት ያረጋገጠ» በማለት ዩክሬንና ሞልዶቫ መግቢያ ነግግሩን እንዲጀምሩ የተወሰነ መሆኑን አስታውቀዋል። የአውሮፓ ኅብረት ይህን ውሳኔ ባለመወሰን ታሪካዊ ስህተት እንዳይሠራ ሲማጸኑ የቆዩት ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ ውሳኔው ለዩኪሬንም ለአውሮፓም ትልቅ ድል ነው በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል። ውሳኔው ዩክሬንን ወዲያውኑ የህብረቱ አባል ባያደርግም፤ የውሳኔው ውድቅ መሆን ግን፤ ለዩክሬን ትልቅ የሞራልና የፖለቲካ ውድቀት ሊሆንና ለሩሲያ ደግሞ ድል ሊሆን ስለሚችል ነው የብዙዎች ጭንቀት የነበረው።
የክርክሩ ሂደትና ከውሳኔ የተደረሰበት ሁኒታ
በዚህ ሁኔታና በኅብረቱ አሠራር ከዚህ ስምምነት እንዴት ሊደረስ እንደቻለ የተጠየቁት የኔዘርላንድሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ማርክ ሩተ ለጋዜጠኞች ሲገልጹ፤ «ከፍተኛ ክርክር ነው የነበረው። ከስምምነት ላንደርስ እንዳንችልም ሰግቼ ነበር፤ በመሀል ግን ኦላፍ ሹልዝ «ፈቃድህ ከሆነ የስብሰባውን አዳራሽ ብትለቅልንና ውሳኔውን ያላንተ ለማሳለፍ ብንችል» በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ኦርባንም በመቀበላቸው በ26ቱ አባል አገሮች መሪዎች ስምምነት ውሳኔው ሊያልፍ መቻሉን አስረድተዋል። ኦርባን ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ሀንጋሪ የዚህ ትክክል ያልሆነ ውስኔ አባል አትሆንም በማለት አሁንም ተቃውሟቸውን ቢገለጹም፤ ሌሎቹ አባል አገሮች ግን ውሳኔውን እንዳያልፉ ሳያግዱ ቀርተዋል።
የታገደው የዩክሬን የገንዘብ እርዳታ
ከዚህ ውሳኔ በኋላ ለዩክሬን ሊሰጥ በታቀደው 50 ቢሊዮን ዩሮ ላይ ግን አሁንም ሀንጋሪ በመቃወሟ ውሳኔ ሳይሰጥበት ቆቷል። ዩክሬን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ያለባት በመሆኑና ከአሜሪካ የምትጠብቀው የ60 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ በምክር ቤቱ በመታገዱ የኅብረቱ ድጋፍ ወሳኝ ቢሆንም በሀንጋሪ ተቃውሞ ገንዘቡ ሊልቀቅ አልቻለም። ልዩ የመሪዎቹ ስብሰባ በመጭው ጥር ወር ተጠርቶ በዚህ ጉዳይ ውሳኔ የሚያሳልፍ ስለመሆኑ ግን ተገልጿል።
በጋዛ ቀውስ ላይ የኅብረቱ አቋም
ሌላው የጉባኤው ዋና አጀንዳ በሆነው የመካክለኛው ምሥራቅ ጉዳይ የኅብረቱ አገሮች አንድ አይነት አቋም አለማያዛቸው በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድ ክፉኛ ያስተቻቸው መሆኑን በተለይ የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስተር የገለጹ ሲሆን፤ የቤልጀየም ጠቅላይ ሚኒስተር ዴክሮ በስጡት አስተያየትም፤ በእስራኤልና ፍልስጤም ጉዳይ የኅብረቱ ትኩረት እየደረሰ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ማስቆም መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። «የእኛ ትኩረት መሆን ያለበት በሁሉም ወገኖች ላይ የሚደርሰው የስዎች ስቃይ እንዲቆም ማድረግ ነው። በዚህ ላይ የጋራ አቋም መውስድና የሚጠበቅብንን መፈጸም ይኖርብናል።» በማለት ይህን በማደረግ ሁኔውን መቆጣጠር ካልተቻለ ችግሩ ከአካባቢው አልፎ አውሮፓም ሊደርስ እንደሚቺል አስገንዘበዋል። እንዲያም ሆኖ ይህ ዘገባ እስክተጠናቀረበት ዓርብ ማምሻውን ድረስ የኅብረቱ መሪዎች በዚህ አጀንዳ ላይ ያሳለፉት ውሳኔ አልታወቀም።
ገበያው ንጉሤ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ