1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውደ ዓመት ሸመታ በአዲስ አበባ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 29 2015

ወይዘሮ መሠረት ጉዲሳ ለገና በዓል ጉድ ጉድ ሲሉ በጀሞ ገበያ አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት በ90 ብር፣ ቀይ ሽንኩርት በ18 ብር ገዝተዋል። ዶሮ እስከ 350 ብር፣ እንቁላል በ8 ብር የሚሸጠው የጨፌ የወጣቶች ሁለገብ የኅብረት ሥራ ማኅበር አባል ሰለሞን ጎብዬ በገበያው የሚታየው የዋጋ ልዩነት በፈላጊ እና ተፈላጊ አለመገናኘት የተነሳ እንደሆነ ይናገራል

Äthiopien Weihnachtsmarkt in Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

የበዓል ገበያ ፣ አቅርቦቱ እና ሸማቹ በአዲስ አበባ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ጎልቶ ከሚከበሩ አውደ ዓመቶች አንዱ በሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መታሰቢያ በገና በዓል የአውደ ዓመቱ ሸመታ እና ግብይቱ ይደምቃል፡፡ በነዚህ አይነት ትላልቅ በዓላት የሸማቹ የመግዛት ፍላጎት ከወትሮም ከፍ ብሎ መታየቱ ደግሞ ከሚፈጥረው የገበያ ውክቢያ በተጨማሪ አልፎ አልፎ የአቅርቦት እጥረት ሲያጋጥሙ የዋጋ ግሽበቱም ሸማቹን ቆንጠጥ ማድረጉ አይቀረ ነው፡፡

ይሁንና በዘንድሮ የገና በዓል ሸመታ በበርካታ የበዓሉ ግብዓቶች ገቢያ ላይ ከቅርብ ጊዜያቱ የበዓል ግብይት ጋር ሲነፃፀር እምብዛም የማያስመርር አቅርቦት እና ሸመታ መስተዋሉን ሰምተናል፡፡

ለዚህ ደግሞ አይነተኛ ሚና ተጫውተዋል ተብለው ከሚታመነው አንዱ የህብረት ስራ ማህበራት ለበዓላት እና አጠቃላይም ለፍጆታ የሚውሉ ምርቶችን ለገቢያው በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ መጣራቸው ነው ይባልለታል፡፡

ወጣት ሰለሞን ጎብዬ ጨፌ የወጣቶች ሁለገብ የህብረት ስራ ማህበር አባል ሲሆን፤ አዲስ አበባ ጀሞ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የዘንድሮ የገና በዓልን ምክኒያት በማድረግ በብዛት የተመረቱትን የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በገፍ ለገቢያተኛው ሲቸበችብ ተመልክተነዋል፡፡ ወጣቱ 12 ሺህ 500 አባላት ባሉት የህብረት ስራ ማህበሩ ታቅፎ መንቀሳቀስ ከጀመረ ገና ውስን ጊዜያት ቢያልፉም ማህበሩ የተለያዩ ጥራጥሬ፣ ፍራፍሬዎች እና የእንስሳት ተዋጽኦን በማምረት ገቢያውን ማረጋጋት ላይ ጉልህ ድርሻ እያሳረፈ መሆኑንም ያወሳል፡፡

የበዓል የእህል ገበያ በአዲስ አበባምስል Seyoum Getu/DW

“ምርቶቻችንን ገዝተን ሳይሆን እያመረትን ነው ለገቢያ የምናቀርበው፡፡ ወደ አዲስ አበባም በአምስቱም በር ምርት እናቀርባለን፡፡ ከጥራጥሬ አሁን ጤፍ በኪሎ ከ10 ብር በላይ ዝቅ ባለ ዋጋ ከፍ ሲል እስከ 52 ብር ነው የምንሸጠው፡፡ ስንዴ በኪሎ 40 ብር ሲሆን ምስር 100 ብር እንሸጣለን፡፡ ቀይ ሽንኩርት በመደበኛው ገቢያው ከ20 ብር በላይ ቢሆንም እኛ ጋ በደረጃው ከ12 እስከ 18 ብር ይሸጣል፡፡ ዶሮ 350 ብር ብቻ ነው የምንሸጠው፡፡ ፍየልም እንደምታየው ከመካከለኛ እስከ ደህና ይዞታ አሉ፡፡ ከ3 ሺህ 500 እስከ 500 ብር ነው የሚሸጡ፡፡ በውጪ ገቢያ ከፍተኛው እስከ 7 ወይም 8 ሺህ ሊያወጣ የሚችል ነው፡፡ እንቁላልም በ8 ብር ነው አምርተን ለገቢያ ያቀረብነው” በማለት መሰል ማህበራት ገቢያውን በማረጋጋት ረገድ ያለውን ሚና አስረድተዋል፡፡

ሰኚ ደሹ ደግሞ የህብረት ስራ ማህበሩ መስራች እና ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ማህበሩ ቀዳሚ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው ገቢያን በማረጋጋት ተጠቃሚዎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደ መሆኑ ምርቶቹ በሚከፋፈሉባቸው ሁሉም ጣቢያዎች ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡

ወ/ሮ መሰረት ጉዲሳን በዚሁ ማህበር ለገቢያ የቀረቡ ሽንኩር እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን ሲሸምቱ ነው አግኝትን ያነጋገርናቸው፡፡ “ምርቶቹ ጥራት ያላቸው እና ዋጋቸውም ተመጣጣኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ሽንኩር ውጪ እስከ 23 ብር ገደማ ቢሆንም እዚህ ኪሎውን አንደኛውን ደረጃ በ18 ብር አግኝቻለሁ፡፡ አንድ እንቁላል ላይም ከ3-4 ብር ቅናሽ አለ” በማለትም ገልጸዋል፡፡

የበዓል ገበያ ድባብ፤ አዲስ አበባምስል Seyoum Getu/DW

ኢትዮጵያ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ለሁለት ዓመታት የቆየችበትን ጦርነት ዘንድሮ ተስፋ ሰጪ በሆነ መልኩ በሰላም እየቋጨች መሆኑ ከዚህ ቀደም የበዓላት አከባበር ላይ የሚያርፈው ጥላ በመጠኑም ቢሆን ቀንሶ ታይቷል፡፡ አዲስ አበባም የዘንድሮውን የገና በዓል ሳምንቱን በሙሉ በየቦታው በተሰናዱ አውደ ርእዮች ተጨናንቃ ነው ያሳለፈችው፡፡ ድባቡም ቢሆን የተሻለ ድምቀት ያለው ሆኖ ተስተውሏል፡፡

በአውደ ርእዮችም የተለያዩ የፍጆታ እቃ ሲቀርቡ ከወትሮ ዋጋቸው ጎምዘዝ ብለው የተስተዋለው የአልባሳት ዋጋ ነው፡፡

በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው የንግድ ትርዒት ለበዓሉ ማድመቂያ የሚውሉ የስጦታ እቃዎች በመሸጥ የተሰማራችው ህሊና ውብሸት የበዓሉን ድባብ በመግለጽ ነው አስተያየቷን የጀመረችው፡፡ “ድባቡንም ሲታየው ካለፉት ከቅርብ ጊዜያቱ በዓላት ደስ የሚል ደመቅ የማለት አዝማሚያ አለ፡፡ ባሁኑ የገቢያ መረጋጋቱም የተሸለ ሆኖተመልክቸዋለሁ፡፡ ነጻ እና የተሻለ እንቅስቃሴ ነው ያስተዋልኩት” ስትልም አስተያየቷል አብራርታለች፡፡

በዓል ማድመቂያ ከሆኑ ግብይቶች አንደኛው የሆነው ዶሮ በመደበኛው የአዲስ አበባ ገቢያ ከ800-1000 ብር ሲሸጥ ተስተውሏል፡፡ የበግ እና የፍየል ዋጋ ደግሞ ከ3000 እስከ 10 ሺህ እንደየደረጃው ተሽጠዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW