የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መባባስ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 4 2013
የአየር ንብረት ለውጥ ተጠናክሮ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን የአየር ንብረት ለውጥን የሚከታተለው የበይነ መንግሥታት መድረክ ትናንት ይፋ አድርጓል። ዋና ጽሕፈት ቤቱ ጄኔቫ የሚገኘው 196 አባል ሃገራት የተሰባሰቡት ይኽ መድረክ በአሁኑ ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ በመላው ዓለም በተጨባጭ እየታየ መሆኑን አመልክቷል። ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ሙቀት፣ የተጠናከረ ሰደድ እሳት፣ ከፍተኛ ዝናብ እና ጎርፍ እንዲሁም ጠንካራ ማዕበል እና ውሽንፍር በተለያዩ ሃገራት ያደረሱት ጉዳት ያለፉት ሳምንታት እና ቀናት ቀዳሚ የዓለም መነጋገሪያ ዜናዎች ሆነዋል። የአየር ንብረት ለውጥን የሚከታተለው የተመድ ዘርፍ ለዚህ ሁሉ የተፈጥሮ አደጋ ዋናው የጠያቂ የሰው ልጆች ጥንቃቄ የጎደለው እንቅስቃሴ እንደሆነም አመልክቷል።
የአየር ንብረት ለውጥን የሚከታተለው በተመ የበይነ መንግሥታት መድረክ በእንግሊዝና ምህጻሩ IPCC በመላው ዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ጎልቶ እየታየ መሆኑን፣ ይኽም በቀላሉ ሊቀለበስ እንደማይቻል የሚያመላክት ዘገባ ትናንት ይፋ አድርጓል። 195 ሃገራት በአባልነት የሚገኙበት የበይነ መንግሥታቱ መድረክ ጥናት ላይ ተመርኩዞ ባወጣው ዘገባ ከዚህ ቀደም ያልታየ የሙቀት ማዕበል እና ዝናብ ድሃም ሆኑ ሃብታም የሚባሉ ሃገራትን ሳይለይ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ መሆኑን አመልክቷል። በጎርጎሪዮሳዊው 1988 ዓ,ም በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ሜቴሪዎሎጂ ድርጅት እና በአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ መርሃግብር ሥር የተቋቋመው የበይነ መንግሥታቱ መድረክ በየስድስት ዓመቱ የአየር ንብረት ለውጥ ይዞታን በመከታተል ዘገባ ሲያቀርብ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ዘገባውም ለፖሊሲ አውጪዎች ገለልተኛ፣ ሳይንስ ላይ የተመሠረተ አዳዲስ ግኝቶችን፣ የአየር ጠባይ ተጽዕኖዎችን እና ችግሩን ለመቆጣጠር ያስችላሉ የሚባሉ ሃሳቦችን ያቀርባል። ትናንት የወጣው የበይነ መንግሥታቱ መድረክ ዘገባ በመላው ዓለም እየታየ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ በከባቢ አየር ውስጥ ካርቦን እና ሌሎች ሙቀት አማቂ ጋዞች ክምችት መብዛትን ምክንያት አድርጓል። ለዚህም የሰው ልጅ ኃላፊነት የጎደለው እንቅስቃሴ ተጠያቂ እንደሆነም አመልክቷል። በምድራችን ላይ እየታየ ያለው የአየር ንብረት ለውጥም ታይቶ የማይታወቅ እና ለማሻሻል ወይም ለመቀልበስም አዳጋች መሆናቸውንም ገልጿል። ዘገባውን የተመለከቱት በዙርክ ስዊዘርላንድ የከባቢ አየር እና የአየር ንብረት ሳይንስ ተቋም ባልደረባዋ ሶንያ ሴኔቬራትኒ የአየር ንብረት ቀውስ ተፈጥሯል ለማለት ያስደፍራል ይላሉ።
«የአየር ንብረት ይዞታው መባባሱን የሚያሳየውን ውጤት ስመለከት የአየር ንብረት ቀውስ አለ ለማለት እደፍራለሁ። በእርግጥም እጅግ በጣም ትልቅ ችግር አለብን።»
IPCC ትናንት ይፋ ባደረገው ዘገባ በዋናነት መዘዝ ያለው በከባቢ አየር ውስጥ የሙቀት አማቂ ጋዞች ክምችት መጨመርን ሲሆን መፍትሄውም ብክለቱን መቀነስ እና የልቀት መጠኑንም ማሳነስን እንደሆነ አመልክቷል። ይኽ ካልሆነ ግን ከ10 ዓመታት በኋላ የዓለም የሙቀት መጠን 1,5 ዲግሪ ሴልሺየስን ሊያልፍ እንደሚችልም አስጠንቅቋል። በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን ሲቀነስ ፈጥኖ ሊከሰት የሚችለው የአየር ጥራት እንደሚሆን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይኽም በተለይ በጎርጎሪዮሳዊው 2020 የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ገደማ በመላው ዓለም የእንቅስቃሴ ገደብ በየሀገሩ ሲጣል እና የአውሮፕላኖች በረራ ሲቀንስ ውጤቱ በግልጽ ታይቷል። የዓለምን የሙቀት መጠንን መቀነሱ ላይ ለውጥ ለማምጣት ግን እስከ 30 ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል ነው የተነገረው። ይኽም ሊሆን የሚችለው ጠንካራ የብክለት ቅነሳ ስልቶችን ከአሁን ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ ማለት ነው። የዓለም መንግሥታት እየተሰባሰቡ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ሲመክሩ፤ የከባቢ አየር ብክለትን ለማጽዳት ሃገራት የየበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ሲደራደሩ እና ዕቅድም ሆነ ስልት ሲነድፉ ዓመታት ተቆጥረዋል። እንዲህ ያለውን ጥረት ባፋጣኝ ካልተጀመረ ወጪውም ቢሆን ሊንር እንደሚችል በጀርመኑ ፖስትዳም የአየር ንብረት ተጽዕኖ ምርምር ተቋም ባልደረባ ማልተ ማይንዝሃውዘን ይመክራሉ።
«የካርቦን መጠኑን አልፎ ያንን ለማስተካከል ከከባቢ አየር ጠርጎ ለማስወጣት ከመሞከር ይልቅ ብክለትን ለማስወገድ ከወዲሁ መሥራቱ እጅግ የተሻለ ነው። አሁን ባለበት ደረጃ ልናስቆመው ካልቻልን ውሎ ሲያድር የሚጠይቀን ወጪም ከፍተኛ ይሆናል።»
የአየር ንብረት ለውጥ እውን መሆኑን የሚያመላክቱ የተፈጥሮ ክስተቶች በየሀገሩ እየታዩ ነው። ለምሳሌ አውሮጳን ብንመለከት በሰሜኑ ክፍል ጠንካራ ዝናብ እና ጎርፍ፤ በደቡብ ደግሞ ሰደድ እሳት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። ግሪክ፣ ጣሊያን፤ ስፔን፣ አልባኒያ እና ሰሜን ሜቄዶንያ በበርካታ የየሃገራቱ ክፍሎች ከተነሳ የሰደድ እሳት ጋር እየታገሉ ነው። ቱርክም እንዲሁ ከሳምንት ለበለጠ ጊዜ እሳት በማጥፋት ተጠምዳለች። ከሳምንታት በፊት ለቀናት የወረደው ከባድ ዝናብ በተለይ በምዕራብ ጀርመን፣ በቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ እና ሉክሰምበርግ ጎርፍ አስከትሎ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋትን ንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል። ካናዳ ላይ ታይቶ የማይታወቅ የተባለው የሙቀት ማዕበል በትንሹ ለ500 ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተለይ በካሊፎርኒያ ግዛት ከባድ እሳት አስነስቷል። እንዲያህ ያለው የተፈጥሮ ክስተት እና አደጋ ከዚህ ቀደም በከፋ መልኩ ታይቶ እንደማይታወቅ ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት። IPCCም በትናንት ዘገባው ይኽንኑ ጠቁሟል። ዘገባውን ካዘጋጀው ቡድን ጋር አብረው የሚሠሩት ፓንማኦ ዛሃኒ እንደውም ከ2000 ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ነው ይሉታል።
«አሁን የምናየው አንዳንዱ ለውጥ በሺህ ዓመታት ውስጥ ታይቶ የሚታወቅ አይደለም ወይም ጭራሽ አልታየም። የአሁኑ ሙቀት መጠን ባለፉት 2000 ዓመት ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። አሁን ያለው የካርቦን ዳይኦክሳይድ ክምችትም ቢያንስ በ2 ሚሊየን ዓመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው። ባለፉት 100 ዓመታት የባሕር ወለል ቢያንስ በ3,000 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ከፍተኛ ፍጥነት እየጨመሩ ነው። አንዳንድ የአርክቲክ የባሕር በረዶዎች ቢያንስ በአንድ ሺህ ዓመታት ውስጥ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በዚያም ላይ ግግር በረዶዎች በሁለት ሺህ ዓመታት ውስጥ ባልታየ ሁኔታ ከጎርጎሪዮሳዊው 1950 ወዲህ እየሟሸሹ ነው።»
IPCC እንደሚለው ይኽን መሰሉ ግምገማ የሚቀርበው ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ የሙቀት መጠኖችን መዝግቦ በማጥናት፣ እንዲሁም በሙቀት አማቂ ጋዞች ብክለት አካኝነት የተከሰተውን የአየር ንብረት ይዞታ ሳይንሳዊ ሂደት በመረዳት ነው። እናም የዚህ ዘገባ ዋናው ምክር ሙቀት አማቂ ጋዞች ያስከተሉትን ብክለት ለማጥራት አስቸኳይ እና ጠንካራ ርምጃ ካልተወሰደ የሚፈራውን የሙቀት መጠን ማስከተሉ የማይቀር ነው የሚል እንደሆነ ጥናቱን ያካሄደው ቡድን ተባባሪ ሊቀመንበር ቫለሪ ማሶን ዴልሞቴ አጽንኦት ይሰጣሉ።
«ከዚህ ዘገባ ግልጽ ሆኖ የወጣው ነገር ምንድነው፤ አስቸኳ፣ ጠንካራ፣ ፈጣን እና መጠነ ሰፊ የሆነ የበካይ ጋዞች ቅነሳ ካልተደረገ የሙቀት መጠኑን ከ1,5 ዲግሪ እንዳይበልጥ የማድረጉ ምኞች አይደረስበትም። ዘገባው በቀጣይ 20 ዓመታት የዓለም ሙቀት መጠን 1,5 ዲግሪ እንደሚደርስ ወይም ከእሱም ሊያልፍ እንደሚችል ያመለክታል።»
የበይነ መንግሥታቱ መድረክ በየጊዜው በሚያቀርባቸው መረጃዎች በመንግሥታት፣ በንግድ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም በወጣት የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር መቻሉ ይነገርለታል። በተመራማሪዎች ያላሰለሰ ክትትል እና ምርምር ላይ ተመርኩዞ በየጊዜያው የሚያቀርባቸው ዘገባዎችም ያለውን አዝማሚያ የሚያመላክቱ እንጂ ትንበያዎች አይደሉም። የአየር ንብረቱን ይዞታ ቃኝቶ አስቀድሞ በሚሰጣቸው ሃሳቦችም ሃገራት የፖሊሲ አማራጮችን እንዲያፈላልጉ እንደሚረዳ ነው የሚገመተው። እስካሁን የትናንቱን ጨምሮ ስድስት ዘገባዎችን ነው ያቀረበው። በአምሰተኛ ደረጃ ያወጣው በጎርጎሪዮሳዊው 2014 ዓ,ም ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ በተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ የዓለም የሙቀት መጠን ከ1,5 ዲግሪ ከበለጠ በተለይ ለደሴት ሃገራት ሕዝቦች አደገኛ መሆኑን በማሳመን ጉባኤው ይኽንን የሙቀት መጠን ለመጠበቅ ተስማምቶ እንዲወስን ረድቷል። ዘንድሮ ያወጣው ዘገባም በመጪው ኅዳር ወር ግላስጎው ኢንግላንድ ለሚካሄደው የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ጉባኤ በአጭሩ COP 26 ፤ ፖሊሲ አውጪዎች ሊያተኩሩበት የሚገባውን ዋነኛ ጉዳይ እንዳያመላከተ ይታሰባል። በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሃገራት ሙቀት አማጺ ጋዞችን ለመቀነስ የገቡትን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ እየተጠየቀ ቢሆንም ትርጉም ያለው ሥራ ባለመሠራቱ ዛሬ የተፈጥሮ ቁጣ የእያንዳንዱን ቤት ማንኳኳት ጀምሯል። መንግሥታት ቃል የገቡትን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ተጠያቂ የሚያደርጋቸው አስገዳጅ አካል ያለም አይመስልም። ፈረንሳይ ግን አዲስ ነገር አሳይታለች። የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ አስተዳደር ቃል በገባው መሠረት የአየር ብክለትን በተገቢው መንገድ ለመቀነስ አልቻለም ሲል 10 ሚሊየን ዩሮ ቀጥቶታል። ባለፈው ዓመት ፍርድ ቤቱ የፈረንሳይ መንግሥት ከጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓ,ም ጀምሮ የአየር ብክለት መጠኑን ለመቀነስ ጥረት ባለማድረጉ፤ የስድስት ወራት ጊዜ ሰጥቶት ነበር። ባለፉት አራት ዓመታት የተለወጠ ነገር ባለመኖሩም ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት በይኖበታል። ይኽ ምናልባት ለሌሎች መሰል ሃገራት ማነቃቂያ ይሆን? ውሎ አድሮ የሚታይ ይሆናል። በዚህ መሃል ግን ዓለም በአንድ በኩል እሳት በሌላ ጎኗ የውኃ ሙላትን እያስተናገደች ነው።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ