1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ “የኮሪደር ልማት” በዚህ ወቅት አስፈላጊ ነው ወይስ አንገብጋቢ?

Eshete Bekele
እሑድ፣ ኅዳር 8 2017

የአዲስ አበባ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሹ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም ይሁኑ ዋና ከተማዋን በጥልቀት ያጠኑ ባለሙያዎች ይስማማሉ። በከፍተኛ ወጪ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኮሪደር ልማት በዚህ ወቅት አስፈላጊ ነው ወይስ አንገብጋቢ? ፒያሳ እና ካዛንቺስን ለመሳሰሉ ነባር ሠፈሮች ነዋሪዎችስ ምን ይዞ መጣ? በዚህ ውይይት ሦስት እንግዶች ተሳትፈዋል።

በካዛንቺስ ኮሪደር ልማት ቤቶች ሲፈርሱ
በሁለተኛው ምዕራፍ የኮረደር ልማት በተካተተችው በካዛንቺስ ባለፉት ሣምንታት በርካታ የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ፈርሰዋል። በሁለተኛው ምዕራፍምስል Solomon Muche/DW

የአዲስ አበባ “የኮሪደር ልማት” በዚህ ወቅት አስፈላጊ ነው ወይስ አንገብጋቢ?

This browser does not support the audio element.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ የሚያደርገው “የኮሪደር ልማት” ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም የአዲስ አበባን ፈለግ በመከተል ላይ ይገኛሉ። ዕቅዱ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የኑሮ ውድነት እና የሥራ አጥነት በበረታበት ወቅት ነው። ከፍተኛ የመኖሪያ ቤቶች እጥረት ያለባት የኢትዮጵያ ዋና ከተማዋ ነዋሪዎች መብራት እና ውኃ የመሳሰሉ መሠረታዊ ግልጋሎቶች እጥረት ይፈታተናቸዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት 33 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን በሐምሌ 2016 የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል። በዕቅዱ መንገዶች፣ መጸዳጃ ቤቶች እና የሕዝብ መዝናኛዎችን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ-ልማቶች በመገንባት ላይ ናቸው።

በዚሁ ዕቅድ ፒያሳ እና ካዛንቺስን በመሳሰሉ አካባቢዎች ነባር ሠፈሮች እየፈረሱ ቦታቸውን ለሌሎች ግንባታዎች እየለቀቁ ይገኛሉ። በመጀመሪያው ምዕራፍ በተካተተችው ፒያሳ የነበሩ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት እና ልዩ ልዩ ግንባታዎች ከፈረሱ በኋላ ቦታው በሊዝ ለሽያጭ ቀርቧል። 

ባለፉት ሣምንታት በካዛንቺስ በርካታ የመኖሪያ ቤቶች እና የንግድ ተቋማት ፈርሰዋል። በሁለተኛው ምዕራፍ በ8 ኮሪደሮች 2 ሺሕ 879 ሔክታር መሬት የሚሸፍን መሆኑን ከንቲባዋ አዳነች አቤቤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በተደረገ ግምገማ ላይ ሪፖርት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናትም ይሁኑ አዲስ አበባን በቅጡ ያጠኑ ባለሙያዎች የዋና ከተማዋ የመኖሪያ ቤቶች እና የመሠረተ-ልማት ችግሮች መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው ይስማማሉ። ይሁንና ከፍተኛ በጀት ሚጠይቀው ዕቅድ ምን ያክል አንገብጋቢ ነው? በነባር ሠፈሮች ነዋሪዎች ኤኮኖሚ እና ማኅበራዊ መስተጋብር ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል?

በዚህ ውይይት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ፣ በበርሚንግሐም ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ሥር በሚገኘው የዓለም አቀፍ ልማት ክፍል (International Development Department) ተመራማሪ ዶክተር ኤዛና ሐዲስ እና በፊንላንድ ራምቦል በተባለ ተቋም የከተማ መሠረተ-ልማት የንድፍ (Design) ባለሙያ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ ቴዎድሮስ ዱጋሳ ተሳትፈዋል።

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW