1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአገው ብሔራዊ ሸንጎና የቅማንንት ዴሞካራሲ ፓርቲ  የምርጫ ዝግጅት

ረቡዕ፣ ሰኔ 9 2013

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ቢያሸንፍ የአገው ህዝብ በራሱ የሚተዳደርበትን ክልል እንደሚመሰርት አስታወቀ። የአገው ብሔራዊ ሸንጎ በአማራ ክልል ሦስት አካባቢዎች ይወዳደራል ተብሎአል። የቅማንንት ዴሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ በቀድሞው ሰሜን ጎንድር  23 እጩዎችን ለፌደራል እና ክልል ምክር ቤቶች እንደሚያወዳድር አመልክቷል።

Äthiopien | Zentral Gonde
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ሁለቱም ፓርቲዎች በምርጫው የሚወዳደሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ነዉ

This browser does not support the audio element.

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ቢያሸንፍ የአገው ህዝብ በራሱ የሚተዳደርበትን ክልል እንደሚመሰርት አስታወቀ። የአገው ብሔራዊ ሸንጎ በአማራ ክልል ሦስት አካባቢዎች ይወዳደራል ተብሎአል። የቅማንንት ዴሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ በቀድሞው ሰሜን ጎንድር  23 እጩዎችን ለፌደራል እና ክልል ምክር ቤቶች እንደሚያወዳድር አመልክቷል። ሁለቱም ፓርቲዎች በምርጫው የሚወዳደሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን  በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና ሌሎች  ምክንያቶች የተፈለገውን ያህል መራጭ እንዳልተመዘገበ ሁለቱም ፓርቲዎች ገልፀዋል፡፡  

የአገው ብሔራዊ ሸንጎና የቅማንንት ዴሞካራሲ ፓርቲ በምርጫው ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው ነው፡፡ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ አቶ አላምረው ይርዳው በስልክ እንደገለፁለን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚሳተፉበት 6ኛው አገራዊ ምርጫ በ21 የምርጫ ክልሎች 59 እጩዎችን ለክልልና ለፌደራል  የተወካዮች ምክር ቤቶች እንዲወዳደሩ አቅርቧል፤  20ዎቹ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ናቸው፡፡

የቅማንንት ዴሞክራሲ ፓርቲም ምክትል ሊቀመንበር አቶ አውግቸው ማለደ እንዳሉት ደግሞ ፓርቲያቸው በማዕከላዊ ጎንድር ዞን  በ2፣ በጭልጋ በ2፣ እንዲሁም በላይ አርማጭሆ፣ በደንቢያ፣ በቋራ፣ በመተማና በወገራ በእያንዳንዳቸው አንድ አንድ በአጠቃላይ በ9 የምርጫ ጣቢያዎች 23 እጩዎችን ለሁለቱም ምክር ቤቶች እንዲወዳደሩ አቅርቧል፣ 14ቱ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ናቸው፡፡

በመራጮች ምዝገባ ወቅት ከፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘና በሌሎችም ምክንያቶች በተለይ በዋግኽምራና ቅማንት አንዳንድ አካባቢዎች የተፈለገውን ያህል መራጭ እንዳልተመዘገበ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ሊቀመንበር አቶ አላምረው  ይርዳው ገልፀዋ ፡፡

የቅማንንት ዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አውግቸው፣ የፀጥታ ችግር ምክንያት በላይ አርማጭሆና በጭልጋ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት  የምርጫ ክልሎች የመጀመሪያ ዙር ምርጫ አይካሄድም ብለዋል፡፡

የአገው ብሔራዊ ሸንጎ በምርጫ ቢያሸንፍ የአገው ህዝብ በራሱ የሚተዳደርበትን ክልል እንደሚመሰረትም ፓርቲው አመልክቷል፡፡ ሆኖም ፓርቲው “እወዳደራለሁ” የሚልባቸው አካባቢዎች የጋራ ወሰን የሌላቸው፣ በመልከዓ ምድር የተለያዩና የተራራቁ ሆነው ሳለ እንዴት በአንድ ክልል ሊረተዳደሩ ይችላሉ? የሚል ጥቄ ከዶይቼ ቬለ የቀረበላቸው የፓርቲው ሊቀመንበር፣ አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጡት አስተያየት እንደሌለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የጋራ ምክር ቤት ከተመሰረተ ጀምሮ በፓርቲዎች መካከል የተሻለ መግባባትና በተግባር የተደገፉ ስራዎችም መሰራታቸውን አቶ አላምረው አመልክተዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን   

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW