1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመከላከያ ሰራዊት ወሰድኩ ያለው ወታደራዊ እርምጃዎች

ሰኞ፣ ሚያዝያ 13 2017

መከላከያ በመግለጫው ሚያዚያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወረዳ “ፅንፈኛ” በሚል በተጠቀሱ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደ ወታደራዊ እርምጃ፤ ከ50 በላይ ታጣቂዎች መገደላቸው ተብራርቷል። በጎጃምም በአንድ ቀን ብቻ ከ300 በላይ ታጣቂዎችን መገደላቸው ገልጿል፡፡

Äthiopien | Äthiopische Nationale Verteidigungsstreitkräfte
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

የአገር መከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ እርምጃዎች

This browser does not support the audio element.

የአገር መከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ እርምጃዎች 
የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ታጣቂዎች ላይ ሰፋፊ ያላቸው ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ «ድልም እየቀናው» መሆኑን አመልክቷል፡፡
እንደ መከላከያ ተደጋጋሚ ይፋዊ መረጃዎች የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በሁለቱ የአገሪቱ ትላልቅ ክልሎች ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላት ላይ በወሰዱት ወታደራዊ እርምጃዎች በመቶዎች መገደላቸውንና የቡድን ጨምሮ የተለያዩ ጦር መሳሪያዎች መማከረካቸውም ተነግሯል፡፡
ወታደራዊ ዘመቻዎች  
እንደ መከላከያ መግለጫ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ሚያዚያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወረዳ “ፅንፈኛ” በሚል በተጠቀሱ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደ ወታደራዊ እርምጃ፤ ከ50 በላይ ታጣቂዎች መገደላቸው ተብራርቷል። የመከላከያ ሰራዊቱ በጎጃም በአንድ ቀን ብቻ ባደረገው ወታደራዊ ኦፕሬሽንም ከ300 በላይ ታጣቂዎችን መገደላቸው ነው በዚሁ ትናንት በወጣው ተመሳሳይ መግለጫ የተመላከተው፡፡እንደ መረጃው በነዚህ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች ከ 30 በላይ ታጣቂዎች ቆስለው የጦር መሳሪያዎች መማረካቸው ተነግሯል። 
በዚሁ መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በቱቲ ቀበሌ እንዲሁም በሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ “የአካባቢውን ሰላም ለማደፍረስ ሲንቀሳቀስ የነበረ ያለውን መንግስት «ሸኔ» ብሎ በሚጠራቸው ታጣቂዎች ላይ መከላከያ በወሠደው እርምጃ በቁጥር ባይገለጽም በርካቶች መገደላቸውና መቁሰላቸው ተገዷል። 
በተመሳሳይ ዜና  በሰሜን ሽዋ ዞን ሂዳቡ አቦቴ ወረዳ በርካታ የጦር መሳሪያዎችንና ተተኳሾችን በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለበት ወታደራዊ እርምጃ መወሰዱን ሚያዚያ 08 ቀን 2017 ዓ.ም የወጣው መግለጫ ያትታል፡፡ 
ሚያዝያ 05 ቀን 2017 ዓ.ም የወጣው የተቋሙ መግለጫም እንዲሁ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በተለያዩ ዞኖችና የዞኖቹ ወረዳዎች በየክልሎቹ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ታጣቂዎቹ ላይ ኪሳራ መድረሱ ተጠቁሟል፡፡
የወታደራዊ ዘመቻዎቹ ውጤት
ለመሆኑ መሰል ወታደራዊ ዘመቻዎች ባለፉት ሰባት ዓመታት ሲወሰዱ ከቆዩት ወታደራዊ እርምጃዎች ጋር ሲነጻጸሩ ምን ልዩነት አላቸው? በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ እጩ እና የሰላምና ደህንነት ባለሙያ አቶ መብራቱ ገርጂሶ «አይደለም» ባይ ናቸው፡፡ “በእውነቱ መንግስት በተደጋጋሚ እንደዚህ አይነት መግለጫ ማውጣቱ የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል” የሚሉት ባለሙያው በዚህ መንገድ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተስተዋሉ ቀውሶች ሲሰፉ ነው እንጂ ሲጠፉ አልታየም ነው ያሉት፡፡
በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት የፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያ እና ተንታኝ አቶ ሰለሞን ተፈራ ደግሞ የመንግስት ፀጥታ ሃይሎች ወደ ጦርነት ለመግባት የተገደዱበት ጉዳይ ላይ በማተኮር ነው አስተያየታቸውን ያጋሩን፡፡ “መከላከያ ሰራዊት ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ የሰላም እጦት ችግርን ጨምሮ ባሏት ልዩልዩ ችግሮች ላይ ግን መንግስት የመወያየት የመደራደር ፍላጎት እንዳለው አውቃለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ መንግስት ያቀረባቸው ጥሪዎች አመራሮችን በሚገድሉና ትምህርት ቤትን ጭምር በሚያወድሙ በታጣቂዎቹ ተቀባይነት በማጣቱ መንግስት እያደረገ ያለው በተሰጠው ሃላፊነት ተቋማትና ህግን የመከላከል ተግባር ነው” በማለት ምንግስት ታጣቂዎቹ ተገደገው ወደ ድርድር እንዲመጡ እየጣረ መሆኑን እንደሚገነዘቡ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ወታደራዊ ዘመቻዎች እያካሄድኩ ነው ብሏል።ምስል፦ AMANUEL SILESHI/AFP/Getty Images


ሰላማዊ አማራጭ
አቶ ሰለሞን ለዘላቂ ሰላም መስፈንሰላማዊ አማራጮች እድል ሊሰጣቸው እንደሚገባውም ቢያምኑም እውነታው ያንን ባለመፍቀዱ ወታደራዊ እርምጃው ግድ ሆኗል በማለት ነው ሃሳባቸውን ያከሉት፡፡ “አመራሮችን፣ የአገር ሽማግሌን እና የሃይማኖት አባቶችን የሚገርፍ የሚገድል አካል ለሰላም ዝግጁ ነው ተብሎ ስለማይታሰብ መንግስት ግለሰቦችን እና ተቋማትን በመጠበቅ መንግስታዊ ሃላፊነቱን ለመውሰድ ሌላ አማራጭ የለውም” ብለዋል፡፡
የሰላምና ደህንነት ባለሙያው አቶ መብራቱ ግን አስተያየታቸውን የሰጡት ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ “በዚያ በኩል ዘላቂ  መፍትሄ  ይመጣል ብዬ አላምንም፡፡ ዘላቂ መፍትሄ  የሚመጣው በመነጋገር ሰጥቶ በመቀበል ነው፡፡ መንግስት የሚወስደው እርምጃ ውጤታማ እንኳ ቢሆን መቼ መልሶ እንደሚያቆጠቁጥ ስለማይታወቅ እውነተኛ እርቅ አገራዊ መግባባት ላይ በመድረስ ለአገር መሰረት ለመጣል ችግሮችን በሰላማዊ መንገዱ መፍታት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የቋጩት፡፡  
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW