የአጣዳፊ ተቅማጥና ትዉከት በሽታ በባቲ ወረዳ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2016በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባቲ ወረዳ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትበተለምዶ (አተት) መከሰቱን የወረዳው ጤና ጽ/ቤት አስታውቋል፣ የበሽታውን መስፋፋት ለመከላከል ባለፈው ሳምንት ችግሩ በታየባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶችና ታላቁ የባቲ ሰኞ ገበያም ተዘግተው መሰንበታቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፣ የአማራ ህብረተሰብ ጤና ተቋም በበሽታው የተያዙ 162 ህክምና እየተሰጣቸው ነው ብሏል፡፡
አጣዳፊ የተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ ከመጋቢት 27/2016 ዓ ም ጀምሮ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር መከሰቱን የወረዳው ጤና ጽ/ቤት የባቲ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የጥራት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ፉአድ ቶፊቅ በባቲ ወረዳ 5 ቀበሌዎች 86 ሰዎች በበሽታው ተይዘው ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነ አመልተዋል፡፡
“በባቲ ገጠር ወረዳ በሚገኙ ፉራ ጨቆቲ ፣ ሞቶና ጨለለቃ የሚባሉ ቀበሌዎች ናቸው፡፡5ኛ ደግሞ ኡሩንጉ ቀበሌ በሽታው ታይቷል” እንደ ባለሙያው 86 ሰዎች በሽታው ተገኝቶባቸው ህክምና እየወሰዱ ነው፡፡
የጤና ጽ/ቤቱ የጥራት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ፉአድ እንደሚሉት በሸታው የተከሰተው በአንድ እለት የጣለን ከባድ ዝናብን ተከትሎ በአካባቢው ያለው አንድ ወንዝን በቆሻሻ በመበከሉ ነው፡፡ የለይቶ ማቆያ ቦታ ተዘጋጅቶ ህክምናው እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡ከታማሚዎቹ አብዛኛዎቹ እያገገሙ አንደሆነም አቶ ቶፊቅ ተናግረዋል፡፡
ስማቸው እንዳጠቀስ የፈለጉ አንድ የባቲ ከተማ ነዋሪ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ከሳምንት በፊት በሽታው መጀመሪያ በተከሰተበት ፉራ ቀበሌ ያሉ ገጠር ትምህርት ቤቶችና ታላቁ የባቲ ፡፡ ገበያ ተዘግተው እንደነበር ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሰኞ የባቲ ታላቁ ገበያ ተዘግቶ ነው የዋለው፣ በሽታውን ለመቆጣጠር ሲባል የሰዎች እንቅስቃሴ ተገድቦ ነው የቆየው፣ በገጠር ፉራ ቀበሌ ውስጥ ያሉ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፣” ብለዋል፡፡
የመከላከል ስራው እየተሰራ ቢሆንም የበሽታው መስፋት በሌሎች ቀበሌዎች እንደ አዲስ እየታየ እንደሆነ የባቲ ከተማ
ነዋሪው ገልጠዋል፡፡
“የመከላከል ስራዎች አሉ፣ ግን አሁንም በሌሎች ቀበሌዎች አዳዲስ ሪፖርቶች እየታዩ ነው፣ ለምሳሌ “ኡሩንጉ” የሚባል ቀበሌ፣ አንድ በሽተኛ ተገኝቷል፣ ራቅ ብሎ ደግሞ “ጨለለቃ” ቀበሌም አዲስ ሪፖርት ተመዝግቧል፣ ይህ የሚያሳየው ህዝቡ ወደ ከተማ እየመጣ በሽታውን እየያዘ የመሄድ ነገር አለ ማለት ነው፡፡”
የወረዳው የጥራት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ፉአድ እንደነገሩን የመከላከልና የህክምና ስራው ተጠናክሮ እየቀጠለ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የባቲ ሰኞ ገበያ ትናንት የዋለ ቢሆንም ወደ ከተማው በሚያስገቡ 5 መግቢያና መውጫ ውሀና ሳሙና ተዘጋጅቶ ገበያተኛው ወደ ገበያው ሲወጣና ሲገባ እንዲታጠብ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ወደ ገበያ የመጣው የሰው ቁጥር ግን ገተለመደው ጋር ሲነፃፀር ከ15 ከመቶ እንደማይበልጥ አንድ የከተማዋ አስተያየት ሰጪ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በሽታው በባቲ ወረዳ መከሰቱንና 162 ሰዎች ታምመው ህክምና እየተሰጣቸው ነው ብለዋል፣ በሽታው በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ ልዩ ወረዳም ታይቷል ነው ያሉት፡፡
አስፈላጊ ግብዓቶችና የሰው ኃይል ከዞንና ከክልል ወደ ቦታዎቹ መላኩን የተናገሩትየጤና ባለሙያዎቹ፣ ግብዓቶች አሁን ያሉትን ታማሚዎች ለማከምም ሆነ ተጨማሪ ሊከሰት የሚችለውን ስጋት ለመቆጣጠር በቂ ናቸው ነው ያሉት፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ