1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ፅንፍ የወጣ የአየር ጠባይ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ

ማክሰኞ፣ ጥር 6 2017

በአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ ግዛት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት የተነሳው የሰደድ እሳት እስካሁን በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ እየተነገረ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥም እሳቱ ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ አካባቢን ያዳረሰ ሲሆን እሳቱን ለማጥፋት ከ1,400 በላይ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ተሠማርተዋል። ሰደድ እሳቱን ያስነሳው ምክንያት እየተመረመረ ነው።

ሎስ አንጀለስ፤ ሆሊውድ ካሊፎርኒያ
ሎስ አንጀለስ፤ ሆሊውድ ካሊፎርኒያ በሰደድ እሳቱ ስትጋይምስል፦ Ringo Chiu/REUTERS

ፅንፍ የወጣ የአየር ጠባይ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ

This browser does not support the audio element.

ሎስ አንጀለስን የጎዳው የሰደድ እሳት

«አመሰግናለሁ እንደምን ዋላችሁ? የተባባሰው የእሳት ሁኔታ እስከ ረቡዕ ድረስ ይቀጥላል። የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል ለዚህ እንደሚዘጋጅ እርግጠኛ እንድትሆኑ እንጠይቃለን። ይህ ንፋስ ከአነስተኛው ርጥበት ጋር ተዳምሮ በሎስ አንጀለስ ውስጥ ያለውን የእሳት አደጋ ስጋት በጣም ከፍ ያደርገዋል።»

የሎስ አንጀለስ እሳት አደጋ ተከላካይ ብርጌድ ኃላፊ አንቶኒ ማሮኔ፤ በትናንትናው ዕለት በሰደድ እሳት ቤት ንብረታቸው እየወደመ ላለው የካሊፎርኒያ ነዋሪዎች ያስተላለፉት መልክት ነው።

በዩናይትድ ስቴትስሷ የካሊፎርኒያ ግዛት በሎስ አንጀለስ እና አካባቢው የተነሳው የሰደድ እሳት በበርካታ ሺህዎች የሚገመቱ ሰዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው እንዲሰደዱ አስገድዷል። ለአንድ ሳምንት ተባብሶ የቀጠለው እሳት እስካሁን ለ24 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት እስካሁን ባሉ መረጃዎች መሰረት ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ቤቶች በእሳቱ ወድመዋል። አብያተ ክርስቲያን፤ መስጊድ እና ምኩራቦችም ከእሳት ቃጠሎው አልተረፉም።

በሎስ አንጀለስ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎችን ባዳረሰው የሰደድ እሳት ምክንያት የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ የተገደዱት ወገኖች ወደየቤታቸው ተመልሰው የደረሰውን ጉዳት በዓይናቸው ለማየትና ንብረታቸውን የመቆጣጠር ፍላጎት እንዳላቸው ቢናገሩም በያሉበት ቢያንስ ለቀጣይ አራት ቀናት እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።

ሰደድ እሳቱ ያፈናቀላቸው ወገኖች ስጋት

ከቤታቸው ከተፈናቀሉት መካከል ሄንሪ ሌቪንሰን አንዱ ነው። የእሳቱ መባባስ ያሰጋው ወጣት የሟች ቤተሰቦቹን አጽም የመሰብሰብ ምኞቱ ወደተከለከለው አካባቢ እንዲመለስ እንደገፋፋው ይናገራል።

«ተበሳጭቻለሁ፤ ተበሳጭቻለሁ እንዲሁም ፈርቻለሁ ምክንያቱም በሰሜን ካሊፎርኒያ እና ማዊ ሁለት ከተሞች በእሳቱ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል። አሁን ደግሞ ፓስፊክ ፓሊሴድስና አልታዴናን አጣን። መቼ ነው ለውጥ የምናየው? እዚያው የተውነውን የአባቴን እና የሴት አያቴን አጽም መሰብሰብ እፈልጋለሁ,። እሳቱ ሲነሳ እናቴ የፈረንስ ግልቢያ ከምታስተምርበት ፈረሶችን እያወጣን ነበር። ቀኑን ሙሉ እዚያው ስለነበር ወደ ቤት የምንመለስበት ዕድል አልነበረንም።»

ሎስ አንጀለስ፤ ሆሊውድ ካሊፎርኒያ ቤት ንብረታቸው በቃጠሎው የወደመ ወገኖች ሀዘን ምስል፦ David Swanson/REUTERS

ሌላው ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ ፈልገው መንገድ ላይ ከሚገኙት አንዱ የአበባ መሸጫ አዳራሽ ባለቤት የሆኑት ማርክ ቻፍ ደግሞ ያሳሰባቸው በግርግሩ ለዘረፋ የተሰማሩ መኖራቸው ነው።

«ለምሳሌ ዛሬ ጠዋት 12 ሰዓት ነው እዚህ የደረስኩት። አሁን አምስት ሰዓት ተኩል ሆኗል፤ ግን ሰዎች እንዲያልፉ አልፈቀዱም፤ ሰዎችም መኪናቸውን ቦታ እያስያዙ እየተመለሱ ነው። በዝርፊያ ምክንያት በትክክለኛው መንገድ ለመግባት አስቸጋሪ ሆኗል። ገበያው ሲነድ ከሁለት ቀናት በፊት ገብቼ ነበር፤ ሆኖም በጭሱ ምክንያት በደንብ ስለማይታይና እና የእሳቱ ጉማጅ ስለሚፈናጠር ለእራሴው ደኅንነት ስል ወደ ኋላ ተመለስኩ። ግን ደግሞ በዚያኑ ወቅት ዘራፊዎች ውስጥ ነበሩ።»

ምንም እንኳን ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው ለመሄድ እሳቸውም መኪናቸውን አሰልፈው ቢጠባበቁም በቀጣይ ከእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች የሚሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ከማድረግ ሌላ አማራጭ የለም ባይ ናቸው የፊልም አዘጋጅ የሆኑት አንዲ ዋትስ።

«ስጋቱ ጉልበት የሚያርድ ነው፣ ሆኖም ግን ስለእሳት የሚረዳ ማንኛውም ሰው ነገሮችን ወደ መጥፎ ለመቀየር ጥሩ ንፋስ ብቻ እንደሚፈልግ ይገባዋል። እናም ያገዱት ለሁሉም ደኅንነት ብለው መሆኑን አውቃለሁ። ሁኔታው ንብረታችንን በተለይ ደግሞ ነዳጅ የሞሉ ተሽከርካሪዎችን ለማውጣት የሚፈቅድልን አይመስልም። ሆኖም ግን እዚያ የስሜት ጋር የተሳሰሩ ዋጋ ያላቸው ነገሮች መኖራቸውን መረዳት ያስፈልጋል። እናም ከዚህ የተለየ ነገር ቢሆን ኖሮ ብሎ መመኘትም አለ።»

እንዲህ በርካቶችን ከመኖሪያ እና ከሥራ ቦታቸው ያፈናቀለው የሰደድ እሳት ያስከተለው ጉዳት በሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ ታሪክ ታይቶ አይታወቅም ነው የተባለው። ጥቂት የማይባሉ ሀብታሞችና ታዋቂ ሰዎች ንብረታቸው እንደዋዛ በደቂቃዎች በእሳት ተበልቶ ወደ አመድነት ሲቀየር ታይቷል። በቪዲዮ የሚወጡ መረጃዎች አንዳንድ መንደሮች ፈጽመው መውደማቸውን ያሳያሉ። 

ሎስ አንጀለስን ያስጨነቀው ሰደድ እሳት መባባሱ

በካሊፎርኒያ ግዛት ሎስ አንጀለስ አካባቢ የተነሳው የሰደድ እሳት በመጠኑ ጋብ ካለ በኋላ በነፋስ ምክንያት በትናንትናው ዕለት ዳግም ሊባባስ እንደሚችል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። የሰዎችን ሕይወት ጨምሮ ለበርካታ መኖሪያ ቤቶች የንግድ ቦታዎችና ተቋማት መውደም ምክንያት ለሆነው እሳት መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉት መነሻዎችን መርማሪዎች እያጣሩ ነው። መርማሪዎቹ እሳቱ ፓስፊክ ፓሌሴድስ ውስጥ ከጫካ አጠገብ ከሚገኝ አንድ ቤት ጀርባ ሳይነሳ እንዳልቀረ ገምተዋል። አብዛኛውን ጊዜ አሜሪካን ውስጥ የሰደድ እሳት በመብረቅ ሊነሳ እንደሚችል ቢገመትም፤ መርማሪዎቹ ግን ይህን ወዲያው ነው ያስተባበሉት። ምክንያቱም በተጠቀሰው አካባቢ የተከሰተ መብረቅ አልነበረም ነው የተባለው።

ሎስ አንጀለስ፤ ሆሊውድ ካሊፎርኒያ እሳቱ ያወደመው መንደርምስል፦ Ringo Chiu/REUTERS

በቀጣይም ሆን ተብሎ የሚለኮስ እሳት እና በአገልግሎት መስመሮች ላይ የሚቀሰቀስ እሳት የሚሉት ግምቶች ቀርበው እየተጣራ ነው። ክስተቱን የአየር ንብረት ለውጥ ውጤት አድርገው የሚገልፁትም ጥቂት አይደሉም። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሥር የወንዶ ገነት ደንና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሰለ ነጋሽ በበኩላቸው ሰደድ እሳት በሁለት ዓይነት መንገዶች ሊከስት ይችላል ነው ያሉት።

የአየር ንብረት ለውጥ ጫና

በዓለማችን በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ አካባቢዎችአንዳንዶቹ በድርቀት ሌሎቹ ደግሞ በኃይለኛ ዝናብ እና እሱ ባስከተለው ጎርፍ መጋለጣቸው ይታያል። የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ሃገራት የክረምት ወቅት እንደመሆኑ ቅዝቃዜው ቢጠበቅም አንዳንዱ አካባቢ ከዚህ በፊት በዚህ ወቅት ይከሰት የነበረው በረዶ እንደተጠበቀው ያልሆነበት፤ የቅዝቃዜው መጠንም የሚታወቀው ዓይነት እንዳልሆነ ይነገራል። ፕሮፌሰር መሰለምንም እንኳን የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖው ፅንፈ የወጣ የአየር ጠባይ እንዲፈራረቅ ቢያደርግም፤ ክስተቱ የአየር ንብረት ለውጥ ነው ብሎ ለመወሰን ግን ቢያንስ ለተከታታይ 30 ዓመታት ያለው የአየር ጠባይ ሁኔታ በየአካባቢው መጠናት ይኖርበታል ነው ያሉት  ፕሮፌሰር መሰለ።

ለቀናት መንደሮችን በማውደም ላይ የሚገኘውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር ከካሊፎርኒያ እና ከሌሎች ዘጠኝ ግዛቶች የተውጣጡ 1,400 የሚጠጉ የእሳት ማጥፊያ ሞተሮች፤ 84 አውሮፕላኖች እና ከጎረቤት ሜክሲኮ ለእርዳታ የመጡትን ጨምሮ ከ14 ሺህ የሚበልጡ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ተሰማርተዋል።  

በነገራችን ላይ ያለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2024 ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ዘመን ነው ተብሏል።  በዚሁ ዓመት ለ41 ቀናት ከፍተኛ ሙቀት መመዝገቡም ተገልጿል። ይህም በሰዎች ጤና እና በስነ ምህዳሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉም ተመዝግቧል። ፅንፍ በወጡ ማለትም በኃይለኛ ሙቀት ድርቅ፤ ጎርፍ፤ ወጀብ፤ እና በመሳሰሉ የአየር ሁኔታዎች ምክንያትም ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ወደ 148 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ተፈናቅሏል። በ2024 የዓለም የሙቀት መጠንም ከ1,5 ዲግሪ አልፏል ነው የተባለው።  ማብራሪያ ለመስጠት የተባበሩን ፕሮፌሰር መሰለ ነጋሽን እናመሰግናለን።  

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW