1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ የፒያሳው የአራዳ ሕንፃ ሱቆች መፍረስ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 25 2015

ዶቼ ቬለ ከተማ አስተዳደሩ ማረጋገጥ ባይችልም ሱቃቸው ለፈረሰባቸው ሰዎች አራዳ አካባቢ በሕብረት ሆነው ሕንፃ የሚገነቡበት ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው አንድ ሰው ገልፀዋል። ከባለ ሱቆቹ እና ዛሬ በአካባቢው ቅኝት አድርገን ባገኘነው መረጃ ደግሞ ከረጅሙ አራዳ ሕንፃ በቀር ሌሎች የንግድ ሱቆችም እንደሚፈርሱ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በየአካባቢው ከሚገኙ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውኃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸውንና ዮለየ አካባቢው የልማት ሥራዎች ክፍያውን በመክፈል ተሳታፊ የነበሩ መሆኑንና ከሕግ ውጪ ለሆነ የቤት መፍረስ መዳረጋቸውን ባወጣው መግለጫ ገልፆ ነበር።።
ሕገ ወጥ ግንባታን የማፍረስ እርምጃ ሕጋዊ ሂደትን መከተል እና እርምጃው ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊ ቀውስ ከግንዛቤ በማስገባት አማራጭ መፍትሔዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል በማለት በኢሰመኮ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይራክተር ዶክተር ብራይትማን ገብረ ሚካኤል ገልፀው ነበር። ምስል Solomon Muchie/DW

የአዲስ አበባ ፒያሳው የአራዳ ሕንፃ ሱቆች መፍረስ

This browser does not support the audio element.

በአዲስ አበባ ከተማ ረጅም እድሜ ካላቸው ቤቶች አንዱ የሆነውና መሃል ፒያሳ ከመስተዳድሩ ቅጥር ግቢ ዝቅ ብሎ ያለው አራዳ ሕንፃ ላይ ወደጎን ያሉት 42ት ሱቆች ባለፈው ሳምንት እንዲፈርሱ ተደርጓል። ለረጅም ዓመታት የንግድ ሱቅ ሆነው በግለሰብ ተከራዮች ሥር የቆዩት እነዚህ የከተማ አሥተዳደሩ ንብረት የሆኑ ቤቶች እንዲፈርሱ የተደረገው በመጠናቀቅ ላይ ለሚገኘው "ዓድዋ ዜሮ ዜሮ" ለተባለው ፕሮጄክት የአረንጓዴ ሥፍራ ማስፋፊያ ተፈልጎ መሆኑን በሥፍራው ሱቅ የነበራቸውና በዚያው ከ ሠላሳ ዓመታት በላይ የሠሩ ሰው ለ ዶቼ ቬለ ገልፀዋል። 

ዶቼ ቬለ ከተማ አስተዳደሩ ማረጋገጥ ባይችልም ሱቃቸው ለፈረሰባቸው ሰዎች በዚያው አራዳ አካባቢ በሕብረት ሆነው ሕንፃ የሚገነቡበት ቦታ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው ያነጋገርናቸው ሰው ገልፀዋል። 

ከባለ ሱቆቹ እና ዛሬ በአካባቢው ቅኝት አድርገን ባገኘነው መረጃ ደግሞ ከዋናው ረጅሙ አራዳ ሕንፃ በቀር ያሉት ሌሎች የንግድ ሱቆችም እንዲፈርሱ በመወሰኑ ለባለሱቆቹ ይህ እንደተነገራቸው ለማወቅ ችለናል። በአዲስ አበባ ፒያሳ አከባቢ በቤቶች ፈረሳ መውደቂያ አጣን ያሉ ነዋሪዎች

የአንድ ከተማ መኖሪያ ሰፈሮች፣ የማሕበረሰብ አሰፋፈሮች በዘፈቀደ የሚገኙ አይደሉም የሚሉት የሥነ ሕንፃ ጥበብ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ መኮንን ቤቶችን "በዘፈቀደ ማፍረስ ወይም ማጎሳቆል ተገቢ አይደለም" ብለዋል። 

ሱቁን ሠላሳ ዓመት ያህል ሠርቼበታለሁ 

"በአንድ ጊዜ ነው የሆነው ጉዳዩ። ዝም ብሎ ላላ ያለ ቶሎ ትወጣላችሁ ፣ ጊዜ የላችሁም በሚል አንድ ቀን ሰበሰቡን። ከዚያ በቃ ስለሚፈለግ ትወጣላችሁ ፣ ከዚያ በአክሲዮን ትደራጃላችሁ መሬት እንሰጣችኋለን፣ ከባንክ ጋር ተያይዞ ትሠራላችሁ አሉን። እኛ ወረቀትም ይሰጡናል ስንል እንደገና በ ሃያ ቀኑ ቢሮ ከተዘጋ በኋላ መጥተው እስከ እሁድ ስድስት ሰዓት እንድትለቁ ብለው የቃል ማስጠንቀቂያ ሰጡን። ተው ብንልም በፍፁም ተብለን በዚህ ሁኔታ ለቀቀን። እስካሁን ድረስ እንሰጣችኋለን ብለዋል ምንም የተጨበጠ ነገር የለም። መጓጓዣ እንኳን ምንም ነገር የተሰጠን ነገር የለም። ለአንድ ሰው ሃያ አምስት ካሬ እንሰጣችኋለን ነው ያሉን"
የት ነው እንሰጣችኋለን የተባላችሁት ? በሚል የጠየቅናቸው አስተያየት ሰጪ እዚያው አራዳ እካባቢ በማለት ገልፀዋል። 

ይህንን ያደረገው ማን ነው? ቦታውስ ለምን ጉዳይ ተፈለገ ? 

"እኛን ያነጋገሩን ክፍለ ከተሞች [ አራዳ ] ናቸው። ቤቱ የመዘጋጃ ነው። ሥራ ሲበዛበት ለቀበሌ አስተላለፈ። ውላችን ቀበሌ ነው የነበረው። እኛ በጨረታ ገዝተን ነው የገባነው ድሮ። እንዲያውም አንድ ሰሞን ካርታ ሁሉ ሊሰጣችሁ ነው የሚሻል ወሬ ነበር። አልሆነም። ቦታው ለአድዋ ዜሮ ዜሮ ፕሮጀክት የአረንጓዴ ሥፍራ ማስፋፊያ ተፈልጓል ነው የተባለው" ።


በአዲስ አበባ ቤቶችን ለልማት የማፍረስ ተግባር 

ከብዙ አመታት በፊት በኢህአዴግ ዘመን መርካቶ አከባቢ ከአንዋር መስኪድ ፊት ለፊት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ይኖሩበት የነበረው የአሜሪካን ግቢ መፍረሱ እና ዜጎች ከሚኖሩበት ቦታ መበተናቸው እና ድርጊቱን ለምን ብለው የተቃወሙትም ለጉዳት መዳረጋቸው ይታወሳል።የቤቶች ፈረሳና እርምጃዉ ያስከተለዉ ጣጣ
ሸገር የተባለው ከተማ ከመዋቀሩ በፊት በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ በነበሩ ከተሞች ዜጎች በሕጋዊ ትምምን ገንዘብ ፈሰስ አድርገው ቤት ከሰሩ በኋላ ቤቴቻቸእ ሲፈርስባቸው ቆይቶ በኋላም ከተማው ከተዋቀረ በኋላ በብዙ ሺህ የሚገመት ቤት ሕገ ወጥ ነው በሚል የሃይማኖት ተቋማት ጭምር ፈርሰዋል።
ፒያሳ ላይ የነበረው ታሪካዊው አንበሳ መድኃኒት ቤት በተመሳሳይ ቦታው ለልማት ተፈልጓል ተብሎ ፈርሷል። እስካሁን ግን ቦታው ላይ የተጀመረ የልማት ሥራ አለመኖሩ ይታያል።
ፈንድቃ የተባለው የባህል ቤት ሊፈርስ ነው ተብሎ ከብዙ ጩኸት በኋላ ሳይፈርስ መቅረቱም ይታወሳል።
አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለልማት ሥራ ይፈለጋል ተብሎ የጥንቱ አራዳ ሕንፃ ሥር ላይ ያሉት እድሜ ጠገብ ሱቆች እየፈረሱ ነው።
ሕገ ወጥ ግንባታን የማፍረስ እርምጃ ሕጋዊ ሂደትን መከተል እና እርምጃው ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊ ቀውስ ከግንዛቤ በማስገባት አማራጭ መፍትሔዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል በማለት በኢሰመኮ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይራክተር ዶክተር ብራይትማን ገብረ ሚካኤል ገልፀው ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በየአካባቢው ከሚገኙ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውኃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸውንና ዮለየ አካባቢው የልማት ሥራዎች ክፍያውን በመክፈል ተሳታፊ የነበሩ መሆኑንና ከሕግ ውጪ ለሆነ የቤት መፍረስ መዳረጋቸውን ባወጣው መግለጫ ገልፆ ነበር።።


የሥነ ሕንፃ ጥበብ ባለሙያ አስተያየት 

የሥነ ሕንፃ ጥበብ ባለሙያው አቶ ዮሃንስ መኮንንን በዚህ ጉዳይ የልማት ሥራዎች ከተሞች ውስጥ እንዴት ትናንትን ከዛሬና ከነጋ ሊያጣጥሙ ይገባል ብለን ጠይቀናቸዋል።
"ልማት ማለት አንድን ቦታ ለማህበረሰብ አገልግሎት እንዲመች አድርጎ ማዘጋጀት ነው እንጂ ረጃጅም ሕንፃ ወይም ደግሞ በዘመናዊ ቁሳቁስ የተገነባ አዳዲስ ሕንፃ መገንባት ላይሆን ይችላል። እሱ ፍላጎቱም ካለ ለዚህ ተለይተው የሚመረጡ ቦታዎች አሉ። እንደዚህ ያሉ የቅርስ ቦታዎች ፣ ኪነ ሕንፃዎች የአንድ ማህበረሰብ ትውስታ አካል ናቸው። እነኚህን ማፈራረስ አንድ ማህበረሰብ ቋሚ የሆነ የማንነት ፣ የጋራ ትውስታ እንዳይኖረው ያደርገዋል" በሸገር ከተማ የቤቶች እና የእምነት ተቋማት ፈረሳ ቆሞ ሕጋዊነቱ እንዲፈተሽ ኦፌኮ ጥሪ አቀረበ

በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አስተያየት ለመጠየቅ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ባለመሳካቱ በዘገባው አልተካተቱም።

ፒያሳ ላይ የነበረው ታሪካዊው አንበሳ መድኃኒት ቤት በተመሳሳይ ቦታው ለልማት ተፈልጓል ተብሎ ፈርሷል። እስካሁን ግን ቦታው ላይ የተጀመረ የልማት ሥራ አለመኖሩ ይታያል።ምስል Seyoum Getu/DW
መሃል ፒያሳ ከመስተዳድሩ ቅጥር ግቢ ዝቅ ብሎ ያለው አራዳ ሕንፃ ላይ ወደጎን ያሉት 42ት ሱቆች ባለፈው ሳምንት እንዲፈርሱ ተደርጓል። ምስል Solomon Muchie/DW

 

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW