የአዲስ አበባ «ኮሪደር ልማት»ን የጎበኘው ጎርፍ
ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017
የአዲስ አበባ «ኮሪደር ልማት»ን የጎበኘው ጎርፍ
የአዲስ አበባ «ኮሪደር ልማት» በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎችን ታሳቢ አድርጎ ይሆን?
ባለፈው 2016 ዓ.ም. የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ከቀጠፉ ፓለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውሶች ባለፈ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችም የብዙዎቹን ሕይወት ነጥቀዋል። በተለይም በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶች በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ መጥለቅለቆችን ታሳቢ ያደረጉ አለመሆናቸው በባለሞያዎች በተደጋጋሚ ይገለጣል። ዳሩ ግን የባለሞያዎቹ አስተያየት ዛሬም ሰሚ ያገኘ አይመስልም።
የአዲስ አበባ መንገዶችንና የመንገድ ዳርቻዎችን ያስጌጠው «የኮሪደር ልማት» የተሰኘው ኘሮጀክት ውስን ክፍል መጠናቀቁ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና በከተማዋ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. መባቻ ላይ ከተበሰረ ወራቶች ሳይቆጠሩ መንገዶቹ በጎርፍ ተጥለቀለቁ። ይህ ብዙ የተነገረለት፣ ብዙ ያወዛገበው፣ እንዲሁም አያሌ ጥሪት የፈሰሰበት «የኮሪደር ልማት» በደረሰበት የጎርፍ ጉዳት አሽከርካሪዎችንም ሆነ ነዋሪውን ከአንዱ የከተማዋ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ አላፈናፍን ሲልም ተስተውሏል።
በንግድ ሥራ እንደሚተዳደር የገለጸልን አቶ ቴዎድሮስ በአዲስ አበባ ከተማ ምሥራቃዊ ክፍል የሰሚት አካባቢ ነዋሪ ነው። በሚያሽከረክራት መኪና በከተማዋ ሲንቀሳቀስ ያስተዋለውን፤ «ጉርድ ሾላ ነው የጎርፍ ችግር በስፋት የተስተዋለው። በቃ የውሃ ማፋሰሻዎች በየመንገዱ አልተገነቡም። ያሉት የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎችም በአግባቡ ያለመፀዳታቸው ዋነኛ መንስኤ ናቸው ብዬ አስባለሁ።» በማለት ለዶቼ ቬለ ገልጿል።
የኮሪደር ልማቱ ውጤትና ተግዳሮቱ
«በከተማዋ በቂ የፍሳሽ ማስወገጃዎች በሌለበት «የኮሪደር ልማት» ግንባታዎች መከናወናቸዉ» ተገቢ ያለመሆኑን ያነሳው አቶ ቴዎድሮስ ጎረፉ የተከሰትው በግንባታ ሂደት ቀደም ሲሉ የነበሩት የጎርፍ ማፋሰሻዎች በአግባቡ ስላልተጸዱ ነው ባይ ነው።
ሞያዊ እይታዎች
ለዶቼ ቬለ ሞያዊ እይታቸውን ያካፈሉን በአገረ ጀርመን ትምህርታቸውን የተከታተሉትና አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲቪል ምህንድስና ትምህርት ክፍል የመንገድ እና የትራንስፓርት ምህንድስና መምህር የሆኑት ዶ/ር ኢንጂነር አስረስ ስሜነህ፥ «አዲስ አበባ ውስጥ የሚስተዋለው መንገድ የሚዘጋ ከፍተኛ የጎርፍ መጠን የሚያሳየው የውኃ ማፋሰሻ ተብለው የተሠሩት ሥራዎች የዲዛይን ውሱንነት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ» ሲሉ ተናግረዋል። «የመንገድ መሠረተ ልማቶች ዝናብ በዘነበ ቁጥር የሚዘጋጉ ከሆነ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የከፋ ዝናብ ቢዘንብ ችግሩ ከዚህ የከፋ ሊሆን እንደሚችል»ም ያስጠነቅቃሉ።
የሰሞነኛው የአዲስ አበባ ጎርፍ ቢያንስ የ 14 ሰዎችን ህይወት አጠፋ
ለ«ኮሪደር ልማት» ፕሮጀክቱ 40 ቢሊዮን ብር የበጀት እቅድ ተይዞለት «ወጪ ቆጣቢ» በሆነ መንገድ በ33 ቢሊዮን ብር ሥራው መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርገዋል። በመሬት ውስጥ ዘመናዊ የደህንነት ካሜሬ እንደተቀበረ ያነሱት ከንቲባዋ እዚያዉ መሬት ውስጥ ለውስጥ በአየርን ንብረት ለውጥ ሳቢያ ሊከሰቱ የሚችሉ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል ስለተሠሩ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ግን ያሉት ነገር የለም።
የመንገድ ኮሪደር ልማቱ እና የተነሺዎች ጥድፊያ በአዲስ አበባ
የ«ኮሪደር ልማት» መቼ ወደ ትግባራ ገባ?
በሙሉ መጠሪያዉ «የአዲስ አበባ የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ግንባታ» የተሰኘው ይኸ ፕሮጀክት ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በከተማዋ አራት የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲደረጉ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው ሦስተኛ ዓመት ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ነበር።
የ«ኮሪደር ልማት» ፕሮጀክቱ አራት የከተማዋን አቅጣጫዎች ያካልላል። 7 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከአራት ኪሎ ተነስቶ በመስቀል አደባባይ እስከ ቦሌ ድልድይ የሚዘልቅ ሲሆን 6.9 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሌላኛዉ መስመር ደግሞ ቦሌ አየር ማረፊያ መንገድን መነሻው አድርጐ እስከ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ ይደርሳል። 6.4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነዉ ሦስተኛው መስመር መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይን መነሻው በማድረግ በአራት ኪሎ በኩል ዓድዋ ድል መታሰቢያ አካባቢን መዳረሻው ያደርገል። የተቀረው 10 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው መንገድ ከመሀል ፒያሳ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ዞሮ በቸርችል ጐዳና ለገ-ሃር ሜክሲኮ በመድረስ እስከ ሳርቤት የሚያካልል ነው።
ከባድ ዝናብ እና የዝናብ እጥረት ያስከተለዉ አደጋ
የከተማ አስተዳደሩ «የመንገድ ኮሪደር ልማቶቹ ሁለንተናዊ የመንገድ ዘመናዊነትን እና ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን» ያሟሉ መሆናቸው ይገልጣል። ሆኖም ከተባበሩት መንግሥታት 17ቱ የልማት ግቦች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው «የስማርት ሲቲ» ንድፈ ሃሳብና አተገባበር፥ ዜጋ ተኮር በሆነ መልኩ መሠረተ ልማቶችንና መንግሥታዊ አስተዳደርን በመረጃና ተግባቦት ቴክኖሎጂ የሚያበለፅግ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ መላመጃ ስልቶች ጋር የሚያስተሳስር እና የሕዝብን ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ የሚያቀላጥፍ የተቀናጀ የዘመናዊ ከተማ ልማት ስርዓት ነው።
ዶ/ር ኢንጂነር አስረስ «የኮሪደር ልማቱ» የብስክሌት መንገድ ያለው መሆኑን በበጎ ቢያነሱም በጣም ሰፊ እና ጥልቀት ያላቸውን የ«ስማርት ሲቲ» መስፈርቶች እና ጠቋሚዎችን አሟልቷል ለማለት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።
የጎርፍ ቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች አስፈላጊነት
አዲስ አበባ በመንገድ ዳርቻዎች ከተተከሉ ጠባብ ቱቦዎች ባለፈ፤ የጎርፍ አደጋዎችን ማስቀረት የሚችሉ ብሎም እንደ ቴሌ ኮሚኒኬሽን፣ ውኃና ፍሳሽ እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያሉ መሠረተ ልማቶችን አስተሳስሮ የሚያቀናጅ የመሬት ውስጥ ዋሻ አልባ ከተማ ነች። «የኮሪደር ልማቱ»ን በፍጥነት (በሦስት ወራት) ስለመጠናቀቁ እንጂ ስለ ዘላቂ የከተማ ልማት እና የአየር ንብረት ለውጥ መላመጃ ትሩፋቶች አልተነገረም አሊያም አልተጠየቀም።
ዶቼ ቬለ ወደ ከተማ አስተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ጋር እነዚህንና ሌሎች ተያያዠ ጥያቄዎችን ይዘን በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ልናገኛቸዉ አልቻልንም። ዶ/ር ኢንጂነር አስረስ ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጎርፍ ችግሮችን ለመቅረፍ አሊያም ለመላመድ የሚያስችሉ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተጣጣሚ ንድፎችና እቅዶች አስፈላጊ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል። ትላልቅ የግንባታ ኘሮጀክቶችም ሲተገበሩ በቂ ጥናት ላይ የተመሰረቱ ቢሆኑ ውጤታቸው ዘላቂነት ሊኖረው እንደሚችል ምክራቸውን ለግሰዋል።
ዳግም ተረፈ
ሸዋዬ ለገሰ