የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 9 2017
ይህ የሆነበትን ምክንያት «የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጉዳዮች የብሔራዊ ደህንነት፣ የማኅበራዊ ፍትሕ፣ የሰብአዊ መብት፣ የዘላቂ ልማትና ሰላም አጀንዳ በመሆን ሁለንተናዊ ሚዛናዊ ምላሽ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው» መሆኑ በረቂቁ ላይ ተገልጿል። ረቂቅ አዋጁ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር «ያልተማከለ ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ» መሆኑንም ያመለክታል። ይህም ማለት የአደጋ ምላሽ ሥራዎች ከቀበሌ ጀምሮ ባሉ አደረጃጀቶች ምላሽ እንዲሰጣቸው የሚያስገድድ አሠራርን የያዘ ነው። ረቂቅ አዋጁ በዝርዝር እንዲታይ እና ለምክር ቤቱ ተመልሶ እንዲቀርብ ለውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
የተፈጥሮ አደጋዎች እና ሰዎች በሚፈጥራቸው እንደ ጦርነት እና ግጭትየመሳሰሉ ችግሮች ሲከሰቱ አስፈላጊውን ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠበቅበት የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አዲስ በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በምከር ቤት እንዲመራ እና ይሄው ምክር ቤት የኮሚሽኑ ከፍተኛው የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ተደንግጓል። ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመራ መሆኑ በረቂቁ ሰፍሯል። የኮሚሽኑ የበላይ ኃላፊ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾም ሆኖ እንደ አስፈላጊነቱ ምክትል ከሚሽነሮች ይኖሩታልም ተብሎ በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል።
ረቂቁ የተቋሙ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን የተደረገበትን ምክንያት ሲገልጽ «የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጉዳዮች የብሔራዊ ደህንነት፣ የማኅበራዊ ፍትሕ፣ የሰብአዊ መብት፣ የዘላቂ ልማትና ሰላም አጀንዳ በመሆን ሁለንተናዊ ሚዛናዊ ምላሽ የሚጠይቅ በመሆኑ ነው» በሚል ተቀምጧል።
የረቂቅ አዋጁ ዋና ዋና አላማዎች
የዚህ ረቂቅ አዋጅ ዓላማዎች «ሁለንተናዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ሥርዓት መገንባት፣ ዘላቂ ልማትን መሠረት በማድረግ በአደጋ ምክንያት ሊከሰት የሚችልን ጉዳት መቀነስ፣ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ውስጥና መካከል የተቀናጀ ዕቅድና ትብብርን ማስፋፋት፣ ለአደጋ ሥጋት የላቀ ዝግጅት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲኖር ማስቻል» የሚሉ እና ሌሎችንም ይዟል።
ረቂቅ አዋጁ ከዚህ በፊት የክልል መንግሥታት እና የፌደራል መንግሥቱ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራርን በተመለከተ ያለባቸዉ የኃላፊነት ልዩነት "ምንድን ነዉ የሚለዉ ተለይቶ አይታወቅም ነበር» ይላል። ይህም በመሆኑ ኮሚሽኑን ከአቅሙ በላይ «እንዲወጠርና ሥራዎች በሚፈለገው ጥራት እንዳይሠሩ እንቅፋት ሆኖ የቆየ አሠራር» ነው ብሏል።
በዚህም ምክንያት አዲሱ ረቂቅ ሕግ «ከታችኛው የአስተዳደር እርከን ጀምሮ ማለትም ከቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልል ከዚያም የፌደራሉ ኮሚሽን ከመከላከል እስከ መልሶ ማቋቋም ያለውን ሥራ በራሳቸው አቅም መሥራት አለባቸዉ» የሚል ሲሆን፤ «ከማንኛውም የአስተዳደር እርከን አቅም በላይ የሆነው የምላሽ ሥራ ቀጥሎ ባለው ከፍተኛ የአስተዳደር እርከን በአሠራሩ መሠረት እየተጣራ እንዲሠራ» ሲል ደንግጓል።
ይህንንም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት ተስፋዬ በልጅጌ አብራርተዋል።
«እየገዘፈና እየሰፋ የመጣውን ተፈጥሯዊ የአደጋ ክስተቶችን ለመመከት የተረጅነት እና የልመና አስተሳሰብን ለመሻገር፣ ከጥገኝነት እና ጠባቂነት ወጥመድ ለመላቀቅ የሚያስችል ዘላቂ ተቋማዊ አቅም መገንባት ይገባናል።»
በረቂቅ አዋጁ «ቅጽበታዊ አደጋ ሲከሰትና ምክር ቤቱ ሊሰበሰብ የማይችል ከሆነ አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እወጃን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ ሊያደርግ ይችላል» በሚል ተደንግጓል።
በረቂቅ አዋጁ የተከለከሉ ተግባራት
በረቂቅ አዋጁ የሰብአዊ እርዳታ ስርጭት አቅጣጫን ማስቀየር፤ እርዳታው ለታለመለት አላማ እንዳይውል ማድረግ፣ መሸጥ፣ ፍቃድ ሳይኖር ይዞ መገኘት ወይም ወደ ሦስተኛ ወገን ማስተላለፍ፤ ማንኛውም በፌደራል ሆነ በክልል ደረጃ የሚገኝ አመራር አካል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓቱ በሚሰጠው የማስጠንቀቂያ መረጃን ተቀብሎ ተገቢው የጥንቃቄ እርምጃ ሳያደርግ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት በሰው ሕይወትና በኑሮ፣ በመሰረተ-ልማት ላይ የከፋ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ፤ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለማግኘት ሀሰተኛ መረጃ ወይም የተጋነነ ጥያቄን ማቅረብ፤ ለተጎጂዎች የሰብአዊ እርዳታ በማንኛውም ሁኔታ በወቅቱ እንዳይደርስ ማዘግየት ወይም እንዳይደርስ ማድረግ፤ ሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለማይገባው ሰው መስጠት፤ አደጋ ሳይኖር አደጋ እንዳለ አድርጎ የእርዳታ ጥያቄን ማቅረብ፤ የአደጋ ስጋትን የሚያባብሱ እና አደጋዎቹን የሚፈጥሩ የትኛውም አይነትኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ድርጊቶች ላይ መሳተፍ የተከለከለ መሆኑ ተጠቅሷል።
ረቂቅ አዋጁ በሁለት የምክር ቤት አባላት ተደግፎ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ሲመራ፣ ከተረጂነት ልማድ ለመውጣትና ራስን ለመቻል ያግዛል የሚለው ተጠቅሶ ነው። «ያለንበት የጊዜ ኹኔታ እርዳታን የምንጠብቅበት ጊዜ አይደለም። በሁሉም ራሳችንን መቻል ያለብን ጊዜ ነው።»
በአዋጁ የተቀመጡ የወንጀል ተጠያቂነቶች
በረቂቅ አዋጁ ለአደጋ ምላሽ የሚሰጥበት በጀት በመንግሥትየሚመደብ መሆኑ ተጠቅሷል። በዋናነትም ከልዩ ልዩ የመንግሥት የአገልግሎት ክፍያዎች ከሚሰበሰቡ የገቢ ምንጮች የሚገኝ መሆኑ ተመላክቷል። ከለጋሽ አካላት እና ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችም ሀብቱ ሊገኝ እንደሚችም ተገልጿል። ቅጣትን በሚመለከት ማንኛውም ሰው የሰብዓዊ እርዳታ ለተረጂዎች እንዳይደርስ ያደናቀፈ ወይም የከለከለ እንደሆነ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ይቀጣል ሲል ደንግጓል።
በተመሳሳይ የሰብአዊ እርዳታን ለራሱ ወይም እርዳታው ለማይመለከተው ሰው ጥቅም እንዲውል ያደረገ እንደሆነ የተዘረፈውን ንብረት ማስመለሱ ወይም መውረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ10 ዓመት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣትም ደንግጓል።
የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለማግኘት ሀሰተኛ መረጃ ወይም የተጋነነ ጥያቄ ወይም አደጋ ሳይኖር አደጋ እንዳለ አድርጎ የእርዳታ ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ ከሦስት ዓመት የማያንስና ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ቀላል እሥራት እንደሚኖርም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተደንግጓል።
ሰለሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ