1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአይን ብርሃን ለሌላቸዉ ህጻናት ብቸኛዉ ህጻናት መዋያ በአዲስ አበባ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 2016

አይነ ስውራን ህፃናት ልጆች ያሏቸው ሰባት እናቶች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተፈላልገዉ እና ተገናኝተዉ ስለ ልጆቻቸው እጣ ፈንታ፤ ስለእድገታቸዉ ስለትምህርታቸዉ ተወያዩ፤ ወሰኑም። ልጆቻችን ቤት ተቀምጠዉ አይቀሩም፤ሲሉ ለጆቻቸዉ በኢትዮጵያ ብቸኛውንና የመጀመርያዉን የአይነ ስውራን መዋዕለ ህፃናት አዲስ አበባ ላይ ከፈቱ።

ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅት
ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅትምስል Vision Blind Kindergarten

የአይን ብርሃን ለሌላቸዉ ህጻናት የተቋቋመዉ ብቸናዉ ህጻናት መዋያ በአዲስ አበባ

This browser does not support the audio element.

የአይን ብርሃን ለሌላቸዉ ህጻናት የተቋቋመዉ ብቸናዉ ህጻናት መዋያ በአዲስ አበባ

«እነዚህ ልጆች የአይን ብርሃን እንዳላቸዉ ሌሎች ልጆች ሁሉ፤ አፀደ ህጻናት በመሄድ አንዳንድ ነገር ይማሩ፤ እዝያ ይዋሉ ነዉ የኛ ዓላማ። እነዚህ ልጆች ስምንት ዓመት እስኪሞላቸዉ እቤት ዉስጥ ተዘግቶባቸዉ መቀመጥ የለባቸዉም። እስከዛሬ ድረስ የአይን ብርሃን የሌላቸዉ ህጻናት አፀደ ህጻናት መሄድ አያስፈልጋቸዉም፤ ያስፈልጋቸዋል የሚለዉ ነገር የግንዛቤ ጉዳይ ነበር። አሁን ግን እኛ አይን ብርሃን ለሌላቸዉ ህጻናት መዋያ ከፍተን ፈር ቀደናል፤ አሳይተናል» ሲሉ የተናገሩት፤

ወ/ሮ ሰናይት የኋላወርቅ ይባላሉ፤ በአዲስ አበባ የሚገኘዉ እና በኢትዮጵያ ብቸኛዉ ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት መዋያ አንዷ መስራች እና የቦርድ አባል ናቸዉ። የህጻናት መዋያዉ « ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅት» ይባላል። ከሁለት ዓመት በፊት ወ/ሮ ሰናይት የኋላወርቅን ጨምሮ አይነ ስውራን ህፃናት ልጆች ያሏቸው ሰባት እናቶች መጀመርያ በህክምና ማዕከል በኋላም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተፈላልገዉ እና ተገናኝተዉ ስለ ልጆቻቸው እጣ ፈንታ፤ ስለእድገታቸዉ ስለትምህርታቸዉ ተወያዩ፤ ወሰኑም።

ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅትምስል Vision Blind Kindergarten

የአይን ብርሃን ለሌላቸዉ ህጻናት መዋያ ሊከፈት ይገባል

ልጆቻቸውን በህጻናት መዋያ ተቀብሎ ሊያስተምርላቸው የሚችል በማጣታቸውም ልጆቻች ቤት ተቀምጠዉ አይቀሩም ሲሉ ጠንክረዉ ተነሱ፤ በድፍረት ለጆቻቸዉ በኢትዮጵያ ብቸኛውን እና የመጀመርያዉን የአይነ ስውራን መዋዕለ ህፃናት አዲስ አበባ ላይ ከፈቱ። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸዉ ደጀን እንደተናገሩት ከክፍያ ነጻ አገልግሎት በመስጠት ሁለተኛ ዓመቱን ስለያዘዉ ስለ «ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅት» በሰፊዉ ነግረዉናል።

«የተቋሙ ስም  «ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅት» ይባላል፤ ድርጅቱን የመሰረቱት አይነስዉራን ህጻናት ያልዋቸዉ ሰባት እናቶች ናቸዉ። ድርጅቱ እንዲመሰረት ያስገደደበት ምክንያት ደግሞ በመዲናዋ አዲስ አበባ ምንም አይነት አይነስዉራን ህጻናትን ተቀብሎ የሚያስተምር መዋለ ህጻናት፤ ባለመኖሩ ምክንያት ነዉ። እነዚህ እናቶች እና በተመሳሳይ ችግር ዉስጥ ያሉ እናቶች ፤ ህጻናቱን በር ዘግተዉባቸዉ እንዲዉሉ፤ ከስራ እንዲስተጓጎሉ በመሆኑ፤ እናቶች በራሳቸዉ ፈቃድ ተነሳስተዉ ይህን የህጻናት መዋያ ለሟቋቋም ችለዋል። ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰቦች ድርጅቶች ባለስልጣን  መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ነዉ ፈቃዱን አግኝቶ ስራን የጀመረዉ። ድርጅቱ ጀርመን አደባባይ፤ ንፋስ ስልክ በሚባል ክፍለ ከተማ ዉስጥ የግለሰቦችን ቤት ተከራይቶ ነዉ ስራዉን የጀመረዉ። ይህ የአይነስዉራን ህጻናት መዋያ በአዲስ አበባ ከተማ በአይነቱ የመጀመርያ የሆነ ነዉ። ይሁንና ድርጅቱ ስራዉን እንዲቀጥል አሁንም እርዳታ ያስፈልገዋል። ህጻናቱ ጠዋት ሁለት ሰአት ተኩል ላይ መዋለ ህጻናቱ ዉስጥ ትምህርታቸዉን ጀምረዉ ወደ ቤታቸዉ የሚመለሱት ከቀኑ ስምንት ሰአት ተኩል ዘጠኝ ሰአት ላይ ነዉ። ህጻናቱ እረፍት ሰዓት እና ምሳ ሰአት ላይ የሚመገቡትን ምሳ ቋጥረዉ ነዉ የሚመጡት። ወላጆቻቸዉ ምግብ ቋጥረዉ እንዲልኳቸዉ እናስገድዳለን። የመማርያ ቁሳቁስ መግዛት ለማይችሉ ወላጆች፤ ለህጻናቱ የመማርያ ቁሳቁስ በመስጠት እናግዛለን።»

ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅትምስል Vision Blind Kindergarten

የአይን ብርሃን የሌላ ቸዉ በርካታ ህጻናት ዛሬም ቤት ዉስጥ ተዘግቶባቸዋል

የድርጅቱ አንዷ መስራች እና የቦርድ አባል ወ/ሮ ሉላ አብደላ ፤ ሰባት እናቶች ሆነዉ ስለከፈቱት የህጻናት መዋያ ደስተኛ ቢሆኑም ህጻናቱ ብዙ ለዉጥ እየታየባቸዉ መሆኑን ቢናገሩም፤ ድርጅቱ በገንዘብ እጥረት ከፍተኛ ችግር ዉስጥ እንደሆነ አልሸሸጉም። ይሁንና የህጻናት መዋያዉ መከፈቱ፤ ከቤታቸዉ ወጥተዉ የማያዉቁ ህጻናት ዉጭ ወጥተዉ ሌላ አየር የተነፈሱበት ከሌሎች ሰዎች እና ከእኩዮቻቸዉ ጋር መነጋገር የቻሉበት እንደሆነ ተናግረዋል። ከህጻናቱ ሰዉኛ ነገር ማግኘታቸዉ በራሱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳስገኘላቸዉ ተናግረዋል።

ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅትምስል Vision Blind Kindergarten

አዲስ አበባ ላይ የሚገኘዉ እና ብቸኛዉ ማየት ለተሳናቸዉ ህጻናት መዋያ፤ የራሱ ገቢ የሌለዉ እና ድርጅቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በሚያስተላልፈዉ የእርዳታ ጥሪ ከቅን እና ደጋግ ልብ ካላቸዉ ወገኖች በሚገኝ የገንዘብ እና የግበአት ድጋፍ የቆመ መሆኑን የነገሩን የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸዉ ደጀን፤ በከተማዋ በርካታ አይነ ስዉራን ህጻናት፤ በህጻናት መዋያዉ ግልጋሎት ማግኘት ቢፈልጉም በአቅም እጥረት ድርጅቱ መቀበል እንዳልቻለም ነግረዉናል። 

በአዲስ አበባ በሚገኘዉ እና በኢትዮጵያ ብቸኛዉ ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት መዋያ ሌላዋ መስራች እና የቦርድ አባል ወ/ሮ ሰናይት የኋላወርቅ ናቸዉ። ወ/ሮ ሰናይት ህጻናት መዋያዉ ከተመሰረተ ከሁለት ዓመት ጀምሮ በህጻናት መዋያዉ የሚዉለዉ የስድስት ዓመት ልጃቸዉ ሳሙኤል ደረጀ ነዉ። እጅግ ብዙ ትምህርት እንዳገኘ እና እሳቸዉ ራሳቸዉ አይነስዉር መሆኑን ሁሉ እንደሚረሱት ተናግረዋል።

ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅትምስል Vision Blind Kindergarten

የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ ቁሳቁሶችን ሰጥቶናል

ህጻናት መዋያዉ ባለፈዉ ሰኔ 30 ለክረምት የዓመት እረፍት ሲዘጋ ዝግጅት አካሂዶ ነበር። በዚህ ዝግጅት ላይ የክፍለ ከተማ ባለስልጣንት ብሎም የአዲስ አበባ የትምህርት ቢሮ ከዚህ ቀደም እርዳታ መስጠታቸዉን ወ/ሮ ሰናይት ተናግረዋል። ይሁን እና መንግሥት ሌሎች ተጨማሪ ቅርንጫፍ ለአይነስዉራን ህጻናት የአፀደ ህጻናት እንዲከፍት እና እርዳታ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ልጆች ያላቸዉ ሰባት እናቶች የግለሰብ ቤትን ተከራይተው የከፈቱት እና አዲስ አበባ ጀርመን አደባባይ የሚገኘው ህጻናት መዋያ  ከመላው አዲስ አበባ ሰፈሮች ረጅም ርቀት አቋርጠው የሚመጡ 35 ህጻናትን ተቀብሎ ሲንከባከብ ቆይቷል። ይሁንና የአምስቱ ህጻናት ወላጆች የህጻናት መዋያዉ ካለበት ቦታ በጣም ርቀዉ ስለሚኖሩ ከብዷቸው ለማቋረጥ መገደዳቸዉ ተሰምቷል። ሌሎቹ ወደ 30 የሚሆኑት ግን በህጻናት መዋያዉ መዋላቸዉን መማራቸዉን ቀጥለዋል። ይሁንና ከተማሪዎች ክፍያ የማይቀበለው ይህ የህጻናት መዋያ በስራዉ እንዲቀጥል አሁንም የእርዳታ ጥሪዉን ያቀርባል።

ቪዥን ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅት - መስራቾችምስል Vision Blind Kindergarten

ኢትዮጵያዉ ሁሉ እንዲረዳን እፈልጋለን

አይነስውራን ብቻ ሳይሆኑ የኦቲዝም እና የሌሎች ህመሞች ተጠቂ ህፃናት የሚገኙበት ይህ መዲና አዲስ አበባ ላይ የሚገኘዉ በኢትዮጵያ ብቸኛዉ ማየት የተሳናቸዉ ህጻናት መዋያ፤ ለህጻናቱ የመማርያ ክፍልና ግብአት አመቺ እንዲሆን ብሎም የመማርያ ቁሳቁስ እና መጻህፍትን በቀጣይ ከዜጎች ብሎም ከአዲስ አበባ አስተዳደር እንደሚያገኝ የድርጅቱ መስራቾች ተስፋቸዉን ሰንቀዋል። ከተማሪዎች ክፍያ የማይቀበለው ድርጅቱ የትምህርት ቤቱን ወጪ የሚሸፍነው ግለሰቦችን እርዳታ በመጠየቅ ነው። በመሆኑም ማየት ለተሳናቸዉ የቆመዉ ህጻናት መዋያ፤ ህጻናቱን በትምህርት በማነጽ፤ ስራዉን እንደሚቀጥል ብሎም ከአዲስ አበባ አስተዳደር እና ከዜጎች እገዛን እንደሚያገኝ እናምናለን።

ሙሉ ጥንቅሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW