1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአዲስ አበባ አዲስ ወሰን

ረቡዕ፣ ነሐሴ 11 2014

ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የሁለቱ አስተዳደሮች ህዝብ ጥንትም በፍቅር የተጋመደ፣ በአብሮነት እና መተሳሰብ የተሰናሰለ በመሆኑ የተቀበረለትን የግጭት ፈንጂ አምክኗል” ሲሉም ውሳኔውን አሞካሽተዋል፡፡

 Addis Ababa City
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የአዲስ አበባና በፊንፊኔ ዙርያ የኦሮምያ ልዩ ዞን አዲስ ወሰን

This browser does not support the audio element.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመዲናዋ አዲስ አበበባ እና በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አስተዳደር ወሰን ማጠናቀቃቸውን አመለከቱ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት ትናንት ከማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተደርጓል በተባለው ውይይት በአስተዳደር ወሰኑ ላይ መጠነኛ መሻሻሎች መደረጋቸውም ተነግሯል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎችም አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የአስተዳደር ወሰኑ መለየት አዎንታዊ ሚና ያለውና ውዝግቦችን የሚያቀዘቅዝ ይሆናል የሚል ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት በጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሲሰራበት የቆየ ነው የተባለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፊንፊኔ ዙርያ የኦሮምያ ልዩ ዞን የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳይ፣ በኢትዮጵያ ህገመንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሰረት እልባት የተሰጠው ነው ተብሏል፡፡ ሁለቱ አስተዳደሮች ትናንት ከህብረተሰብ ተወካዮች ካሏቸው ጋር ከተወያዩ በኋላ ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡ የወሰን ጉዳዩ በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ አስተዳደር አካላት የጋራ ስምምነት መፈታቱንም ‘ታሪካዊ’ ነው ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የወሰን ማካለል ስራውን ስኬታማ ብለውታልም፡፡ “በዚህ የአስተዳደር ወሰን የሰራነው አጥር አይደለም፡፡ በህዝቦች መሃከል አጥር ልናበጅ አንችልም፡፡ ይልቁንም በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባውን የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት የሚያፀና ነው” ብሏል ከንቲባዋ፡፡
በትናንትናው የውይይት መድረክ ከተሳተፉት የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ዋና ፀኃፊና የቱላማ አባገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ ይገኛሉ፡፡ አባገዳ ጎበና ለዶይቼ ቬለ  በሰጡት አስተያየታቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፊንፊኔ ዙርያ የኦሮምያ ልዩ ዞን መካከል ተከልሶ ይፋ የሆነው የአስተዳደር ወሰን አዎንታዊ ፋይዳ ያለው ነው ብሏል፡፡ 
“እኔ እንደገባኝ የአስተዳደር ወሰኑ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩና በፊንፊኔ ዙርያ የኦሮምያ ልዩ ዞን ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰብ መካከል ገደብ በመፍጠር የሚለያይ አይደለም፡፡ የአስተዳደር ወሰኑ በግልጽ ተለይቶ አለመሰመር በከተማዋ ዙሪያ ላሉ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ችግር ሲፈጥርም ቆይቷል፡፡ ከዚህ የተነሳም ህዝቡ ጥያቄ ሲያነሳ ነበር፡፡ ለዘመናት ከነገስታቱ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ በወሰኑ ዙሪያ ስጋትና የግጭት መንስኤ ሊሆን የነበረው ጥያቄም አሁን እልባት እንዳገኘ ነው የሚሰማኝ፡፡ ከእንግዲህ በዙሪያው የሚገኙ የአርሶ አደሮች መብት የሚጠበቅ ይመስለኛል፡፡ የመልማት ጥያቄውም በተሻለ ይፋጠናል ብለን እናስባለን፡፡ የተሰመረው የአስተዳደር ወሰን እንጂ ድንበርም አይደለም፤ ልክ እንደ ገላንና ዱከም ያለ ወሰን ነው በሚል ነው የተረዳነው” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ምስል፦ Seyoum Getu/DW

አባገዳ ጎበና ሆላ ለአስተዳደር ወሰኑ እንደ ወንዞችና ተራራ ያሉ የተፈጥሮ ወሰኖች እና ትላልቅ መንገዶች ጥቅም ላይ መዋላቸውም እንደተብራራላቸው አንስተዋልም፡፡ 
ከንቲባ አዳነች አቤቤ እያተከናወነ ያለው የአስተዳደር ወሰንን መልክ ማስያዝ ልማትን ለማፋጠንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡ “የሁለቱ አስተዳደሮች ህዝብ ጥንትም በፍቅር የተጋመደ፣ በአብሮነት እና መተሳሰብ የተሰናሰለ በመሆኑ የተቀበረለትን የግጭት ፈንጂ አምክኗል” ሲሉም ውሳኔውን አሞካሽተዋል፡፡ 
በባለስልጣናቱ ታሪካዊ ነው በተባለው በዚህ የአስተዳደር ወሰን ውሳኔ በብዛት የኦሮምያ እና  አዲስ አበባ ወሰን በነበረው ሲቀጥል፤ በኦሮምያ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ውስጥ የተገነቡ ኮንዶሚኒየሞች ለአብነትም ኮዬ ፈጬ፤ ቱሉዲምቱ በከፊልና ጀሞ ቁጥር ሁለት ወደ ኦሮምያ ልዩ ዞን መካለሉን ነው የተገለጸው፡፡ ኦሮምያ የገነባውን የቆጣሪ ኮንዶሚኒየም ወይም ለቡ አካባቢ ከፉሪ ሃና ማሪያምና የኦሮምያ ኮንዶሚኒየሞች ጨምሮ እስከ ቀርሳ ወንዝ ያለው ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲካለሉ መሆኑ በሁለቱ አስተዳደሮች ከስምምነት ላይ መደረሱን ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በፊናቸው በትናንታነው የጋራ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህ በአካባቢዎቹ የትኛውም አይነት መንግስታዊ አገልግሎት እንደማይቋረጥና የፀጥታ ስራዎች በአስተዳደሮቹ የጋራ ተሳትፎ ይጠናከራል ነው ያሉት፡፡

ምስል፦ Seyoum Getu/DW

በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችም እንደማይቆምና ይልቁንም በፍጥነት እንደሚሰራ ያመለከቱት አስተዳደሮቹ፤ የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱና የተማሪዎች የቋንቋ ጉዳይ በነበረበት ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በየአከባቢዎቹ የሚሰጡ መንግስታዊ አገልግሎቶች ላይ ቋንቋ ምንም አይነት ተፅእኖ እንዳያሳርፍ እንደሚደረግም ተነግሯል፡፡ ወደ ኦሮምያ ልዩ ዞን የተካለሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችም ሆነ ከኦሮሚያ ወደ አዲስአበባ የተካለሉም ተጠቃሚዎቹ እጣ የወጣላቸውና ከዚህ በፊትም ሲገለገሉበት የነበሩ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ለበርካታ ዘመናት ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ በተለይ ከሰባት ዓመታት በፊት ኢህአዴግ ያስተዋወቀው የመዲናዋ 100 ኪ.ሜ. ራዲየስ ያካልላል ተብሎ የነበረው ማስተር ፕላን የህዝቡን እምቢተኝነት አስከትሎ በአገሪቱ ከባድ ቀውስ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ማስተር ፕላኑ አዲስ አበባን እና የኦሮሚያ አካባቢዎችን በስፋት የሚያስተሳስር ነው ቢባልም፣ በኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞን ቀስቅሶ ለመጣው መንግስታዊ ለውጥ አንዱ ምክንያት መሆኑን ይጠቀሳል። 
ሥዩም ጌቱ 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW