1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ ፈረሰች፥ ውይይት

እሑድ፣ መጋቢት 22 2016

የአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ፦ መንግሥት ከተማዪቱን ለማዘመን ባለው ርምጃ ፈርሳለች። በእቴጌ ጣይቱ አስተውሎትና በዳግማዊ አጤ ምንሊክ ፈቃድ አዲስ አበባ በ1879 የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ተቆረቆረች። የከተማዪቱ ቀዳሚና ዘመናዊ አካል የነበረችው ፒያሳ ዘንድሮ ከ1 ክፍለ ዘመን በኋላ በትዝታ ማኅደር ውስጥ ብቻ በነበር ቀርታለች፦ ሳምንታዊ ውይይት።

ምስል Seyoum Getu/DW

ከ3600 በላይ ባብዛኛው የቀበሌ ቤቶች መፍረሳቸው ተናግሯል

This browser does not support the audio element.

የአዲስ አበባ እምብርት ፒያሳ፦ መንግሥት ከተማዪቱን ለማዘመን ባለው ርምጃ ፈርሳለች ። በእቴጌ ጣይቱ አስተውሎት እና በዳግማዊ አጤ ምንሊክ ፈቃድ አዲስ አበባ በ1879  የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ተቆረቆረች ። የከተማዪቱ ቀዳሚ ዘመናዊ አካሏ የነበረችው ፒያሳ ዘንድሮ ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ በትዝታ ማኅደር ውስጥ ብቻ በነበር ቀርታለች ።

ጠቅላይ ሚንስተር አብይ አሕመድ የከተማዪቱን ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ሰብስበው እንዳነጋገሩ ዐስታውቀዋል ። «የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ሥራ ሂደት» ያሉትን በገመገሙበት ስብሰባም ባለስልጣናቱ በፈረሳው እንዲገፉበት ትእዛዝ አስተላልፈዋል ።

የፒያሳ ፈረሳ በጠቅላይ ሚንስትሩ እና ባለስልጣናቱ አንደበት፦ «አዲስ አበባን አፍርሶ የመሥራት፥ መልሶ መገንባት» ድርጊት ነው ተብሏል ። ድርጊቱም «የማጽዳት» በሚል በባለስልጣናቱ በተዋረድ በተደጋጋሚ ተገልጧል ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ባለስልጣናቱ ፈረሳውን የሚያከናውኑት «አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ» ማድረግ መሆኑን በተደጋጋሚ ተናግረዋል ።

መሃል ፒያሳ የነበረበት አካባቢ ከፈረሱ ሕንጻዎች በከፊል። ፒያሳ የአዲስ አበባ እምብርት ናት። በጣልያንኛ ቋንቋ ስያሜ የምትጠራው ፒያሳ የከተማ እና ከተሜነት መገለጫዎችን ያቀፈች ነበረች። ሲኒማ ቤቶች፣ ወርቅ ቤቶች ፣ ኬክ ቤቶች ፣ ሆቴሎች፣ የምሽት መዝናኛ ቤቶች ፣ ሙዚቃ ቤቶች እና ሌሎችም የሚገኙበት ነበር።ምስል Solomon Muchie/DW

ብዙዎች ስለ ፒያሳ አራት ኪሎና የአዲስ አበባ የጥንት መንደሮች ፈረሳ ሲናገሩ፦ ዋነኛ ዐላማው «ልማት» ሳይሆን ሌላ መሆኑን ያብራራሉ ። የከተማዪቱን ኅብረተሰብ የቆየ ጠንካራ ትስስር የመበጣጠስ፥ ታሪክ እና ቅርስ የማውደም አካል ነውም ሲሉ አስረግጠው ይናገራሉ ።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ «ቅርስ ማለት ምን ማለት ነው?» ሲሉ ጠይቀው ራሳቸው መልስ ሰጥተዋል ። «ማንም ያቦካው ጭቃ ሁሉ ቅርስ አይደለም» ሲሉም አጣጥለው ተናግረዋል ። ቅርስ ምን እንደሆነም ለባለስልጣናቶቻቸው አብራርተዋል ። በእርግጥ ቅርስ ማለት ምንድን ነው? ብዙ የአዲስ አበባ ትውስታዎች እና ታሪካዊ ቤቶችን ያቀፈችው አራዳ ወይንም ፒያሳን እንዲህ በጥድፊያ ማፍረስ ያስፈለገው ለምንድን ነው? የከተማዪቱ ነዋሪ ኅብረተሰብስ ተጎጂ ሳይሆን ተጠቃሚ እንዲሆን ምን ያህል ተሳታፊ ተደርጓል?

ጣይቱ ሆቴል በኢትዮጵያ የመጀመርያው ዘመናዊ ሆቴል ነው። አሁን በእድሳት ላይ ይገኛል። ከዚህ ሆቴል አጠገብ ብዙ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቴች እና ቡና ቤቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ይህ አንዱ ነበር።ምስል Solomon Muchie/DW

በሳምንታዊው የአንወያይ መሰናዶ ካተኮርንባቸው ዐበይት ጉዳዮች የተወሰኑት ናቸው ። በውይይቱም 3 እንግዶች ተሳትፈዋል ። 

1- ሠይፈ-ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር)፦ የእናት ፓርቲ ፕሬዚደንት እና የትብብር ፓርቲዎች የወቅቱ ሊቀመንበር እንዲሁም

2- ወ/ሮ እናት ዓለም መለሠ፦ የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽ ኃላፊ

3- አቶ ክንፈ-ሚካኤል ኃይለ-ሥላሴ፦ በጀርመን ሀገር የሥነ-ሕንጻ ባለሞያ

ሙሉ ውይይቱን በድምፅ ማጫወቻው ማድመጥ ይቻላል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW