የአዕምሮ መታወክ ያስከተለው የኬንያ ተቃዉሞ እና የዛምቢያ የሳይበር ህግ ድጋፍ እና ተቃዉሞ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 5 2017
በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በእስር ላይ እያለ ህይወቱ ያለፈው የ31 ዓመቱ ጦማሪ እና መምህር የአልበርት ኦጃዋንግ ጉዳይ ኬንያ ውስጥ በርካቶችን ለሞት የዳረገ ብርቱ ቁጣና ብጥብጥ ቀስቅሷል። ባለፈው ወር ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ/ም መዲናዪቱ ናይሮቢ ውስጥ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ሰዎች መካከል ደግሞ ወጣቷ ዌንዲ ትገኝበታለች። ዌንዲ ወደ ተቃዉሞው አደባባይ ለመውጣት በርግጥ ድፍረት የሚጠይቅ እና ምናልባትም ሕይወቷን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነበር። ይህ ደግሞ በተለይ የኬንያ መንግስት ለተቃዉሞ አደባባይ የሚወጡ ሰዎችን ለማስቆም እየወሰደ ያለው ያልተመጣጠነ እየጨመረ በሄደበት ወቅት በመሆኑ በርግጥ አስፈሪ ነበር።
መጀመሪያ ላይ፣ በፍራቻ ምክንያት ከቤት መውጣት እንደማትችል የምትናገረው ወጣቷ በተለይ በዚህ ጊዜ ጥቃቶቹ ሴቶች ላይ ማነጣጠራቸውን ትገልጻለች ይህ ደግሞ ወጣት ተቃዋሚ ኬንያውያኑ በፍራቻ እንዲያዙ እና ነገሮችን በስጋት እንዲመለከቱ እያስገደዳቸው መምጣቱን ነው ወጣቷ ተቃዋሚ የምትናገረው።
" እና ላልፈራ ነው? አዎ እፈራ ነበር፤ ለዚያውም ብዙ ጊዜ። በርግጥ እኔን የገጠመኝ ሌሎችን ላይወክል እንደሚችል አውቃለሁ ።ነገር ግን ወደ ተቃውሞ ለመሄድ ከቤት ስወጣ አብዛኛውን ጊዜ በፍራቻ ውስጥ ሆኜ ነው።»
የሆነ ሆኖ ዌንዲ በዕለቱ በርካቶች ከተገደሉበት እና ሌሎች በርካቶች ጉዳት ካስተናገዱበት የሰኔ 17ቱ ተቃዉሞ በሰላም ወደ ቤቷ መመለስ ችላለች።
በዕለቱ በመላው ሀገሪቱ ባለፈው ዓመት በመንግስት ላይ የተደረገውን ሀገር አቀፍ ብርቱ ተቃዉሞ ለመዘከር አደባባይ ከወጡ ኬንያዉያን መካከል ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት 19 ሰዎች ተገድለዋል።
ሀገሪቱ ከገጠማት የኤኮኖሚ ችግር ባሻር ፖሊስ በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የተከተለው የጭካኔ መንገድ ለፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግስት አስተዳደር ብርቱ ተግዳሮት ሆኗል። ይህ ደግሞ በተለይ በወጣት ተቃዋሚዎች የሚመሩ ሰልፎች በመላው ሀገሪቱ እንዲቀጣጠሉ እና አሁን ሀገሪቱ ያለችበት ተጨባጩ የፖለቲካ ምህዳር መገለጫ ሆኗል።
ኬንያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ መቃወም ከስጋት በላይ መሆኑን የምትናገረው ዌንዲ አሁን አሁን መቃወም በራሱ በአዕምሮ ጤና ላይ ጉዳት እንደመጋበዝ ነው ትላለች።
የኬንያ የተቃዉሞ ሰልፎችን የሚያሳዩ ናቸው የተባሉ የውሸት ምስሎች እና ቪዲዮዎች
ጥቃቱ አሁን አሁን በወጣት ተቃዋሚዎቹ ላይ ብርቱ ፍርሃት እና ጭንቀት እየፈጠረ ፤ በቀጣዩ የህይወታቸው ምዕራፍ ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ ሊያሳድር ለሚችል የጤና እክል እንደዳረጋቸው ነው ስትል በርሷ ላይ የደረሰውን በምሳሌነት ትጠቅሳለች።
« ከአእምሮ እና ስሜታዊ ጤንነቴ ጋር እየታገልኩ ነው። አንዳንድ ቀናት በጣም የተሸነፍኩ ያህል ይሰማኛል። አንዳንዴም ምንም መጨመር እንዳልቻለ ነው ከንቱነት ይሰማኛል። ለትግሉ ምን አበረከትኩ ብዬም ራሴን እጠይቃለሁ ።»
ለተቃዉሞ አደባባይ ከወጡ ወጣት ኬንያዉያን መካከል አሌክስ ሙቱዋ አንዱ ነው። አሌክስ እንደሚለው በየሰላማዊ ሰልፉ እና በየፖለቲካው ስብሰባ ላይ ያለውን ስጋት ሲገልጽ "ለሀገሬ ለመታገል በወጣሁ ቁጥር በፖሊስ ጥቃት ይደርስብኝ ይሆን በሚል ስጋት ውስጥ ሆኜ ነው" ይላል።
"እንደ አንድ ወጣት ኬንያዊ፣ እኔም የሰላማዊ ሰልፉ አካል ነኝ። ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ብቻ የምንሻ ተቃዋሚዎች። የዚያ ተቃውሞ አካል መሆን እና ፖሊስ ለተቃውሞው የሚሰጠውን ምላሽ ማሰቡ ደግሞ በጣም አስፈሪ ፈተና ነው። "
ኢሬኔ ሙዋሪ ናይሮቢ ውስጥ በተከታታይ ለተቃዉሞ አደባባይ ከሚወጡ ወጣቶች መካከል አንዷናት ። ኢሬኔ እንደምትለው በተቃዉሞ ሰልፎቹ ላይ በስሜት የሚወጡ ወጣቶች ዋጋ እየከፈሉ ነው። ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱ በርግጥ አሳሳቢ ነው ትላለች።
" አንዴ ተቃዉሞ ሰልፍ ላይ እሳተፋለሁ ብዬ ከቤት ከወጣሁ በሰላም ወደ ቤት መመለሴን እርግጠና አይደለሁም ። በዚህ ወቅት ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን በቀጥታ ጥይት እየተኮሰ ነው ። እናም ዕድለና ከሆንክ ብቻ ነው ከጥይቱ ማምለጥ የምትችለው ። መንግስት ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ለማደናቀፍ እንዲህ እያደረገ ነው። "
ትኩረት በአፍሪቃ፤ ኤኮዋስ ለሕልዉናዉ እየታገለ ነዉ፤ የኬንያ ተቃዉሞ ሠልፈኞች ፅናት
በመንግስት ላይ ተቃዉሞ ለማሰማት አደባባይ በሚወጡ ሰዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ እየጨመረ መሄዱ በቀጣናው የተሻለ ዴሞክራሲ አላት ለምትባለው ሀገር ፈተና ሆኗል። ዜጎች አሁን አሁን መንግስትን በአደባባይ መቃወም እስከ ሞት የሚደርስ ጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው። ልጆቻቸው የተገደሉባቸው ወላጆች ፣ ጓደኞቻቸው በአደባባይ ሲገደሉባቸው ያዩ ወጣቶች የአዕምሮ እና የስሜት ጉዳት ውስጥ መሆናቸውን ነው እየገለጹ ያሉት ። ይህ ደግሞ በአንድ ጊዜ ከሁለት ነገሮች ጋር ግብግብ ስለመግጠማቸው አመላካች መሆኑን ነው የሚያነሱት።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት እንደሚሉት ግን የኬንያው መንግስ ተቃዋሚዎችን ለመግታት እየወሰደ የሚገኘው የተቃዉሞውን ዳራ ያሰፋበት ይሆን እንጂ ተቃዋሚዎችን ዝም ማሰኘት ይችል እንደሁ እርግጠኞች አይደለንም እያሉ ነው።
ነገር ግን ለጤናማ የፖለቲካ ስረዓት ተቃዉሞዎች ተጠባቂዎች በመሆናቸው ከፍራቻ ነጻ የሆነ እና የአዕምሮ ጤና የተጠበቀ እና ለመብቱ የሚሟገት ዜጋ እንዲኖር ተገቢው ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ እየተጠየቀ ነው።
የሀገሪቱ መንግስትም ከዴሞክራሲያዊ መርህ ባሻገር ተቃዉሞዎችን ለማፈን የሚወስዳቸውን መሰል እርምጃዎችን እንዲገታ ከመጠየቅ ባሻገር ዜጎች ሳይሸማቀቁ ስለ መብታቸው በሰላም መጠየቅ «የአዕምሯቸው ደህንነት መጠበቅ አለበት » የባለሞያዎች መልዕክት ነው።
የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ የ2025 የሳይበር ደህንነት እና ስራ ላይ የዋለውን የሳይበር ወንጀሎች ህግ ከፈረሙ እነሆ ሶስት ወራት ሊሞላቸው ነው።
ፕሬዚዳንቱ ዲጅታል ወንጀሎችን ለመዋጋት እና የሃገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ለማስጠበቅ የወሰዱት ርምጃ ከደጋፊዎቻቸው ተራማጅ ሃሳብ እና ውሳኔ ተብሎ ጠንካራ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።
በዚያው ልክ ግን የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚወሰዱ ርምጃዎች ኢ ዲሞክራሲያዊ ናቸው የሚሉ የመብት ተሟጋቾች እየተደመጡ ነው። ህጎቹን ለማስከበር የሚወሰዱ ርምጃዎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመናገር መብትን የሚገድቡ ናቸው ሲሉ በፕሬዚዳንቱ ላይ ወቀሳ ማቅረብ ጀምረዋል።
ዛምቢያ ተግባራዊ ያደረገቻቸው እነዚሁ የሳይበር ደህንነት ህጎቹ የስልክ ጥሪዎችን ጨምሮ፣ ኢሜይሎች፣ መልዕክቶችን እና የክትትል ይዘቶችን ጨምሮ ሁሉንም የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነቶች ለመጥለፍ እና ለመከታተል ይፈቅዳሉ።
በተጨማሪም ህጎቹን ተላልፎ የተገኘ ሰው እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት እስከ መቀጣት የሚያደርስ ከባድ ቅጣት ሊቀጣ ከመገደዱ ባሻገር ለውጭ ሃገራት ተላልፍ እንዲሰጥ እስከ መፍቀድም ይደርሳል ነው የተባለው።
ይህኑኑ ለማቀላጠፍም ገለልተኛ የመንግስት ተቋም ሆኖ ይሰራ የነበረው የዛምቢያ የሳይበር ደህንነት ኤጀንሲ አሁን በፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት ስር እንዲተዳደር መወሰኑ ጉዳዩ ለመክበዱ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል።
የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ እና ትብብር ሚንስትር ሙላምቦ ሃይምቤ ይህንኑ ለመከላከል በሰጡት ሃሳብ እንዳሉት ህጉ የዜጎችን ደህንነት በግንኙነት መስመሮች ላይ ከመጠበቅ ያለፈ መሰረታዊ የጻነታቸው እና መብታቸውን ለማፈን ያለመ አይደለም ብለዋል።
"የሳይበር ሕጎች ለማፈን ታስበው የተዘጋጁ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ እና ወደ ግላዊ ጉዳዮች ይገባል የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አይደለም ። በትክክለኛው አውድ ውስጥ መቀመጥ አለበት ። የመንግስት ዓለማ ማንኛውንም ግንኙነት መጥለፍ እና መግባት ነው ከሚለው በተቃራኒው መታየት ነው ያለበት "
የገዢው ዩናይትድ ፓርቲ ለብሔራዊ ልማት (UPND) የሚዲያ አማካሪ ኦሊቨር ሻላላ ሴፒሶ እንዲሁ አዲሱን የዛምቢያ የሳይበር ህጎች ይከላከላሉ። ህጉ ዜጎችን መሰለል የሚደግፍ ሳይሆን የዲጂታል ወይም የመረጃ ደህንነትን መጠበቅ ብቻ ታላሚ ያደረገ ነው ነው ይላሉ።
በአንጻሩ ግን ተግባራዊ የተደረጉ ሕጎቹ ዛምቢያውያንን ከዲጂታል ወንጀሎች እና ከማንነት ስርቆት ለመጠበቅ የታቀዱ ቢሆኑም ብዙም ተቀባይነት እንዳላገኙ እየተነገረ ነው። ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት የቀረበው ደግሞ የህጉን ዝርዝር ሁኔታ በተመለከተ በቂ ትምህርት እና ግንዛቤ ስላልተሰጠበት ነው የሚል ወቀሳም ቀርቦበታል። አብዛኛው ዜጋ ስለ ህግ መውጣት እና አንድምታውን በመለከተ በሀገሪቱ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መስማቱን መረጃዎች የሚያሳዩት ።
በኢሜይል የሚመጡ የመረጃ ስርቆቶችን እንዴት እንከላከል?
በውጭ የሚገኙ አንዳንድ የሀገሪቱ ዜጎች በበኩላቸው ህጉ ጣልቃ ገብ ነው በማለት አጥብቀው እየኮነኑ ነው ።
የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል የሳይበር ህግ ያስፈልጋል የሚሉት የዛምቢያ ጦማሪያን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሪቻርድ ሙሎንጋ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ ህጎች አስፈላጊ ቢሆኑም ከዚያ ባሻገር የሚመጡ ነገሮች ናቸው አሳሳቢ የሚሆኑት።
«ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የመገደብ አቅም ያላቸው አንዳንድ ድንጋጌዎች ለምሳሌ ስብሰባ ፣ ማህበር እና ሰፋ ያለ የዲጂታል መብቶች አሉ።»
የዛምቢያ የህግ ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ሉንጊሳኒ ዙሉ በበኩላቸው ማህበራቸው አዲሱን ህግ በፍርድ ቤት እንደሚሟገት ነው ያስታወቁት ።
"አሁን ህግ የሆነው በርካታ ድንጋጌዎች የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚጋፉ፣ የነጻ ፕሬስን የሚያደናቅፉ እና በአገራችን የተከበረውን ዲሞክራሲ የመናድ አቅም ያላቸው ናቸው።"
አዲሱ ህግ በጎርጎርሳዉያኑ 2021 በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ጸድቆ ተግባራዊ የተደረገውን የሳይበር ደህንነት እና የሳይበር ወንጀሎች ህግን ይተካል ነው የተባለው። ህጉ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የሀገሪቱ ፖሊስ በመንግስት ባለስልጣናት እና ተቋማት ላይ የሚያፌዝ እና የሚያንጓጥጡ ምስሎች እና ቪዲዮዎች ማጋራቱን ተከትሎ ታዋቂውን ኮሜዲያን ምቤዌ ሲባጄኔን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በቁጥጥር ስር አውሎታል። ምስሎቹ የመንግስት ሹማምንትን ከመሳደብ ባለፈ ስም አጥፊ እና በመንግስት ላይ ብጥብጥ እንዲነሳ ያለመ ነበር የሚል ክስ በኮሜዲያኑ ላይ ቀርቦበታል።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ሄችሌማ ህጉ የመንግስት የመከታተያ መሳሪያ ነው ፤ በማለት ነው የነቀፉት። እንደዚያም ሆኖ ግን በሀገሪቱ ጥብቅ የሳይበር ደህንነት ህግ መውጣቱን ግን መሪው አልሸሸጉም።
መቀመጫውን ካምፓላ ያደረገው የ CIPESA (ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ፖሊሲ ለምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ትብብር)፣ የሳይበር ደህንነት ህግ በዛምቢያ ብቻ ሳይሆን፤ በጎረቤት ደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባብዌ፣ ናሚቢያ እና ማላዊ ጭምር እየወጣ እና ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል።
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ