በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ አለዉ ሲሉ አርሶደሮች ቅሬታ አቀረቡ
ሐሙስ፣ መጋቢት 4 2017
ወደ ሀገር ዉስጥ ገብቶ ለአርሶደሩ እየተሰራጨ የሚገኘዉ የአፈር ማዳበሪያ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሬ አለዉ ሲሉ አርሶደሮች ተናገሩ። አስተያየታቸዉን ለዶቼ ቬለ የሰጡ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙ አርሶደሮች የማዳበሪያ ዋጋዉ በቀናት ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ ጭማሬን ማሣየቱን ይናገራሉ።
«ከሁን በፊት በዚሁ ሰሞን ገዝተን የነበረዉ ከዛሬ አስራ አምስት ቀን በፊት 3,770 ብር አካባቢ ነዉ አሁን ላይ ደግሞ ከስድስት ሽህ ብሩ 12 ብር ነዉ የተመለሰልኝ። በጣም እጥፍ ጨመረብን አቤት ለማለት ወደየት እንሂድ ምን እንሁን?» ሌላው አርሶአደር ደግሞ «ባለፈዉ መጀመሪያ ላይ ለመስኖ 3,400 ብር ነበር አሁን 7,000 ገብቷል። አሁን ዛሬ ይህ ተገዝቶ ሀብታም የምትለዉም አልቻለዉም እንኳን ደሀ»
658ሺህ 249 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ወደ ሀገር ዉስጥ ገብቷል ቢባልም አቅም ካላቸዉ አርሶደሮች ዉጭ ማዳበሪያ ገዝቶ መጠቀም ከባድ ነዉ ይላሉ።
«አቅርቦቱ አለ አሁን የመጣ ማዳበሪያ አለ እስከመጨረሻ አርሶደሩን ያርካ አያርካ አይታወቅም አሁን በመስኖ ላይ የነበረ የማዳበሪያ ዋጋ 3,800 ተጀመረ አሁን ግን 5,870 ደረሰ 3ኩንታል ይጠቀም የነበረ አንድ ኩንታል ቢገዛ ነዉ አሁን። ማዳበሪያ እያወጡ ያሉት አላቸዉ የምትላቸዉ ናቸዉ እንጂ አብዛኛዉ ከታች ያለዉ ማዳበሪያ የማዉጣት እድሉ እየከበደበት ነዉ»
አርሶደሮቹ ከማዳበሪያ ጋር ተያይዞ አሁን ባለዉ ዋጋ ገዝቶ ለመጠቀም ብዙሀኑ እንደሚቸገር ገልፀዉ አሁን የተፈጠረዉ የኑሮ ዉድነት በግብርናዉ ዘርፍ ላይ ተፅኖ እንዳሳደረ ይገልፃሉ።
«የማዳበሪያዉ ጭማሬዉን ቃላት አይገልፀዉም። መድኃኒት ነዉ እንጂ እህልም እንደዚህ ሆኖ አያዉቅም። የሚቀመሰዉ እንኳን ማዳበሪያ ምንግዜም ኑሮ ዉድነት ኑሮ ዉድነት ይባላል የዘንድሮዉ የተለየ ነዉ። ያዉ ሽምብራዉን ጓያዉን መዝራት ነዉ። ማዳበሪያ የማይለዉን መድረሻ የጠፋዉ ነዉ ዛሬ»
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ እንደሚገልፁት የአፈር ማዳበሪያዉ ወደ አርሶደሩ ሲደርስ መንግስት ከፍተኛ ድጐማ ባያደርግበት ዋጋዉ ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችል ነበር ይላሉ።
«መንግስት ከፍተኛ የሆነ ድጐማ ተደርጎበት ነዉ ማዳበሪያዉ ዋጋዉ የቀነሰዉ እንጂ ባንድ ኩንታል ማዳበሪያ 10,400 ብር ነበር 3,779 ብር በኩንታል መንግስት ድጎማ አድርጓል።»
አሁን ላይ ወደ አርሶደሩ እየደረሰ ያለዉ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጭማሬን በተመለከተ ለአርሶደሩ የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየሰራን ነዉ የሚሉት አቶ ደመቀ አርሶደሮቹ የማዳበሪያ እጥረት እንዳይፈጠር ነዉ ስጋታቸዉ ይላሉ።
«አርሶደሩ በተገቢዉ መንገድ እንዲገነዘብ በማድረግ በኩል ወደታች ወርደን ግንዛቤ እየፈጠርን ነዉ ያለነዉ። በብዙ አካባቢዎች እጥረቱ እንዳይገጥመን እንጂ የዋጋዉን ሁኔታ ተቋቁመን እንወስዳለን የሚል ነዉ። አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ እንደዚህ አይነት ነገር ሊኖር ይችላል በቂ የሆነ ድጐማ ተደርጓል።»
በዚህ ጉዳይ ኃሳባቸዉን እንዲያካፍሉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ጋር በተደጋጋሚ ብንደዉልም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።
ኢሳያስ ገላው
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ